የኢትዮጵያ ኢንሳይደር መገናኛ ዘዴ መሥራችና ዋና አዘጋጅ እስር
ረቡዕ፣ ሰኔ 4 2017
በጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ የዋስትና መብት ላይ ፖሊስ ለሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ በማለቱ ለነገ ጠዋት ተቀጠረ። በጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ የዋስትና መብት ላይ ፖሊስ ይግባኝ በማለቱ ተጠርጣሪው ዛሬ ከቀትር በኋላ በአዲስ አበባ ሰበር ሰሚ ችሎት ቀርቧል። መዝገብ ከተከፈተ በኋላ «ዳኞች የሉም» በመባሉ ለነገ ጠዋት ቀጠሮ ተሰጥቷል ሲሉ የጋዜጠኛው ጠበቃ ቤተማርያም ዓለማየሁ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።
ከዚህ አስቀድሞ ዛሬ ረፋድ ጉዳዩ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ችሎት የታየ ሲሆን፣ ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ የሥር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በማጽናት የጋዜጠኛው የዋስትና መብት እንዲከበር የወሰነ ቢሆንም መርማሪ ፖሊስ ለሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ በማለቱ ጋዜጠኛው ከእሥር አልተፈታም። በጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ የዋስትና መብት ላይ የአዲስ አበባ ሰበር ሰሚ ችሎት ነገ ጠዋት እንደሚሰየም ለማወቅ ተችሏል። ጋዜጠኛው «ሀሰተኛ መረጃ ማሰራጨት» በሚል ተጠርጥሮ እሑድ ዕለት መታሠሩ ተገልጿል።
«ኢትዮጵያ ኢንሳይደር» የተባለው የበይነ መረብ የመገናኛ ዐውታር መሥራችና ዋና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ «ሀሰተኛ መረጃ ማሰራጨት» በሚል ተጠርጥሮ እሑድ ሰኔ 1 ቀን 2017 በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር መዋሉን ኢትዮጵያ ኢንሳይደርን የሚያስተዳድረው ሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ትናንት አስታውቋል። የጋዜጠኛው ጠበቃ ቤተማርያም ዓለማየሁ ዛሬ ለዶቼ ቬለ እንዳሉት ደንበኛቸው በተያዘበት ወቅት የእጅ ስልኩም ለምርመራ በሚል ተወስዶበታል።
ኢትዮጵያ ኢንሳይደርን እንደሚያስተዳድር የገለፀው ሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ተስፋለም ከተያዘ በኋላ የመጀመሪያውን ሌሊት መስቀል አደባባይ - እስጢፋኖስ ቤተ ክርስትያን አካባቢ ከሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ማደሩን፣ ሰኞ ዕለት ደግሞ ቄራ አካባቢ ወደሚገኝ የፖሊስ መምሪያ መዛወሩን ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ማክሰኞ ሰኔ 3 ቀን ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምድብ ችሎት ቀርቦ በ15,000 ብር ዋስትና እንዲፈታ ተወስኖም ነበር። ይሁንና መርማሪ ፖሊስ ይግባኝ በመጠየቁ ጋዜጠኛ ተስፋለም ዛሬ ረቡዕ ረፋድ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ችሎት ቀርቧል። ጠበቃ ቤተማርያም ዓለማየሁ የዛሬውን የይግባኝ ሰሚ ችሎት ውሎ ሲገልጹ፤
«ፖሊስ ያቀረበው የይግባኝ አቤቱታ የተጠርጣሪውን በእሥር መቆየት የግድ የሚል ባለመሆኑ በሥር ፍርድ ቤት የተሰጠው የዋስትና መብት እንዲፀና ወስኗል»። ነው ያሉት።
ይህ ከሆነ በኋላ ግን መርማሪ ፖሊስ ለሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ እንደሚል በቃል በመግለጹ ምክንያት ጋዜጠኛው ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት አመሻሽ ድረስ ከእሥር አለመለቀቁን ለማረጋገጥ ችለናል።
«ለጋዜጠኝነት ባለው ፅኑዕ ክብር እና ለሙያው ባለው ቁርጠኝነት የሚታወቀው ተስፋለም ዳግም በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር መዋሉ የሥራ ባልደረቦቹን፣ ወዳጆቹን እና ቤተሰቦቹን በእጅጉ አሳስቧል» ያለው ሐቅ ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ጋዜጠኛው «ተደጋጋሚ ችግሮች ቢገጥሙትም» ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ባለፉት ዓመታት «ነጻ እና ገለልተኛ የሆኑ፣ ከፍተኛ ሙያዊ ሥነ ምግባራቸውን የጠበቁ ዘገባዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል» በማለት «በአስቸኳይ ወደ ሥራው እንዲመለስ» ጥሪ አድርጓል።
ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (CPJ) «የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልድየስን ያለምንም ቅድመ ኹኔታ በአስቸኳይ ይፍቱ» ሲል ትናንት ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። «የተስፋለም ወልድየስ እሥር ፍርድ ቤት እንዲፈታ ትእዛዝ ከተላለፈ በኋላም ቢሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ለፍርድ ሂደቶች እና ለፕሬስ ነፃነት ያለውን ግድየለሽነት ያሳያል» ሲሉ የተቋሙ የአፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ ሙቶኪ ሙሞ መናገራቸው በወጣው መግልጫ ላይ ሰፍሯል።
ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ከዓመት በፊት ቢሮው ተሰብሮ በተፈጸመበት ስርቆት ልዩ ልዩ የሥራ ቁሳቁሶቹ እንደተወሰዱበትም ይታወቃል።
ሰሎሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