1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ውዝግቦችኢትዮጵያ

የቡታጅራው ተቃውሞና ያስከተለው ጉዳት

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ሰኞ፣ መስከረም 19 2018

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምሥራቅ ጉራጌ ዞን በቡታጅራ የተከሰተውን አለመረጋጋት ለመፍታት ከህዝቡና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየመከረ እንደሚገኝ የከተማው አስተዳደር አስታወቀ። በከተማው አሁድ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ወጣቶች ከጸጥታ አስከባሪዎች ጋር ተጋጭተው ሦስት ሰዎች ሲሞቱ አራት መቁሰላቸውን እማኞች ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

ቡታጅራ
በቡታጅራ ዛሬ ሰኞ አንጻራዊ እንቅስቃሴ እንደሚስተዋል ለዶቼ ቬለ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ትናንት ተስተጓጉለው የነበሩት የንግድ እና የህዝብ ማመላለሻ አገልግሎቶች ወደ ቦታቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል ፡፡ ምስል፦ Shewangzaw Wegayehu/DW

የቡታጅራው ተቃውሞና ያስከተለው ጉዳት

This browser does not support the audio element.

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምሥራቅ ጉራጌ ዞን ቡታጅራ ከተማ ትናንት ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ወጣቶች ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር ተጋጭተዋል ፡፡ ወጣቶቹ ለተቃውሞ የወጡት “ የሲናኖ ሴራ” የተባለው ባህላዊ የሽምግልና ሥረዓት የባለቤትነት ጥያቄ ጋር በተያይዘ  መሆኑን የከተማው ነዋሪዎች ተናግረዋል ፡፡

የሽምግልና ሥረዓቱ የባለቤትነት ጥያቄ የተነሳው የቤተ ጉራጌ አካል በሆኑት የመስቃን እና የዶቢ ማህበረሰብን እንወክላለን በሚሉ ወጣቶች መካከል መሆኑን  ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል ፡፡

“ባህላችን ሊወሰድብን ነው “ የሚሉ የመስቃን ወጣቶች ሰሞኑን ወደ ቡታጅራ ከተማ አስተዳደር በመሄድ ጥያቄ ማቅረባቸውን ለዶቼ ቬለ የተናገሩ ሁለት የከተማይቱ ነዋሪዎች “ ነገር ግን በዶቢ በኩል ጥያቄው ምላሽና ውሳኔ ባላገኘበት ሁኔታ ትናንት አሁድ የሲናኖ ሤራ ለማድረግ ተሰባስበው ነበር፡፡ ይህም ተመሳሳይ ጥያቄ ባነሱት የመስቃን ወጣቶች ላይ ቁጣ እንዲቀሰቀስ በማድረግ ወደ ጎዳና ወጥተዋል  ፡፡ ወጣቶቹ በከተማዋ ጎዳናዎች በመውጣት መንገዶችን በመዝጋት ተቃውሞ አሰምተዋል ፡፡ ይህን   ተከትሎም በሥፍራው ከደረሱ የክልሉ አድማ በታኝ ፖሊስ አባላት ጋር ተጋጭተዋል “ ብለዋል ፡፡

በግጭቱ የደረሰው ጉዳት
 
ወጣቶቹ ትናንት እሁድ በከተማው ዋና ዋና መንገዶች በመውጣት ተቃውሞ ሲያሰሙ መዋላቸውን የአይን እማኖች ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል ፡፡ በከተማው የተኩስ  እሩምታ ይሰማ እንደነበር የጠቀሱት ነዋሪዎቹ የአምቡላንሶች ምልልስም በርቀት ሲሰሙ እንደነበር ጠቅሰዋል ፡፡

በቡታጅራ ወጣቶቹ የከተማዋን ጎዳናዎች በድንጋይ እና በጎማ መዝጋታቸውን ተከትሎ በሥፍራው ከደረሱ የክልሉ አድማ በታኝ ፖሊስ አባላት ጋር ተጋጭተዋል ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ በግጭቱም ሦስት ሰዎች ከፀጥታ አባላቱ በተተኮሰ ጥይት ሲገደሉ ሌሎች አራት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን እንደሚያውቁ ተናግረዋል ፡፡ምስል፦ Shewangzaw Wegayehu/DW

ወጣቶቹ የከተማዋን ጎዳናዎች በድንጋይ እና በጎማ መዝጋታቸውን ተከትሎ በሥፍራው ከደረሱ የክልሉ አድማ በታኝ ፖሊስ አባላት ጋር ተጋጭተዋል ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ በግጭቱም ሦስት ሰዎች ከፀጥታ አባላቱ በተተኮሰ ጥይት ሲገደሉ ሌሎች አራት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን እንደሚያውቁ ተናግረዋል ፡፡

ዶቼ ቬለ በተቃውሞ እና የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ የቡታጅራ ከተማ አስተዳደርንም ሆነ  የምሥራቅ ጉራጌ ዞን የሥራ ሃላፊዎችን ለማነጋገር ጥረት አድርጓል ፡፡ ነገር ግን ሃላፊዎቹ የሥልክ ጥሪ እና የጹሁፍ መልዕክት ባለመመለሳቸው ምላሻቸውን ማካተት አልተቻለም  ፡፡ ያም ሆኖ የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ባወጣው የጹሁፍ መግለጫ ትናንት እሁድ “ የተደራጁ “ ያላቸው ቡድኖች በከተማው በተወሰኑ መንደሮች ላይ ብጥብጥና ረብሻ ፈጽመዋል ብሏል ፡፡

የተነሳውን ረብሻ የፀጥታ ሀይሎች  ከሰላም ወዳዱ ማህበረሰብ ጋር በመሆን ማስቆም መቻሉን አስተዳደሩ በመግለጫው ጠቅሷል፡፡ ይሁን እንጂ በተፈጠረው አስነዋሪ ድርጊት የህይወትና የአካል  ጉዳት ደርሷል ያለው መስተዳድሩ ህይወታቸውን ላጡት ለቤተሰቦቻቸው እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን እንደሚመኝ ገልጿል፡፡ አሁን ላይ በከተማው የተከሰተውን አለመረጋጋት ለመፍታት ከህዝቡ እና  ከሚመለከታቸው አካላት ጋር  እየመከረ እንደሚገኝ መስተዳድሩ አመልክቷል ፡፡  

የከተማው አሁናዊ ሁኔታ

ዛሬ ሰኞ በከተማው አንጻራዊ እንቅስቃሴ እንደሚስተዋል ለዶቼ ቬለ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ትናንት ተስተጓጉለው የነበሩት የንግድ እና የህዝብ ማመላለሻ አገልግሎቶች ወደ ቦታቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል ፡፡ ቡታጅራ የገቡት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ከከተማው የተለያዩ የማህበረሰብ አካላት ጋር ዛሬ ውይይት መጀመራቸው ታውቋል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW