የበዓላት ወቅት የሳይበር ጥቃቶች እና ጥንቃቄዎቻቸው
ረቡዕ፣ መስከረም 2 2016
በዓለም አቀፍ ደረጃ የበዓላት ወቅት ከሌሎች ጊዜያት በተለየ መልኩ በቀላሉ የመረጃ ጥቃቶችን ለማድረስ ለሳይበር ወንጀለኞች የተመቸ ነው። ምክንያቱም ሰዎች በበዓላት ሰሞን ትኩረታቸው እንደሚከፋፍል የሳይበር ወንጀለኞች ጠንቅቀው ያውቃሉ። የበዓል ወቅት ሰዎች ስጦታዎችን ፣ለበዓል ፍጆታ የሚውሉ ሸቀጦችን እና ሌሎች የበይነመረብ ግብይቶችን በማከናወን እንዲሁም ከወዳጅ ዘመድ ጋር የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክቶችን በመለዋወጥ ረዘም ላለ ጊዜ በይነመረብ ላይ የሚቆዩበት እና ከወትሮው በበለጠ የሞባይል ስልኮቻቸውን የሚጠቀሙበት ጊዜም ነው። ግብይት በጨመረ ቁጥር ደግሞ የሸማቾችን መረጃ የበለጠ የማግኘት ዕድል ስላላቸው የሳይበር ወንጀለኞች ጥቃቶችን ለመፈፀም እድል እንዲያገኙ በር ይከፍታል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት 24% የሚሆኑት ጥቃቶች ከዚሁ ጋር ተያይዞ ይፈፀማሉ። ለምሳሌ ራንሰምዌር የሚባለው መረጃን በመያዛዣነት የሚጠቀመው የጥቃት አይነት በበዓላት ወቅት ከመደበኛ ወራት ጋር ሲነፃፀር 30% ይጨምራል።በኢትዮጵያም በዓልን ጠብቀዉ በሚፈጸሙ የሳይበር ጥቃቶች የገንዘብ እና የማንነት ስርቆቶች እንዲሁም የማጭበርበር ተግባራት በተለያዩ የበዓላት ወቅቶች እንደሚፈፀሙ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የዛሬ ዓመት ገደማ ያወጣው መረጃ ያሳያል።እየጨመረ የመጣው የሳይበር ጥቃት በኢትዮጵያየሳይበር ደህንነት ባለሙያው አቶ ብሩክ ወርቁም ሰዎች በበዓላት ሰሞን ትኩረታቸው በሙሉ በበዓላቱ ላይ መሆንም ለሳይበር ጥቃቶች ተጨማሪ ምክንያት ነው ይላሉ።
«በበዓላት ጊዜ የሳይበር ጥቃቶች በዓለም አቀፍ ደረጃም የሚጨምሩ ነው የሚሆነው።ያው የሳይበር ጥቃት ፈጻሚዎች አያርፉም ሁል ጊዜ ነው የሚሰሩት ። 365ቱን ቀናት ነው የሚሰሩት።ከዚያ በተጨማሪ ግን በበዓት ወቅት በጣም አክቲቭ ይሆናሉ።ለዚያ ደግሞ የተለያዩ ,ምክንያቶች አሏቸው። ከምክንያቶቹ ዋናው ሰዎች በጣም «ፌስቲቭ» መሆን ወይም «ፎከሳቸው»ን ክብረ በዓላት ላይ በማድረጋቸው የተነሳ ለነሱ/ለሳይበር ጥቃት ፈጻሚዎች/ የሚመቹ መደላድሎች መፈጠሩ ነው።ለምሳሌ ኢሞሽናቸው ከፍ ማለት እና ትኩረታቸው ከስራ ውጭ የሆኑ «ሶሻል» እና በዓሉን የተመለከቱ ነገሮች ላይ ብቻ ማድረግ። «አታከሮች»ን ነቅቶ የመጠበቅ ባህልን የሚያቀዘቅዘው በመሆኑ የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠሩ እንደ አንድ ምክንያት ሊቆጠር ይችላል።» በማለት አብራርተዋል።
አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች አዲስ ዓመትን በመሳሰሉ የበዓላት ሰሞን ከወዳጅ ዘመድ ጋር የደስታ ጊዜ የሚያሳልፉበት እና ዘና የሚሉበት ጊዜ በመሆኑ ትኩረታቸው ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ በመሆኑ ከሚደርሰው የሳይበር ጥቃት በተጨማሪ፤ አቶ ብሩክ እንደሚሉት በበዓላት ወቅት ለተጠቃሚዎች በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው የሚላኩ የተለያዩ የበዓል መልዕክቶች ለሳይበር ጥቃት ያጋልጣሉ።
«ግለሰቦች እንግዲህ በዓል ሲመጣ በሞባይል ስልኮቻቸው ብዙ ዓይነት መልዕክቶች ይደርሷቸዋል። ከዚህ ጋር በተገናኘ በተለይ አዘውትረው በሚጠቀሙባቸው እንደ ቴሌግራም እና ዋትስ አፕ ያሉ ሜሴጅንግ አፕሊኬሽንስ /የመልዕክት መቀበያ መተግበሪያዎች / ላይ እንኳን ደስ ያላችሁ ፣እንኳን አደረሳችሁ፣ መልካም በዓል የሚሉ አይነት ስጦታ የመጣላቸው ሎተሪ የደረሳቸው ወይም ደግሞ ዕድል ለመሞከር የሚያበቁ የሚስመስሉ «ሊንክ» ያላቸው «አታችመንት» ያላቸው መልዕክቶች ይደርሷቸዋል።ጥቃት ፈጻሚዎች እንደዚህ አይነት ነገር የሚልኩት በጣም ብዙ ቁጥር ላላቸው ተጠቃሚዎች በመሆኑ፤ በበዓል በግለሰቦች ላይ የሚደርሰው የሳይበር ጥቃት በቁጥር ከፍ ያለ ነው የሚሆነው።»ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በበዓላት ወቅት ያልተፈጠሩ ፣ የተሳሳቱ ወይም የተጋነኑ እና ስሜት ኮርኳሪ መረጃዎችን እና ዜናዎችን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በማሰራጨት ዜናውን በጥልቀት ለማየት አባሪዎችን እና አገናኞችን/ ሊንኮችን/ ተጫኑ በሚል የተጠቃሚዎችን መረጃ መመንተፍም ሌላው ችግር መሆኑን ባለሙያው ገልፀዋል።
ከግለሰቦች በተጨማሪ መስሪያ ቤቶችም የበዓላት ወቅት የሳይበር ጥቃት ዒላማ ናቸው።በበዓት ወቅት ሰራተኞች ሥራዎቻቸውን በፍጥነት በመጨረስ በበዓሉ ለመታደም በሚጣደፉበት ጊዜ በመሆኑ፤ የሳይበር ደህንነት ጥንቃቄዎችን ችላ ሊሉ ወይም የሳይበር ጥቃት ምልክቶችን ልብ ላይሉ ይችላሉ።ጥናቶች እንደሚያሳዩት እነዚህ ስህተቶች የሳይበር ወንጀለኞች የተሳካ የሳይበር ጥቃት እንዲፈፅሙ በማድረግ 95% ለውሂብ ጥሰት ይዳርጋሉ።አቶ ብሩክ እንደሚሉት ደግሞ የበዓላት ወቅት ከፍተኛ የመፈጸም አቅም ያላቸው ሰራተኞች ጭምር እረፍት የሚወጡበት ጊዜ በመሆኑ የተለመደው የቁጥጥር ስራ ይላላ እና ስራ እስከማቆም የሚደርስ ጥቃት ሊፈፀም ይችላል።የተቋማቱ ሰራተኞች ወይም ሃላፊዎች የሚጠቀሟቸውን የኢሜል አድራሻዎች የሚመስሉ ኤሜሎችን በመጠቀም የሚፈፀም ማጭበርበርም /ኢሜል ፊሽንግ/ በበዓላት ቀን ጎልቶ የሚታይ ሌላው የሳይበር ጥቃት መሆኑን ባለሙያው አመልክተዋል።በኢሜይል የሚመጡ የመረጃ ስርቆቶችን እንዴት እንከላከል?
