1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የበርሊኑ ጥቃትና የኢትዮጵያዉያን አስተያየት

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 14 2009

በሳምንቱ መጀመርያ በጀርመን መዲና በርሊን በተዘረጋዉ የጀርመናዊ ባህላዊ የገና ገባያ ላይ ጥቃት ከደረሰ ወዲህ ፤ በሃገሪቱ በየዓመቱ በሚጠበቀዉ የጀርመናዉያኑ የገና በዓል አከባበር ላይ የሃዘን ጥላ ያንዣበበበት ይመስላል። በጀርመን የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን የጀርመናዉያኑን ገና እንዴት ይሆን የሚያከብሩት? ኢትዮያዉያንን አስተያየት አሰባስናል።

Berlin Breitscheidplatz Wiedereröffnung Weihnachtsmarkt
ምስል DW/F. Hofmann

Kultur_REAX_ Äthiopier über Anschlag/Berlin. Wie feiern sie Deutsche Weihnachten - MP3-Stereo

This browser does not support the audio element.

    

በጀርመናዉያኑ ዘንድ በደማቅ ሥርዓት የሚከበረዉ የገና በዓል በገና ዛፍ ማለት ጥዱን አሽቆጥቁጦ፤ በገና ገበያ በቅርንፉድ ቀረፋ የተፈላዉን ወይን ይዞ፤ የገና አባት የተባለዉን ባለነጭ ሪዛም ሽማግሌን ስጦታ አሸክሞ፤ ቤተሰብን አሰባስቦ በመምጣቱ በጉጉት ይጠበቃል። በሳምንቱ መጀመርያ ታኅሳስ 10 ቀን ሰኞ ምሽት በበርሊን ከተማ በተዘረጋዉ በባህላዊዉ የገና ገበያ ላይ የደረሰዉ ጥቃት በርግጥ በጉጉት የሚጠበቀዉን ይህን በዓል ጥላ ሳያጠላበት አልቀረም። እንድያም ቢሆን በርካታ ጀርመናዉያን በተለያዩ የብዙኃን መገናኛዎች በሚሰጡት አስተያየት ጥቃቱ የፈሪ ነዉ ፤ ለፈሪ ደግሞ ባህላችን እና አኗኗራችንን አንቀይርም ሲሉ ይናገራሉ።

የበርሊን ነዋሪዎች ቦታዉ ላይ በመገኘት ኃዘናቸዉን እየገለጹ ነዉምስል picture-alliance/dpa/B. Pedersen

ጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን የጀርመናዉያንን ገናን በዓል እንዴት ያከብሩታል፤ በበርሊን የደረሰዉ ጥቃት የአከባበር እቅዳቸዉን ቀይሮት ይሆን?።

በጀርመን የገና በዓል  በየዓመቱ በጎርጎረሳዉያኑ ታህሳስ 24 ማለት ምሽት ጀምሮ መከበር ይጀምራል። በጎርጎረሳዉያኑ ታሕሳስ 24 ማለት ዲሴምበር 24 ምሽት ፤ እየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ቅዱስ ምሽት፤ በነጋታዉ ታህሳስ 25 ቀዳማዊ ገና፤ ታህሳስ 26 ቀን ደግሞ ዳግማዊ ገና ሲሉ ጀርመናዉያን በተከታታይ ቀናት ከቤተሰብ ጋር በእርጋታ ያከብሩታል።

ጀርመናዉያን በገና በዓል አከባበር ከሌሎች አዉሮጳዉያን የሚለዩት ደግሞ፤ ያዉ ከአራት ሳምንታት ጀምሮ በዓሉ እስከሚከበርበት ድረስ፤ በሚዘረጉት በገና ገበያቸዉ እና፤ በቀረፋ ቅርንፉድ በተቀመመዉና በተፈላዉ በወይን መጠጣቸዉ ነዉ። የገና በዓል ሊከበር አራት ሳምንት ሲቀረዉ ጀምሮ በየእሁዱ አንዳንድ ሻማን ያበራሉ፤ የበዓሉን መምጣት ይጠባበቃሉ። በየከተማዉ መሃል የሚዘረጋዉም ባህላዊዉ የገና ገበያም ቢሆን የገና በዓል ሊከበር አራት ሳምንት ሲቀረዉ ነዉ የሚዘረጋዉ። በዚህ ገበያ  የሕጻናት የአዋቂዎች መጫወቻና መዝናኛ ቦታዎች ይገኛል፤ ምግብ መጠጡም ቢሆን በገፍ የሚቀርብበት ቦታም ነዉ። በርግጥም የጀርመናዉያን ዋንኛ ባህላዊ እንቅስቃሴ የሚታይበት ቦታ ነዉ። ባለፈዉ ሰኞ ታኅሳስ 10 በበርሊን እንብርት ላይ በተዘረጋዉ የገና ገበያ ላይ ጥቃት ደርሶ ሰዎች በመገደላቸዉ በርግጥ በዓሉ ላይ የሃዘን ጥላ ያጠላበት ይሆን ? በጀርመን ሲኖሩ ከ 20 ዓመታት በላይ ያስቆጠሩትና በበርሊን ይኸዉ አደጋ ከደረሰበት ብዙም ሳይርቅ የሚኖሩት አቶ ደረጀ መንገሻ ድርጊቱ እንዳሳዘናቸዉ ይናገራሉ።  

በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት በሶቭየት ኅብረት ቦንብ የተመታዉ በርሊን እንብርት ላይ የሚገኘዉ ቤተ-ክርስትያንምስል Getty Images/A. Rentz

«በጣም በጣም የሚያሳዝን ነዉ። ባለፉት ዓመታት በሌሎች ሃገራት ላይ የደረሱትን የሽብር ጥቃቶች ታዝበናል። በጀርመን ሃገር አንጻራዊ ሰላም ነበር። እንደሚታወቀዉ በጀርመን ገና በዓል፤ በከተማ መሃል በሚዘረጋዉ የገና ገበያ ቦታ ቤተሰቦች ሕጻናት ልጆቻቸዉን ዘመዶቻቸዉን ጓደኞቻቸዉን ይዘዉ ነዉ የሚሄዱት። ገበያዉ ቦታ ልዩ ልዩ መጫወቻ ቦታዎች አሉ፤ መዝናኛ ቦታዎች ተዘጋጅተዉ ይገኛሉ። ቤተሰብ ሁሉ የሚሰባሰብበት ቦታም ነዉ ።እና ይህ ጥቃት ሰዉ የሆነን ሰዉ ሁሉን የሚያሳዝን ልብ የሚሰብር ድርጊት ነዉ። በዚህም ወቅቱ የሃዘን ድባብ ያጠላበት ሆንዋል። እርግጥ ይህን ነገር በሃዘን ብቻ ማለፍ ሳይሆን፤ ይበልጥ ሽብርተኝነትን ለመታገል ሕዝቡ የበለጠ ቆርጦ መነሳት እንዳለበት የሚያመላክትም ነዉ ብዬ ነዉ የማስበዉ።»    

በበርሊን እንብርት ላይ የሚገኘዉ የጀርመን ባህላዊ የገና ገበያ የተዘረጋዉ ታሪካዊ ቦታ ነዉ ያሉን አቶ ደረጀ፤ ገበያዉ የተዘረጋበት አደባባይ ላይ የሚገኘዉ ቤተ-ክርስትያን ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት በከፊል የተረፈ ነዉ።

« ቤተ-ክርስትያኑ በሁለተኛዉ ዓለም ጦርነት ጊዜ በቦምብ የተመታ ነዉ። የቤተ-ክርስትያኑ ጉማጅ አሁንም እዝያዉ ቦታ ይገኛል በርግጥ አሻሽለዉታል፤ ቤተ-ክርስትያኑ አሁንም ፀሎት ይካሄድበታል፤ አላፊ አግዳሚዉ፤ የሃገር ጎብኝዉ ሁሉ የሚመጣበት ቦታ ነዉ። ድሮ ምዕራብና ምስራቅ ጀርመን በነበረበት ጊዜ የምዕራብ በርሊን ማዕከላዊ የሚባል ቦታ ነበር። ሰዉ ሁሉ የሚገኛኝበት ቦታ ነበር፤ አሁን በርሊን ከተማ ስለሰፋ ብዙ  ማዕከላዊ የሚባል ቦታ ተፈጥሮአል። ድሮ ግን ይህ ቤተ-ክርስትያን የሚገኝበት ቦታ ሰዉ የሚገናኝበት ማዕከላዊ የታወቀ ቦታ ነበር፤ ልክ እኛ ሃገር ፒያሳ እንደሚባለዉ ቦታ ማለት ነዉ። »

የበርሊን ነዋሪዎች ቦታዉ ላይ በመገኘት ኃዘናቸዉን እየገለጹ ነዉምስል picture-alliance/dpa/B. Pedersen

በጀርመን ብሎም በአዉሮጳ የገና በዓል በድምቀት ይከበራል ያሉን በጀርመን ሲኖሩ ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ ያስቆጠሩት ወ/ሮ ባዩሽ አበበ በበኩላቸዉ

« አዉሮጳዉያን በብዛት የክርስትና እምነት ተከታዮች ናቸዉ። የገና በዓል ደግሞ በጣም በከፍተኛ ሁኔታ የሚከበር ትልቅ በዓል ነዉ። አብዛኞቹ ነዋሪዎች ከጥንት ከብዙ ሺህ ዘመን ጀምሮ የክርስትና እምነት ተከታዮች ናቸዉ ፤ ስለዚህ የገና በዓል ከፋሲካም ከማንኛዉም በዓል በላይ በድምቀት ይከበራል፤ ቤተሰብም ከተለያየ ቦታ የሚሰባሰብበት በዓል ነዉ»

