1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ምን ይዞ መጣ ?

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 9 2016

ኢትዮጵያ በቆላማ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል ያግዛል ያለችውን የ424 ሚሊየን ዶላር ፕሮጀክት መጀመሯን ዐሳወቀች ፡፡

Äthiopien | Dürre und Hunger in Tigray nehmen zu
ፎቶ ከማኅደር፦ ደረቃማ አካባቢዎችምስል Million Hailesilassie/DW

የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ምን ይዞ መጣ ?

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያ በቆላማ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል ያግዛል ያለችውን የ424 ሚሊየን ዶላር   ፕሮጀክት መጀመሯን ዐሳወቀች ፡፡ በሰባት ክልሎች እና በአንድ የከተማ አስተዳደር የሚተገበረው ፕሮጀክት ከ600 ሺህ በላይ ቤተሰቦችን በቀጥታ ፤ 2 ሚሊየን ሰዎችን ደግሞ በተዘወዋሪ ተጠቃሚ ያደርጋል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል ፡፡

የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ምን ይዞ መጣ ?

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በኢትዮጵያ ከጠቅላላ የቆዳ ሥፋት ሁለት ሦስተኛ በቆላማ አካባቢዎች የተሸፈነ ነው ፡፡  ከ15 ሚሊየን በላይ ህዝብም ይኖርበታል ተብሎ ይገመታል ፡፡ የቆላማ አካባቢው ለመስኖ ልማትና ለእንስሳት እርባታ የተመቸ መሆኑ ይነገርለታል ፡፡ ግን ደግሞ አካባቢው በተደጋጋሚ ድርቅ የሚያጠቃ ፤ ነዋሪው ዛሬም ሕይወቱን በድህነት የሚገፋ ነው   ፡፡

ከዓለም አቀፍ አበዳሪና ረጂ ተቋማት ጋር ሲመክር የከረመው የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን ላይ የቆለኛውን ኑሮ ለማሻሻል ያስችላል ያለውን የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል ፡፡ በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው የፕሮጀክት ማስጀመሪያ ሥነሥርዓት ላይ የተገኙት የመስኖና ቆላማ ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ ዶክተር እንዲሪያስ ጌታ ፕሮጀክቱ በሰባት ክልሎች እና በአንድ የከተማ አስተዳደር  ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ይተገበራል  ብለዋል ፡፡

የመስኖና ቆላማ ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ ዶክተር እንዲሪያስ ጌታምስል Shewangizawe Wegayehu/DW

በፕሮጀክቱ ምን ይከወናል ?

በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ ላይ እንደተገለጸው የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ የሚደረገው በአፋር ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ፣ ጋምቤላ ፣ ኦሮሚያ ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ፣ ሶማሌ ክልሎች እና በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ነው ፡፡ የፕሮጀክቱ ሁለተኛ ምዕራፍ ሊጀመር የቻለው ቀደምሲል የተካሄደው የምዕራፍ አንድ ፕሮጀክት  በዓለም አቀፍ አበዳሪና ረጂ ድርጅቶች ተገምግሞ ውጤታማ ሆኖ በመገኘቱ ነው ተብሏል ፡፡

የፕሮጀክቱ ዓላማ በአገሪቷ ቆላማ አካባቢዎች የሚገኙየአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ህይወት ለማሻሻል የሚያግዙ ተግባራት ለማከናወን መሆኑን የጠቀሱት የመስኖና ቆላማ ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ ዶክተር እንዲሪያስ ጌታ  "በዚህም ሥራው የሚከናወነው በክልሎቹ የተመረጡ 120 ወረዳዎች ውስጥ ነው ፡፡

ከሚከናወኑት ተግባራት መካከል የመሬት ለምነትን በዘላቂነት በመጠበቅ ፣ የእንስሳት መኖ ልማት፣ የሰብል እና የአትክልት ምርታማነት ማሻሻል ፣ የእንስሳት ጤና ፣ አነስተኛ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ይገኙበታል ፡፡ በተለይም በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ወቅቱን የጠበቀ መረጃ ለአርብቶ አደሩ  በመስጠት  የድርቅ ተጋላጭነትን የመቀነስ ሥራዎች ይከናወናሉ ፡፡ በዚህም 600 ሺህ አባወራዎችን በቀጥታ ፤ ከ2 ሚሊያን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በተዘዋዋሪ  ተጠቃሚ ይሆናሉ ። ከተጠቃሚዎቹ መካከል  ከ30 እስከ 50 በመቶ ወጣቶችና ሴቶች ናቸው " ብለዋል ፡፡

የደቡብ ኦሞ አርብቶ አደሩ ገመሮ አይኬ ምስል Shewangizawe Wegayehu/DW

የአርብቶአደሮቹ ተስፋ

የአፋር ክልል የአርብቶ አደር  ጽሕፈት ቤት ተወካይ ናስር ገነቶ እና የደቡብ ኦሞ አርብቶ አደሩ ገመሮ አይኬ በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ ላይ ከተገኙት መካከል ናቸው ፡፡  በመጀመሪያው የፕሮጀክቱ ምዕራፍ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን የጠቀሱት ናስር እና ገመሮ  ሁለተኛው ምዕራፍ ላይም ተስፋ ማድረጋቸውን ተናግረዋል ፡፡

ይህ ፕሮጀክት " የአፋር ክልል የጀርባ አጥንት " ሲሉ የገለጹት የክልሉ  የአርብቶ አደር ጽህፈት ቤት ተወካይ ናስር " በመጀመሪያው ምዕራፍ በትምህርት ቤት ግንባታ ፤ በመስኖ ልማትና ጥሩ ውጤት አይተናል ፡፡ ቀጣዩ ፕሮጅክትም ዕድሉ ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች ተመሳሳይ ጥቅምን ያስገኛል የሚል እምነት አለኝ " ብለዋል ፡፡

የአፋር ክልል የአርብቶ አደር ጽህፈት ቤት ተወካይ ናስር ገነቶምስል Shewangizawe Wegayehu/DW

ፕሮጀክቱ ከብት በማደለብ እገዛ ማድረጉን የተናገሩት የደቡብ ኦሞ አርብቶ አደሩ ገመሮ አይኬ " በተለይ የግጦሽ ቦታዎችን በመጠበቅና ከብቶችን በማደለብ እገዛ ሲያደርግ ቆይቷል ፡፡ ቀጣዩ ፕሮጀክትም የኑሮ ዘይቤያችንን በመለወጥ ያግዛል ብለን እንጠብቃለን  " ብለዋል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW