1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቡና አቅራቢዎችና ላኪዎች የጋራ ዉይይት

ማክሰኞ፣ ሰኔ 25 2016

የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የቡና አቅራቢዎች ማህበር ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ዳንኤል ሚጃኔ በሀዋሳው አውደ ርዕይ ከተሳተፉት መካከል አንዱ ናቸው ፡፡ አቶ ዳንኤል ይህን መሰሉ አውደርዕይ አምራቾች፣ አቅራቢዎች እና ላኪዎችን በቀጥታ እርስ በእርስ ለማገናኘት እንደሚረዳ ተናግረዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ቡና አቅራቢና ላኪዎች ተቀራርበዉ አለመሥራታቸዉ ክፍተት መፍጠሩ ተነግሯል
የኢትዮጵያ ቡና አቅራቢዎችና ላኪዎች ሐዋሳ ከተማ ዉስጥ ያደረጉት ዉይይትና አዉደ ርዕይምስል Shewangizawa Wegayoh/DW

የቡና አቅራቢዎችና ላኪዎች የጋራ ዉይይት

This browser does not support the audio element.

መንግሥት በቡና አምራችና ላኪዎች መካከል የሚታየውን የገበያ ሠንሰለት ክፍተት እንዲያስተካክል በዘርፉ የተሠማሩ ኩባንያዎች ጠየቁ ፡፡ ኩባንያዎቹ ለዶቼ ቬለ እንዳሉት አሁን ላይ አቅራቢና ላኪ የሚገናኙበት የገበያ ትሥሥር ባለመጠናከሩ አቅራቢዎች ከገበያ እየወጡ ይገኛሉ ብለዋል ፡፡ የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን የሥራ ሃላፊዎች በበኩላቸው በአቅራቢ እና ላኪዎች መካከል የገበያ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል ሥራዎችን በማከናወን ላይ አንደሚገኙ አስታውቀዋል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ ዝርዝር አለው

የቡናው ዘርፍ ተስፋና ተግዳሮት 

ኢትዮጵያ ለውጭ ከምታቀርባቸው ምርቶች ቡና ትልቁን ድርሻ እንደሚሸፍን ይነገራል ፡፡  መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አገሪቱ በተያዘው የበጀት ዓመት 10 ወራት ብቻ  ወደ ተለያዩ አገራት 210 ሺህ ቶን ቡና ልካለች ፡፡ ከዚህም የ1 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን  ባለፈው የግንቦት ወር ላይ ገልጾ ነበር ፡፡
የቡና ምርት ገቢ መጠኑን ለማሳደግና በአምራቾች፣ አቅራቢዎች እና ላኪዎች መካከል ያለውን የግብይት ሠንሠለት ለማሳለጥ ያስችላል የተባለ የቡናና ቅመማ ቅመም አውደ ርዕይ በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል ፡፡በአውደ ርዕዩ ላይ ከኦሮሚያ፣ ከሲዳማ፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ እና ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የተውጣጡ ከ300 በላይ የቡና አምራቾች፣ አቅራቢዎች እና ላኪዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ ፡፡
የአውደ ርዕዩ ፋይዳ

የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የቡና አቅራቢዎች ማህበር ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ዳንኤል ሚጃኔ በሀዋሳው አውደ ርዕይ ከተሳተፉት መካከል አንዱ ናቸው ፡፡ አቶ ዳንኤል ይህን መሰሉ አውደርዕይ አምራቾች፣ አቅራቢዎች እና ላኪዎችን በቀጥታ እርስ በእርስ ለማገናኘት እንደሚረዳ ተናግረዋል ፡፡
አውደ ርዕዩ የቡና አምራቾች፣ አቅራቢዎችና ላኪዎችን በዘርፉ የሚያነሷቸውን ችግሮች ለመፍታት ታስቦ መዘጋጀቱን የጠቀሱት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ደበላ “ በቡና ንግድ ሂደት ውስጥ አምራቾች ፣ አቅራቢና ላኪዎች መካከል ያለው ግንኙነት ብዙም የጠነከረ የሚባል አይነት አይደለም ፡፡ ይህ  አውደ ርዕይ እነዚህን አካላት ለማገናኘት ትልቅ ፋይዳ አለው “ ብለዋል።
የደላላ እጆች

ሐዋሳ በተደረገዉ ዉይይትና አዉደ ርዕይ የቡና አቅራቢና ላኪዎች ያጋጠማቸዉ ችግር ተወስeቷልምስል Shewangizawa Wegayoh/DW

አቶ ታምራት አለማየሁ በሀዋሳው አውደርዕይ ላይ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል አንዱ ናቸው ፡፡ ከጌዲዮ ዞን የኮቸሬ ወረዳ ቡና አቅራቢ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ታምራት በቡና አቅራቢዎችና ላኪዎች መካከል የሚስተዋለው የገበያ ክፍተት መፍትሄ አለማግኘቱ አሁንም አቅራቢዎችን  እየጎዳ ይገኛል ይላሉ  ፡፡
መንግሥት ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት በተጨማሪ በድርድር የሚካሄድ የትይዩ ግብይት / vertical integration / ተግባራዊ መድረጉ ለአቅራቢዎችና ላኪዎች የተሻለ አማራጭ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ታምራት “ ይሁንእንጂ ሁለቱን አካላት የሚያገናኝና የሚያቀራርብ መድረክ አብሮ አለመመቻቸቱ ለደላሎች ዕድል እየፈጠረ ይገኛል ፡፡ ይህም በግብይት ሂደት ውስጥ ትልቅ ሥጋትና ተግዳሮት ይዞ እየመጣ ነው  ፡፡ መንግሥት የገበያ ትሥሥሩን በማጠናከር ክፍተቱን የሚቀረፍበትን  ሥራ ሊያከናውን ይገባል “ ብለዋል ፡፡
የባለሥልጣኑ ጥረት

የቡና ምርት አቅራቢዎችን  ከላኪዎች ጋር ለማስተሳሰር ይህ መሰሉን አውደ ርዕይ ጨምሮ የተለያዩ የገበያ ዕድሎችን ለመፍጠር እየተሠራ እንደሚገኝ የገለጹት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ በበኩላቸው “ ላኪዎች ከዓለም አቀፍ ተቀባይ ድርጅቶች ጋር ጥሩ የሆነ ትሥሥር ቢኖራቸውም ምርቱን ለላኪዎቹ የሚያቀርቡ አቅራቢዎች ጋር ግን የገበያ ክፍተት ነበር ፡

ምስል Shewangizawa Wegayoh/DW

፡ አቅራቢዎች ለማንና እንዴት እንደሚሸጡ የተሟላ መረጃ የማግኘት ችግር አለ  ፡፡ ይህ አውደ ርዕይ አቅራቢዎች ከላኪዎች ጋር ለማስተሳሰር የተዘጋጀ  የመጀመሪያው መድረክ ነው ፡፡ በቀጣይ ይህን ጨምሮ የተለያዩ የግብይት ትሥሥር የሚፈጠርባቸው ሥራዎችን የምናከናውን ይሆናል “ ብለዋል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ነጋሽ መሐመድ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW