የቡድን ሀያ ጉባኤ እና አፍሪቃ
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 5 2009
የጀርመን የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ጌርድ ምዩለር ጥድፍያ ላይ ናቸው ። ሚኒስትሩ በርሊን በተካሄደው አፍሪቃ ውስጥ የሚሰሩ የጀርመን ኩባንያዎች ማህበር እና የቬስተርቬለ ተቋም ባዘጋጁት የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ላይ ያተኮረ ጉባኤ ላይ እንግዳ ነበሩ ። ምዩለር በጎርጎሮሳዊው 2017ን ጀርመን በአፍሪቃ ላይ ለማተኮር በማቀዷ ደስተኛ ናቸው ። በአፍሪቃ መዋዕለ ነዋያቸውን የሚያፈሱ የጀርመን ባለሀብቶች
« 2017 ለአፍሪቃ ትኩረት የሚሰጥበት ዓመት በመሆኑ ደስተኛ ነኝ ። አፍሪቃ በዓመቱ ትኩረት እንዲሰጣት ማድረጉ ስለተሳካልን ተደስቻለሁ ። እዚህ ሰፊ ድጋፍ አለን ። የፌደራል የገንዘብ ሚኒስትር ከኔ ጋር ናይሮቢ የነበሩት የፌደራል የኤኮኖሚ ሚኒስትር እንዲሁም አሁን ደግሞ አፍሪቃን ዋነ ኛ አጀንዳ ማድረግ የሚፈልጉት የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን ድጋፍ አግኝተናል ።»
ጀርመን ለአፍሪቃ ትኩረት እሰጣለሁ ባለችበት በ2017 በፕሬዝዳንትነት በምትመራው የቡድን 20 ጉባኤ ላይ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ማሰባሰብ ትፈልጋለች ። የተለያዩ የጀርመን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ይህን ማሳካት ያስችላሉ ያሏቸውን የተለያዩ ሀሳቦች አቅርበዋል አንዳንዶቹም እያዘጋጁ ነው ። የልማት ተራድኦ ሚኒስትሩ ምዩለር ለዚሁ ዓላማ ይረዳል ያሉትን «የአፍሪቃ የማርሻል እቅድ» የሚል ስያሜ የሰጡትን ሀሳብ አቅርበዋል ። የጀርመን የገንዘብ ሚኒስቴር ደግሞ ከሌሎቹ የቡድን ሀያ አባል ሀገራት ጋር «ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ» የሚል ስያሜ የሰጡትን ሀሳብ እያዳበረ ነው ። ባለፈው ታህሳስ የጀርመን የልማት እና የኤኮኖሚ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣በአፍሪቃ ተጨማሪ ንግድ እና የመዋዕለ ንፋይ ፍሰት ለማካሄድ የጋራ ስልት ያቀፈ ሰነድ አቅርበዋል ። በማይንዝ እና በላይፕሲሽ ዩኒቨርስቲዎች የአፍሪቃ ጉዳዮች አጥኚ ሄልሙት አሼ የጀርመን መንግሥት ለአፍሪቃ ትኩረት ለመስጠት የፈለገበትን አዲሱን እንቅስቃሴ አድንቀዋል ሆኖም መሟላት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ ይላሉ ።
«ሀሳቡ በጣም ትልቅ ነገር ነው።በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች መካከል የተሻለ ሊኖር የሚገባው ቅንጅት የተሻለ ሊሆን ይችል እንደነበረ የአደባባይ ሚስጥር ነው።ይህን አፍሪቃውያን አጋሮቻችንም አላጡትም »
አሼ እንደሚሉት ሚኒስትሮቹ አሁን ይህን እየተገነዘቡ መጥተዋል ። ሆኖም እስካሁን ከጀርመን ፌደራል መንግሥት በኩል ለቡድን ሀያ የሚቀርብ አንድ የተቀናጀ የጋራ ስልት ይጎድላል ። የማርሻል እቅድንም ሆነ ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ በተባሉት ሀሳቦች ላይም መልስ ያላገኙ ብዙ ጥያቄዎች አሉ ።ለምሳሌ ለሁለቱ ፕሮጀክቶች የሚያስፈልገው ገንዘብ እንዴት ሥራ ላይ የሚውለው የሚለew ግልጽ አይደለም ። የቡድን 20 የገንዘብ ሚኒስትሮች በቅርቡ ባካሄዱት ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ የወጡት መግለጫ ዓላማው ተለይተው በተመረጡ የአፍሪቃ ሀገራት የመዋዕለ ንዋይ ፍሰትን ይበልጥ ማስፋፋት መሆኑ ተገልጿል ። ይሁን እና የጀርመን ፌደራል መንግሥት ጊዜው እያለቀበት ነው ።የተቀናጀው ስልት እስከ መጪው በጋ መጠናቀቅ አለበት ። አፍሪቃ ላይ ያተኮረው የቡድን ሀያ ጉባኤ በርሊን ውስጥ በሰኔ ወር ነው የሚካሄደው ። የቡድን ሀያ አባል ሀገራት የመራህያነ መንግሥታት እና የርዕሳነ ብሔራት ጉባኤ ደግሞ ሐምሌ ውስጥ በሀምቡርግ ያካሄዳል ። ከዚያ በኋላ ደግሞ ጀርመን ውስጥ የምርጫ ዘመቻ ይጀመራል። ከመስከረሙ የጀርመን የምክር ቤት ምርጫ በኋላ ደግሞ ሪ,አዲስ መንግሥት ምሥረታ ድርድር ይጀመራል ። እናም የጀርመን ፌደራል መንግሥት በተፈላጊው ጊዜ አፍሪቃ ላይ ያተኮረ አንድ የጋራ ሀሳብ ይዞ መቅረብ መቻሉ እያጠያየቀ ነው። አሼ ይህ መሳካቱን ይጠራጠራሉ ሆኖም መንግሥት ሳናስበው አሳክቶ ሊያስደምምመንም ይችል ይሆናል ብለዋል ። ክሪስቶፍ ካነንጊሰር አፍሪቃ ውስጥ የሚሰሩ የጀርመን ኩባንያዎች ማህበር ሊቀ መንበር ደግሞ ወደ ተግባራዊው እንቅስቃሴ እንዲገባ ያሳስባሉ
«የጀርመን ፊደራል መንግሥት አፍሪቃን ዋነኛ አጀንዳው እንደሚያደርግ ማስታወቁ በራሱ ያሳደረው ተጽእኖ አለ ። አሁን መሆን ያለበት ጉዳዩ ከዐርዕስተ ዜናነት አልፎ ተጨባጭ ነገሮች የሚታዩበት እንዲሆን ማድረግ ነው ።»
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