1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የበርበራ ወደብ እና የደቡብ አፍሪቃ ፖለቲካ

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 15 2015

በአፍሪቃ ቀንድ የበርበራ ወደብን የማስፋፋት ሥራ እየተሠራ ነው። 400 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ወደብ ዋነኛ ተጠቃሚ ኢትዮጵያ እንደምትሆን ነው የተገለጸው። ተቀናቃኞቻቸው ጠንካራ ዘመቻ ቢከፍቱባቸውም የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ ለገዢው ፓርቲ ANC ሊቀመንበርነት በድጋሚ ተመርጠዋል።

Hafen Berbera Somaliland
ምስል Jonas Gerding/DW

ትኩረት በአፍሪቃ

This browser does not support the audio element.

በአፍሪቃው ቀንድ፤ የበርበራ ወደብ መስፋፋት

በጭነት ማጓጓዣው መርከብ ሰማያዊ የዕቃ የማጫኛ ክፍል አንዱ መኪና ከሌላው ኋላ ተደርድሮ ከወደቡ ቆመ። ሦስት የዕቃ ማንሻዎች ወይም ክሬኖች በመርከቡ ላይ አንዣበቡ እና አንዱን ዕቃ መጫኛ ኮንቴይነር የያዘውን ከባድ መኪና ወደ ላይ አነሱት። መርከቡ የዚህ አይነት አምስት ጭኗል።  የደህንነት ሰደሪያ የለበሱት ጢማሙ መሐመድ አቴይ ከዳር ቆመው ያስተውላሉ። ለመጀመሪያ ጊዜ በጎርጎሪዮሳዊው 2021 ዓም በይፋ የተከፈተው 400 ሜትር ርዝመት ያለው የሶማሊላንድ በርበራ ወደብ የፈረቃ ሥራ አስኪያጅ ናቸው። ከዚህ ቀደም እንዲህ ያለው ሥራ ሲከናወን በሠራተኞቹ ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት ያስከተለ አደጋ ያጋጠመበት ጊዜ እንደነበር አቴይ ይናገራሉ። ዛሬ ግን ዕቃውን የሚያወርደውን መሣሪያ የሚያንቀሳቅሱት ሠራተኞች ከርቀት መሥራት ችለዋል። ይህ ደግሞ ሥራቸውን ለማቀላቸፍ እረድቷቸዋል።

የሶማሊላንድ ወደብ በርበራምስል Jonas Gerding/DW

እንዲህ ላለው ሥራ ገንዘብ የሚመጣው የተባበረው አረብ ኤሜሬቶች ንብረት ከሆነው DP ወርልድ ከተሰኘው ኩባንያ ነው። DP ወርልድ በመላው ዓለም የወደብ አገልግሎትን በመገንባት ከተሰማሩት ትላልቅ ኩባንያዎች አንዱ በመሆን ይታወቃል። ይህ የግል ኩባንያ በ34 ሃገራት ውስጥ የሚሠራ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 12ቱ የሚገኙት አፍሪቃ እና መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ነው።

ሶማሊላንድ ምስል DW/J. Jeffrey

ዕቃዎች እየተመሩ በበርበራ ነጻ የንግድ ቀጣና በኩል በመርከብ ይጓጓዛሉ። ወደ ጎረቤት ኢትዮጵያም ይገባሉ፤ ከዚያም ይወጣሉ። DP ወርልድ በዚህ የወደብ ፕሮጀክት ላይ 442 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ሥራ ላይ ለማዋል እና በምላሹም ለ30 ዓመታት ለማስተዳደር ይፈልጋል። ውሉ ኤኮኖሚያዊ አደጋ ሊያመጣ፤ በፖለቲካው በኩልም ሌላ ጥንቃቄ የሚያሻው ነው። ሶማሊላንድ ምንም እንኳን ከጎርጎሪዮሳዊው 1991 ዓ,ም ጀምሮ ከሶማሊያ ተነጥላ እራስ ገዝ ብትሆንም ዓለም አቀፍ እውቅና የማግኘት ጥያቄዋ ገና አልለየለትም።

ሱፓቺ ዋታናቬራቺ የሙቀት ሁኔታን በሚያስተካክል የቢሯቸው መስኮት አሻግረው በመቶዎች የሚቆጠሩትን የዕቃ ማጓጓዣዎች ከነዕቃ ማውረጃዎቹ መመልከት ይችላሉ። ታይላንድ ውስጥ የተወለዱት ዋታናቬራቺ የኢንፎርሜሽን ቴክኒዎሎጂ ባለሙያ ሲሆኑ ብራዚል እና ኔዘርላንድ ውስጥ በዘርፉ ሠርተዋል። አሁን ደግሞ እያደገ ባለው የአፍሪቃ ቀንድ የDP ወርልድ ሥራ አስኪያጅ ናቸው።

«በአፍሪቃውን ቀንድ ኢትዮጵያን ብቻ ስንመለከት። የሕዝቧ ብዛት ስንት ነው? ከመቶ ሚሊየን በላይ። ኬንያስ ስንት ነው? ይህን ጨምረን፤ በአፍሪቃው ቀንድ ብቻ ወደ 200 ሚሊየን ሊጠጋ ይችላል። ኢትዮጵያ ደግሞ ወደብ አልባ ሀገር ናት። ሀገሪቱ የሚያስፈልጋትን ለማግኘት በርካታ መግቢያዎች ያስፈልጓቸዋል። በርበራ ደግሞ ስልታዊ ቦታ ላይ ነው ያለችው። ከበርበራ እስከ አዲስ አበባ ያለውን እርቀት ብንመለከት፤ 900 ኪሌ ሜትር ገደማ ነው። ከጅቡቲ ጋር ተመሳሳይ ነው። ዛሬ 90 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ የዕቃ ጭነት በጅቡቲ በኩል የሚገባ ነው ማለት ይቻላል። ሆኖም ኢትዮጵያ በአንድ ወደብ ብቻ መተማመን አትችልም።»  

የሶማሊላንድ የገንዘብ ምንዛሪ ገበያምስል DW/J. Jeffrey

በዚህ አካባቢ ካለው የወደብ ተጠቃሚነት ፍላጎት አኳያ ሶማሊላንድ ሰፊ ዕድል እንዳላት ነው የሚናገሩት። ኩባንያቸው ትርፍ ፈላጊ ቢሆንም በረዥም ጊዜ ውስጥ ያንን ያገኛል ብለው ያስባሉ። ትርፍ ከማግኘታቸው አስቀድሞ ግን የአካባቢውን ነዋሪዎች የተሻለ ኑሮ እንዲኖራቸው ያስፈልጋል ብለው ያምናሉ። እሳቸው እንደሚሉትም ባለፉት አምስት ዓመታት ያንን የሚያመላክት ሥራ ተሠርቷል። 2,700 የሥራ ዕድሎች ተፈጥረዋል፤ 116 ሚሊየን ዶላር ለማኅበራዊ እና ለአካባቢው ማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራ ላይ ውሏል። የሀገሪቱ መንግሥት ደግሞ 87 ሚሊየን ዶላር ቀረጥ አግኝቷል። በበርበራ ወደብ የነጻ ንግድ ቀጣና በኩል ወደ ሌላ ሀገር የሚላኩ ዕቃዎች ቀረጥ አይከፈልባቸውም፤ ከውጭ የሚገቡ ከሆነ ግን አስገቢው አካል ቀረጥ ሊከፍል ግድ መሆኑን በዚህ የሥራ ኃላፊነት ላይ የሚገኙት ኬንያዊው ጆሴፍ ኦጉታ የተናገሩት። የወደቡ የነጻ ንግድ ቀጣና በመጪው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2023 መባቻ ሥራውን ይጀምራል። ሶማሊላንድ የሕዝቧ ብዛት 4,2 ሚሊየን ብቻ ነው። DP ወርልድ በዚህ ወደብ ከሚጓጓዘው ጭነት ሦስት አራተኛው ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ እንደሚሆን ይገምታል።

ሰፊው የበርበራ ወደብ ገጽታምስል Jonas Gerding/DW

ሜይ ዳርዊች በበርሚንግሃም ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ናቸው። ቀደም ሲል በመካከለኛው ምሥራቅ ላይ ያተኮረ ጥናት ያደርጉ ነበር, አሁን ደግሞ የባሕረ ሰላጤው ሃገራት በአፍሪቃ ቀንድ በመሠረተ ልማት ላይ የሚያደርጉትን የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ይመረምራሉ። ቀደም ሲል ወደ ጅቡቲ፤ አሁን ደግሞ ወደ በርበራ ተጉዘው ተመልክተዋል።

«እጅግ መጣም አደጋ ነው። የሶማሊላንድ መንግሥት አብዛኛውን ገቢውን ከቀረጥ ነው የሚያገኘው፤ ይኽ ደግሞ ሊቀር ይችላል። ያ ደግሞ ከገቢ አኳያ ኪሳራ ነው። ከዚህ ይልቅ ማለቴ ሶማሊላንድ አንዳንድ የንግድ፤ የመዋዕለ ንዋይ አፍሳሾችን መምጣት በተመለከተ እድገት ማየት ትፈልጋለች። እንደሚመስለኝ ያ ነው ተስፋው።» ይላሉ። ከመነሻው ኢትዮጵያ ከፕሮጀክቱ 19  በመቶ ድርሻ በመውሰድ በዚህ ለመሳተፍ ፈልጋ ነበር። ሆኖም ትግራይ ክልል የተቀሰቀሰው ጦርነት የኤኮኖሚ ቀውስ በማስከተሉ አልተሳካላትም። ኮቪድ 19ም እንዲሁ የዓለምን ንግድ ጎድቷል። አሁን DP ወርልድ 65 በመቶውን ድርሻ ይዟል፤ የፕሮጀክቱን 35 በመቶ የያዘችው የወደቡ ባለቤት ሶማሊላንድ ብትሆንም ውሳኔ የመስጠት አቅም ግን የላትም። ይህ ደግሞ ለውጪ የፖለቲካ ጫና የተጋለጠ እንደሚያደርገው ዳርዊች አመልክተዋል።

የደቡብ አፍሪቃ ፖለቲካ፤ ራሞፎሳ ዳግም የገዢው ፓርቲ መሪ መመረጣቸው

 

ዳግም ለገዢው ፓርቲ መሪነት የተመረጡት ሲሪል ራማፎሳምስል Denis Farrell/AP Photo/picture alliance

ምንም እንኳን ተቀናቃኞቻቸው ጠንካራ ዘመቻ ቢከፍቱባቸውም የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ ለገዢው ፓርቲ የአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት በእንግሊዝኛ ምህጻሩ ANC ሊቀመንበርነት በድጋሚ ተመርጠዋል። ከፋይናንስ ጋር በተገናኘ ቅሌት የሚከሰሱት ራማፎዛ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ዳግም የANC መሪነትን መያዛቸው ሥልጣናቸውን ለማጠናከር ጠቅሟቸዋል እየተባለ ነው። በመጪው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2024 ላይ በሀገሪቱ በሚካሄደው ምርጫም ለፕሬዝደንትነት ለሁለተኛ ጊዜ ለመወዳደር ጥርጊያውን አመቻችቶላቸዋል። የሀገሪቱን ፖለቲካ በቅርበት በሚከታተሉ ወገኖችም አጋጣሚው ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ እንዲደረግ ብዙዎች የሚመኙትን የአስተዳደር ማሻሻያ ሂደት አዳጋች ሊያደርገው እንደሚችል ተገምቷል።

በገዢው ፓርቲ ANC ውስጥ ከእሳቸው ጋር የተመረጡት አባላት የራማፎሳ ጠንካራ ደጋፊዎች መሆናቸውን ነው የሚነገረው። የብሪታኒያው የፖለቲካ ተንታኝ ተቋም ቻተም ሀውስ ከፍተኛ ተመራማሪ ክሪስቶፈር ቫንዶምም ይህንኑ ያረጋግጣሉ።

ሲሪል ራማፎሳ በደጋፊዎቻቸው ተከብበውምስል Jerome Delay/AP Photo/picture alliance

«በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ሥልጣን ካሉት ሰባቱ ከጎናቸው ናቸው፤ ጠንካራ የደጋፊዎች ቡድን በዙሪያቸው አለ። ይህ ማለት ደግሞ የፖሊሲ አጀንዳዎቻቸውም በተለይም ለፓርቲው የሚያቀርቡትን አጀንዳ ለማሳለፍ ቀላይ ይሆንላቸዋል።» ነው የሚሉት።

ለፓርቲው ሊቀመንበርነት በተካሄደው ምርጫ የራማፎዛ ተፎካካሪ ሆነው የቀረቡት የሀገሪቱ የቀድሞ የጤና ሚኒስትር ዝዋሊ ማኪዚ ነበሩ። ፓርቲያቸው ANC በውስጡ ክፍፍል ከተፈጠረ ውሎ አድሯል። ገሚሱ ከቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ጄኮብ ዙማ ጎን ሲሆን በፓርቲው ውስጥ ማሻሻያ እንዳይደረግ እንቅፋት በመሆን ይወቀሳል። የደቡብ አፍሪቃው ታዋቂ ጋዜጣ ዘ ዴይሊ ማቭሪክ እንደሚለው ለፓርቲው ሥራ አስኪያጅ ኮሜቴነት ከተመረጡት 80 አዲስ አባላት አንድ አራተኛ የሚሆኑት የቀድሞ የጤና ሚኒስትር ማኪዚን ጨምሮ የራማፎዛ ረቃዋሚዎች ናቸው። ለፓርቲው ሊቀመንበርነት ተወዳድረው የአባላቱን 43 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸው ራማፎሳ በANC ውስጥ ጠንከር ያለ ተቃውሞ ሊገጥማቸው እንደሚችል ማመላከቻ መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ። ካቢኔው ውስጥ የሚገኙት ሁለቱ የራማፎሳ ተቺዎች ገለል ተደርገዋል። የትብብር ጉዳዮች ሚኒስትር የሆኑት ናኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ለፓርቲው ፕሬዝደንትነት እጩ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ድጋፍ አላገኙም። ፕሬዝደንቱን በድፍረት በመተቸት የሚታወቁት የቱሪዝም ሚኒስትር ሊንዲዌ ሲሱሉም በANC ጉባኤ ወቅት ከሌሎች ተነጥለው መገኘታቸው በፓርቲው ውስጥ ሹም ሽር መኖሩ አይቀሬ ነው አስብሏል።