ስለሆነም በበዓላት ወቅት ተቋማት መረጃን ከጥቃት ለመጠበቅ ማድረግ አለባቸው ያሏቸውን የጥንቃቄ ርምጃዎች ጠቁመዋል።
«እንዲህ አይነት ነገሮች በዓል ሲሆን በድርጅቶች ላይ በብዛት የሚፈፀም ስለሆነ በድርጅ የሚገኙ ሰራተኞች የፊሽንግ ኢሜሎችን ከሌላ ጊዜ በበለጠ ጠንቅቀው መጠበቅ ይኖርባቸዋል።በተለያዩ መንገዶች በዓልን አስመስለው እንኳን አደረሳችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ የሚሉ በዓሉን የሚመስሉ መልዕክቶች ሲመጡ ክሊክ ባለማድረግ አታችመንቶችን «ዳዉን ሎድ» እንዳያደርጉ ለሰራተኞቻቸው የንቃት ማስጨበጫ ሊሰጡ ይገባል።»በማለት ገልፀዋል።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የተንቀሳቃሽ ስልክ አማካኝነት በበይነመረብ ባንክ መጠቀም/ሞባይል ባንኪንግ / እየጨመረ መምጣቱን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በየ ጊዜው የሚያወጣቸው መረጃዎች ያሳያሉ።ከዚህ ጋር ተያይዞ የበይነመረብ ግብይት እና ክፍያም እያደገ ነው።በዚያው መጠን በበይነመረብ የሚደረግ ማጭበርበርም እየጨመረ መሆኑ ይነገራል።ከዚህ ባሻገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ በቴሌግራም፣ በፌስቡክ፣ በዋትስአፕ እና ኢንስታግራምን በመሳሰሉ የማህበራዊ የትስስር ገጾች በተለይ በበዓላት ወቅት ምርቶችን ማስተዋወቅ እና በበይነመረብ ግብይት መፈፀምም እየተለመደ ነው።ይህ ሁኔታም በበዓል ወቅት ሸማቾችን ለመረጃ መንታፊዎች እና ለአጭበርባሪዎች ሊያጋልጥ ስለሚችል ፤ተጠቃሚዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል። መደረግ ካለባቸው ጥንቃቄዎች መካከልም ወደ መልዕክት መቀበያ ሳጥን የሚገቡ አጠራጣሪ አገናኞች ፣ አባሪዎች እና ሌሎች መልዕክቶችን ከመክፈት በፊት በጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ባለሙያው መክረዋል። የዘመኑ መተግበሪያዎችን መጫንም ሌላው የጥንቃቄ ርምጃ ነው።በበዓላት ወቅት የመረጃ ጠላፊዎች ኣጥፊ ተልዕኮ ያላቸዉ ሰነዶችን፣ ደረሰኝ፣ ስጦታ፣ ዝመና ወይም የትዕዛዝ መረጋገጫ በማስመሰል ሊልኩ ስለሚችሉ በኢ-ሜይል ለሚላኩ ቅጾች ወይም አገናኞች የይለፍ ቃልን ወይም ገንዘብ ነክ መረጃን ማስገባት አይመከርም፡፡በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚሰራጩ አጥፊ አገናኞችን የያዙ ዜናዎችን በችኮላ ከመክፈት ይልቅ ከታዓማኒ የዜና ምንጮች ቀድሞ ማረጋገጥ፣ የባለብዙ ደረጃ የማንነት ማረጋገጫ ዘዴዎችን መጠቀም ፤ ጠንካራ የይለፍ-ቃል መጠቀም እና ቶሎቶሎ መቀየር እና የዘመነ ሶፍትዌር መጠቀም ከመፍትሄዎቹ መካከል ናቸው።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሀይ ጫኔ
ታምራት ዲንሳ