የበዓል ገበያ በአሶሳ
ረቡዕ፣ ጳጉሜን 5 2017
በበኒ ሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማየአዲስ ዓመት ዋዜማ ገበያ ከዚህ ቀደም ከነበረው ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ የቁም እንስሳ ለሽያጭ ቀርቧል። ነዋሪዎች እንዳመለከቱት የበግ ዋጋ ከለፈው ዓመት ጋር ሲናጻጸር ዋጋ ጨምሯል፡፡ በሌሎች መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶች ላይ ደግሞ መጠነኛ ጭማሪዎች ቢኖሩም የጎላ የዋጋ ለውጥ አለመታየቱን አመልክተዋል፡፡ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ በበኩሉ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግ እየተቆጣጠረ መሆኑን አስታውቋል፡፡
‹‹በቁም እንስሳት ላይ ዋጋ ጭማሪ ተስተውሏል››
በመሰረታዊ የፍጆታ ምርቶች ዋጋ ላይ የጎላ ጭማሪ ባይኖርም አሁን ያለው ወቅታዊ ዋጋ ከፍተኛ መሆኑ በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ እንደሚያሳድር ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ ለበዓል ውሎ የሚረዱ ከዶሮ ጀምሮ ያሉ ግብአቶችን በመጥቀስ ወቅታዊ የገበያውን ሁኔታ ያነጋገርናቸው ሁለት ነዋሪዎች እንደሚከተው አብራርተዋል፡፡
‹‹ምክንያታዊ ያልሆነ ዋጋ የጨመሩ ግለሰቦቸ ተቀጥተዋል››
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ አሶሳ ከተማን ጨምሮ በሁሉም የክልሉ ከተሞች ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላትን ቁጥጥር እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡ የቢሮ ኃላፊ አቶ አሲር ኢብራሂም ህግ ወጥ ንገድና ምክንያታዊ ያልሆነ ዋጋ ጭማሪ የሚቆጣጠሩ ግብር ሀይል በስራ ላይ እንደሚገኝ የተናገሩ ሲሆን እስካሁን የታየ የጎላ የዋጋ ጭማሪ አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡
የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ 200 የሚደርሱ ያለአግባብ ዋጋ ጨምረዋል የተባሉ ግለሰቦችን መቅጣቱንም አመልክተዋል፡፡ በዛሬው የአሶሳ ገበያው ውሎም ከአጎራባች ክልሎችም በርካታ የቁም እንስሳት ለገበያ መቅረቡም ተገልጸዋል፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ሥለሺ