ወ/ሮ ባዩሽ በመቀጠል እንደተናገሩት በርሊን ጀርመን ላይ የተከሰተዉ ጥቃት ቢያሳዝንም ጀርመናዉያን ችግሩን ለመፍታት ወደፊት ስልሚያዩ  በገና በዓል አከባበር ላይ ለዉጥ አያመጣም።

« እነዚህ ነገሮች እኮ በዓለም ላይ አሁን እየተደጋገመ የምናየዉ ነዉ፤ በተለያዩ  የዓለም ሃገራት ማለቴ ነዉ። ስለዚህ ጀርመናዉያን ጠንካሮች ናቸዉ ብዙ ያለፉ ናቸዉ። በርግጥ ጥቃቱ ቤተሰብን የጎዳ ቢሆንም አካባቢዉን የጎዳ ቢሆንም፤ እንዲሁም ሕዝብ በተሰበሰበበት ቦታ ይህ ጥቃት ስለተፈፀመ ያሳዝናል እንጂ ፤ በገና በዓላቸዉ ላይ ያንን ያክል ተጽኖ የሚያመጣ አይሆንም። ጀርመናዉያን ብዜ ጊዜ ወደፊት ነዉ የሚመለከቱት፤ አንድ ችግር ላይ ቆመዉ አይቆዩም »

በጀርመን ኢትዮጵያዉያን በመሰባሰብ በተለያዩ ማኅበራትና ስፖርታዊ ዝግጅቶችና ኢትዮጵያዊ ባህላዊ ክንዉኖች ከሚታዩባቸዉ ከተሞች በተለይ ኑረምበርግ ከተማ የሚገኙት ኢትዮጵያዉያን ልቀዉ ይገኛሉ። በኑረምበርግ ከተማ የሚገኘዉ የገና ገበያ በጀርመን ከሚገኙት የገና ገበያዎች ሁሉ የላቀ መሆኑ ይነገርለታል። በኑረምበርግ የኢትዮጵያዉያን ማኅበር ዉስጥ በመሥራታቸዉ የሚታወቁት የኑረምበርግ ነዋሪ አቶ ካሱ ለገሰ ፤ እንደሚሉት በጀርመን የደረሰዉ ጥቃት በጣም የሚያሳዝን ነዉ የገና ስሜትን ረብሽዋል፤

ጥቃት አድራሹ ተጠርጣሪ የቱኒዚያ ተወላጅ አኒስ አምሪ እየታደነ ነዉምስል picture-alliance/dpa/Bundeskriminalamt

« ይህ አይነቱ ሁኔታ በተለያዩ አዉሮጳ ሃገራት እየተከሰተ ነዉ ። በጀርመን ላይም ሊከሰት ይችላል ተብሎ ጥበቃ ቢደረግም ያዉ በርሊን ላይ ጥቃት ሊጣል ችሎአል። በርግጥ እንዲህ አይነቱ ጥቃት እንዴትና የት ሊከሰት እንደሚችል መገመቱ አስቸጋሪ ነዉ። እኔ በምኖርበት በኑረንበርግ ከተማ የገና ገባያ በታም ታዋቂ ነዉ ጥበቃዉ በጣም ጠንካራ ነዉ። በበርሊን ጥቃት ከደረሰ በኋላ ጥበቃዉ ይበልጥ ተጠናክሮ አይቻለሁ። እናም በዚህ ዓመት ብቻ በኒዛ፤ በቤልጄም፤ በጀርመንም ቢሆን በተለያየ ሁኔታ ጥቃትን አይተናል፤ የአሁኑ የበርሊኑ ጥቃት በጣም የሚያሳዝን ነዉ የገና ስሜትን ረብሽዋል፤ በጣም የሚሳዝን ነዉ፤ እንግዲህ ከእንዲህ አይነቶች ጋር አብሮ መኖር ነዉ። »

በጀርመን ስኖር ወደ 27 ዓመት እንደሆናቸዉ የነገሩን ዶክተር ለማ የጀርመናዉያኑን ገና እንደ ማኅበረሰቡ ሁሉ እንደሚያከብሩ ነግረዉናል።  በዝግጅቱ ቃለ ምልልስ የሰጡን ለጀርመናዉያኑ መልካም የገና በዓልን ተመኝተዋል። የፈረንጆቹን ገና በዓልን ለምታከብሩ የዶይቼ ቬለ ተከታታዮች በሙሉ መልካም የልደት በዓል እያልን ቃለ ምልልስ የሰጡንን በማመስገን ሙሉ ቅንብሩን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን!  

አዜብ ታደሰ

ነኃሽ መሃመድ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW