ቡታጅራ ፖሊስ 47 ተጠርጣሪዎችን አስሯል
ረቡዕ፣ መስከረም 21 2018
በቡታጅራ ከተማ ሁከትና ብጥብጥ አንስተዋል ያላቸውን 47 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የምሥራቅ ጉራጌ ዞን ፖሊስ አስታወቀ ፡፡ የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ሙሰማ ጀማል ዛሬ ለዶቼ ቬለ እንዳሉት ተጠርጣሪዎቹ በፖሊስ የተያዙት ባለፈው እሁድ በተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተሳትፈዋል ተብለው በመጠርጠራቸው ነው ፡፡ የሦስት ሰዎች ህይወት ካለፈበት ከእሁዱ ተቃውሞ በኋላ አሁን ላይ ከተማው ሙሉ በሙሉ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ መመለሱን የከተማው ነዋሪዎች ተናግረዋል ፡፡
የቡታጅራ ፖሊስ 47 ተጠርጣሪዎችን አስሯል
የምሥራቅ ጉራጌ ዞን ፖሊስእንዳስታወቀው በባለፈው አሁድ በቡታጅራ ከተማ የተካሄደውን ተቃውሞ ተከትሎ በተነሳው ሁከት እጃቸው አለበት በሚል የጠረጠራቸውን እየያዘ እንደሚገኝ አስታውቋል ፡፡ የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ሙሰማ ጀማል እንዳሉት ተጠርጣሪዎቹ የተያዙት በከተማው ተፈጥሮ በነበረው ሁከት በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ተሳትፈዋል በሚል በመጠርጠራቸው ነው ፡፡ ፖሊስ እስከአሁን 47 ተጠርጣሪዎችን በመያዝ ምርመራ መጀመሩን ነው ኢንስፔክተር ሙሰማ ለዶቼ ቬለ የገለፁት ፡፡
ከተቃውሞው ማግስት
ሦስት ሰዎች ከሞቱበት ሌሎች አራት ከቆሰሉበት ከባለፈው እሁድ ተቃውሞ በኋላ አሁን ላይ ከተማው ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ መመለሱን ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የከተማው ነዋሪዎች ተናግረዋል ፡፡ ተቃውሞውን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ሁከት የፌዴራል እና የክልል የፀጥታ አባላት ባደረጉት ጥረት የከፋ ጉዳት ሳይደርስ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ፖሊስ አስታውቋል ፡፡ አሁን ላይ በከተማው ተጥሎ የነበረው የሰዓት እላፊ ገደብ መሻሻሉንና ፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ መግባታቸውን የፖሊስ አዛዡ ጠቅሰዋል ፡፡
«በውይይት ይፈታል»
በቡታጅራ የሰው ህይወት የቀጠፈው ተቃውሞ መነሻ “ የሲናኖ ሴራ “ የተባለው ባህላዊ የሽምግልና ሥርዓት የባለቤትነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ መሆኑን የከተማው ነዋሪዎች ተናግረዋል ፡፡ የሽምግልና ሥርዓቱ የባለቤትነት ጥያቄ የተነሳው የቤተ ጉራጌ አካል በሆኑት የመስቃን እና የዶቢ ማህበረሰብን እንወክላለን በሚሉ ወጣቶች መካከል መሆኑን ነዋሪዎች አስረድተዋል ፡፡ አሁን ላይ አለመግባባቱን በውይይት ለመፍታት በየደረጃው ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ህዝባዊ ውይይቶች እየተካሄዱ እንደሚገኝ የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል ፡፡ ዶቼ ቬለ አስተያየታቸውን የጠየቃቸው የከተማው ነዋሪዎች አለመግባባቱን በዘላቂነት ለመፍታት ከፖለቲከኞች ውሳኔ ይልቅ ከሁለቱ ማህበረሰቦች የተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎች ከህዝቡ ጋር በመወያየት የደረሱበትን ቢያቀርቡ የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ነጋሽ መሐመድ