የቢቂላ ዕውቅናና ሽልማት በቶሮንቶ ካናዳ
ረቡዕ፣ መስከረም 14 2018
ዕውቁ ኢትዮጵያዊ የማራቶን ሯጭ አትሌት አበበ ቢቂላ ስም የተሰየመው፣ የቢቂላ ሽልማት ድርጅት የላቀ አስተዋጽኦ ላደረጉ ግለሰቦች ዕውቅና እና ሽልማት ሲሰጥ ዘንድሮ 11ኛ ዓመት ሆነው።
የአበበ ቢቂላ ማስታወሻ
ድርጅቱ፣ ለብዙ አትሌቶች መነሳሳትን በፈጠረው ስመ ጥሩ አትሌት አበበ ቢቂላ ስም ተሰይሞ፣ በሁሉም የሙያ ዘርፎች ከፍተኛ ድርሻ ላበረከቱ ግለሰቦች ዕውቅና እንደሚሰጥ የድርጅቱ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ በሃይሉ አጥናፉ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።
«አበበ ቢቂላ እንግዲህ፣ ለኢትዮጵያ አትሌቶች ፈር ቀዳጅ የሆነና በዓለም ኢትዮጵያ በሩጫው ስፖርት እንድትታወቅ ያደረገ ትልቅ ባለውለታ መሆኑን እናውቃለን። እና በተለያየም ዘርፍ እንደዚሁ ማድረግ ይቻላል በሚል ነው። በተለይ እውቅና የሚገባቸውን ብዙ ጥሩ ነገር የሠሩትን ሰዎች በሕይወት እያሉ ዕውቅና መስጠት፣ እንደዚሁም ደግሞ ወጣቶችን ከእነዚህ ሰዎች መማር እንዲችሉ የተቋቋመ ነው።»
በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችም ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።
የ2025 ተሸላሚዎች
ከዘንድሮ የቢቂላ ሽልማት ድርጅት ተሸላሚዎች መኻከል፣ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን፣ ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው፣ በጤና ዘርፍ ባበረከቱት የላቀ አስተዋጾ ደግሞ ዶክተር ደብረ ወርቅ ዘውዴ፣ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ የልብ ህክምና አገልግሎት የሚሰጡት ባለትዳሮች፣ ዶክተር ኦቢሲኔት መርዕድ እና ባለቤታቸው ዶክተር ተስፋዬ ተሊላ እንዲሁም በካናዳ የሞፈር ቡና ባለቤት አቶ ሚልክያስ ተፈራ ይገኙበታል።
ሰሞኑን የተካሄደው፣ የሽልማት መርኀ ግብሩ አጠቃላይ ገጽታ ምን ይመስል እንደነበር፣ አቶ በሃይሉ እንደሚከተለው ተናግረዋል።
«በአጠቃላይ የነበረው ሁኔታ ፣በጣም መንፈስን የሚያነሳሳ፣ ውስጥን የሚነካ፣ መቻልን፣ የምናስበው ነገር ማድረግ እንደምንችል እና ብዙ ሰዎች ደግሞ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ምሳሌ የሆኑ ሰዎች በእኛ ውስጥ እንዳሉ የሚያሳይ እና አብዛኛውን ሰው ያነቃቁ ንግግሮች ነበሩ»
የንግድ ልቀት ተሸላሚው
ከዘንድሮው ተሸላሚዎች መኻከል፣ ዶቼ ቬለ ያነጋግራቸው፣ አቶ ሚልክያስ ተፈራ፣ ካናዳ የሚገኘው፣ የሞፈር ቡና ድርጅት መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ናቸው።
ለሽልማት ለመብቃታቸው፣ ጉልዕ ሆኖ የተጠቀሰው ጉዳይ ምንድነው በማለት ላቀረብንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ «'ልዩ የሚያደርገን ዋናው የራሳችንን ቡና ነው የምንጠቀመው፣ ሁለተኛ የግንባታችን ሁኔታ በጣም በተለየ ሁኔታ አገነባብ ዘዴ ነው ያደረግነው፤ ውስጡ በጣም ያምራል። በደንብ ጊዜ ወስደን ነው የምንገነባው ማለት ነው፣ እና የኢትዮጵያንም መልክ ይዞ እንዲሄድ ነው የምናደርገው። ድባቡ ያው ኢትዮጵያዊነትን ስለሚያመለክት ነው።»
ወደ ካናዳ የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራ የሚቀጠሩበት ድርጅታቸው ሞፈር ቡና፣የአዲስ መጪዎች ተስፋ ተብሎ እንደሚጠራ አቶ ሚልክያስ ገልጸውናል።
ሞፈር ቡናን በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ በመላው ዓለም ተደራሽነቱን የማስፋት ውጥን እንዳለው የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ ለደንበኞች የሚሰጡት አገልግልግሎትም ድርጅታቸው በልዩነት እንዲታይ እንዳደረገው አመልክተዋል።
ታሪኩ ኃይሉ
ሸዋዬ ለገሠ
ታምራት ዲንሳ