የANC ምርጫ ቅስቀሳምስል picture-alliance/ dpa

ፓርቲው ውስጡን ከማስተካከል በተጨማሪ የደቡብ አፍሪቃውያንን አመኔታ ዳግም የማግኘት ከባድ ሥራ ከፊቱ ተቀምጧል። ፓርቲው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ጉባኤውን ሲያካሂድ በቀረበው ዘገባ መሠረት ባለፉት አምስት ዓመታት የአባላቱ ቁጥር በእጅጉ ቀንሷል። በመላው ደቡብ አፍሪቃ በቀን ለሰባት ሰዓታት ገደማ የኤሌክትሪክ ኃይል ይቋረጣል፤ የሥራ አጡ ቁጥር 37 በመቶ ደርሷል፤ በዚያም ላይ ሙስና የመንሰራፋቱ ነገር ሕዝቡን አሰላችቷል። ዶቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው ደቡብ አፍሪቃዊው ደራሲ እና የፖለቲካ ተንታኝ ሉክሆና ማንጉኒ ራማፎሳ ከፓርቲው ማሻሻያ ጎን ለጎን በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ አፋጣኝ መፍትሄ የሚሹ ችግሮች ከፍታቸው መደቀናቸውን ይገልጻሉ።

ይኽ ብቻም አይደለም ራማፎሳ እሳቸውን ለሚመለከት ሌላ ችግርም እንዲሁ መፍትሄ ማፈላለግ ይጠብቃቸዋል። ባለፈው ሳምንት ነበር የፓርቲያቸው አባላት ከግል ድርጅታቸው ጋር በተገናኘ ቀረበባቸው ቅሌት ምክንያት ከሥልጣን እንዲነሱ የተጀመረውን ድምጽ የማሰባሰብ ሂደት በአብላጫ ድምጽ የቀለበሱት። የአደን ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ባለቤት የሆኑት ራማፎሳ ድርጅታቸው በርከት ያለ የውጭ ምንዛሪ በመደበቅ ቢከሰስም እሳቸው ግን የተጠቀሰው ድርጅታቸው በኪሳራ እንደሚንቀሳቀስ መናገራቸው ተሰምቷል። ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በፖለቲካው ውስጥ ከፍተኛ ሚና ያላቸው ወገኖች በግሉ የንግድ ዘርፍ በመሰማራት ገንዘብ ማካበታቸው የተለመደ እንደሆነ የቻተም ሀውስ ጆሀንስበርግ ጽሕፈት ቤት ባልደረባ የሆኑት ቫንዶም ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል።

የፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ የአንደን ስፖርት ማዘውተሪያ ምስል AP Photo/picture alliance

የANC ፓርቲ መሪዎች በሚቀርብባቸው የሙስና ክስ ምክንያት በሕዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት እየቀነሰ መምጣቱ እየታየ ቢሆንም ራማፎሳ ግን በዚህ ሁሉ ውዝግብ መሀል የብዙዎችን ድጋፍ አግኝተው ዳግም የገዢው ፓርቲ ሊቀመንበር ሆነዋል። እንዲያም ሆኖ ግን ከአንድ ዓመት በኋላ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በሚካሄደው ምርጫ አሁን ለANC ሊቀመንበርነት ዳግም ያበቃቸው ተቀባይነት ይዘልቅ ይሆን የሚለው በጥያቄነት እንደሚቆይም ቫንዶም ያመለክታሉ። ምክንያቱ ደግሞ ሀገሬው የተሰላቸባቸው እንደ የኃይል አቅርቦት ችግር እና የሥራ ፈጠራ ለመሳሰሉ መሠረታዊ ጉዳዮች ቃል በገቡት መሠረት እስካሁን ትርጉም ያለው መፍትሄ ማምጣት አለመቻላቸው እንደሆነ ይነገራል። ይህ ደግሞ በቀጣይ ደቡብ አፍሪቃን እስካሁን እንደነበረው በANC ገዢ ፓርቲነት መተዳደሯ ቀርቶ ጥምር ፓርቲ ሊመራት ይችላል የሚል ግምትን አስከትሏል።

ሸዋዬ ለገሠ/ዮናስ ጌርዲንግ/ ክርስቲና ክሪፓል

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW