1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰሞኑ ቅዝቃዜ እና የበረታው የክረምት ዝናብ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 15 2016

በአዲስ አበባ ዛሬ ረቡዕ ነሐሴ 15 ቀን 2016 ዓ .ም እስከ ረፋድ ድረስ የበረታ ጭጋጋማ የአየር ፀባይ ተከስቷል። ከሳምንት በፊት የጣለው ከባድ ዝናብ መንግሥት ከጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራ ጋር በተያያዘ በተለይ ጉርድ ሾላ አካባቢ የተሽከርካሪ ፍሰት ያስተጓጎለ የጎርፍ አደጋ ተከስቶ ነበር።

የአዲስ አበባ ጎዳና ላይ ሰዎች ፣ ታክሲ እና መኪኖች
የአዲስ አበባ ጎዳናምስል Solomon Much/DW

This browser does not support the audio element.

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ ቅዝቃዜ ያለው የአየር ንብረት እየተስተዋለ እንደሆነ ይነገራል። የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት ባይደርስም ከሁለት ቀናት በፊት አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የጎርፍ አደጋ እንደነበር ገልጿል። የኢትዮጵያ ሜትሪዎሎጂ ኢንስቲትዩት በበኩሉ በቀጣዮቹ 10 ቀናት ተደጋጋሚ ከባድ ዝናብ እንደሚከሰት አስታውቋል።

ሰሞነኛው የአዲስ አበባ ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ

ባለፈው ሐምሌ ወር ኢትዮጵያ ውስጥ ከባድ ዝናብ ያስከተላቸው የሰው ሕይወት የቀጠፉ አምስት የመሬት መንሸራተት እንዲሁም የመሬት መሰንጠቅ አደጋዎች ተከስተዋል። ከሁለትና ሦስት ቀናት ወዲህ ደግሞ በዋና ከተማ አዲስ አበባ ከፍተኛ ቅዝቃዜ አዘል እንዲሁም ዛሬ ረቡዕ በጭጋግ የተሸፈነ የአየር ፀባይ ሁኔታ ተስተውሏል። ከከተማዋ ሰሜን አቅጣጫ ከእንጦጦ ጫካ ሥር ያሉ አካባቢዎች ይሄው ጭጋጋማ ሁኔታ ዛሬ ረፋድ በብርቱ ተስተውሎባቸዋል።

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ ቅዝቃዜ ያለው የአየር ንብረት ተስተውሏልምስል Solomon Much/DW

አዲስ አበባ ውስጥ ያለው የጎርፍ ተጋላጭነት ሁኔታ

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ - መንግሥታት ድርጅት (IGAD) የአየር ንብረት ትንበያ ማዕከል ከወር በፊት ባወጣው የክረምቱ ወራት የቀጣናው የአየር ጠባይ ትንበያ፤ በመካከለኛው እና ሰሜን ኢትዮጵያ፣ በኤርትራ፣ በሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ውስጥ ባሉ የተለያዩ አካባቢዎች ከቀደመው ጊዜ የበለጠ መጠን ያለው ዝናብ ይኖራል ብሎ ነበር። 

አዲስ አበባ ውስጥ ሰሞኑን እየጣለ ባለው ዝናብ አንዳንድ አካባቢዎች የተሽከርካሪ ፍሰት ጭምር ያስተጓጎለ ጎርፍ ጉርድ ሾላ አካባቢ ተከስቶ ነበር። 

የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ በዚህ ክረምት በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት ባይኖርምየጎርፍ አደጋ  አንዱ የከተማዋ ሥጋት መሆኑን ገልፀዋል። ተቋማቸው በቀጣይ የሚከሰቱ መሰል ችግሮች ላይ ምላሽ ለመስጠት ዝግጅት ማድረጉን አምልክተዋል።ከዚህ በተጨማሪ የድጋፍ ሥራ ማከናወን፣ የተደፈኑ የፍሳሽ ማለፊያ ቦዮችን የመክፈት እና የማጽዳት ሥራ ስለመከናወኑ እንዲሁም በወንዞች ዳር አካባቢ ኑሮ የመሠረቱ ሰዎች ካሉበት የችግር አካባቢ እንዲነሱ ቢደረጉም ተመልሶ የመሄድ ችግር መኖሩንም አብራርተዋል።

በቀጣዮቹ 10 ቀናት ተደጋጋሚ ከባድ ዝናብ እንደሚከሰት ተተንብይዋልምስል Solomon Much/DW

የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የቀጣይ ወራት ትንበያ

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አዲስ አበባን ጨምሮ በብዙ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚቀጥሉት 10 ቀናት ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው በኢንስቲትዩት የትንበያ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሳምነው ተሾመ ለዶቼ ቬለ ዛሬ የትንበያ መረጃውን አጋርተዋል። ተቋማቸው ክረምት ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑ አካባቢዎች "ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ ስርጭት" ይኖራል ሲል ትንበያ ማስቀመጡንም አብራርተዋል።

ባለፈው ሐምሌ ወር ላይ የደረሱ የተፈጥሮ አደጋዎች

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም. በተከሰተ የመሬት ናዳ ቢያንስ የ11 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ  ልክ የዛሬ አንድ ወር በዚሁ ክልል ጎፋ ዞን ውስጥ በደረሱ ሁለት ተከታታይ የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ከ250 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል። ከእነዚህ አደጋዎች ባለፈ ምንም እንኳን የሰው ሕይወት ላይ ጉዳት ባያደርስም በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ከተማ በደረሰ የመሬት መሰንጠቅ አደጋ፣ መስጂድን ጨምሮ የግለሰብ ቤት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወቃል።

ሰለሞን ሙጬ
ልደት አበበ
ዮሃንስ ገብረእግዚዓብሄር
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW