የባህል ተወዋዡ ቢንያም እሸቱ
እሑድ፣ መጋቢት 11 2014
የባሕላዊ ውዝዋዜ ባለሙያው ብንያም እሸቱ ወይም በቅጽል ስሙ የደስታ ልጅ እያሉ የጠሩታል። ይህን ስም ያገኘዉ ከዚህ ዓለም በሞት የተለቸዉ የእስክስታ ንግስት በመባል ትታወቅ የነበረዉ የደስታ ገብሬ ልጅ በመሆኑ ነዉ። ብንያም እሸቱ ማለትም የደስታ ልጅ ዛሬ የእናቱን ሙያ ወርሶ በባሕላዊ ውዝዋዜና በሌሎች የጥበብ ዘርፎች ላይ ተሰማርቶ ይገኛል። ወደ ዋናው የሱ ስራዎች ከመግባታችን በፊት ስለእናቱ ደስታ ገብሬ ባጭሩ ያለንን እናጋራችሁ። `` እናቴ ደስታ ገብሬ ለሙዚቃ በተለይም ደግሞ ለባሕላዊ ጭፈራ የነበራት ፍቅር ማንም የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያውቀው ነው። የባሕላዊ ውዝዋዜን አስተምራለች። እኔም ከሷጋ ሆኜ አስተምሬያለሁ። እኔ ከሷ ብዙ ነገሮችን ተምሬያለሁ። ሙያዋ አክባሪና ጥሩ እናት ነበረች``
የባሕላዊ ውዝዋዜ ባለሙያው ቢንያም እሸቱ ወደ ሙያው የገባው በእናቱ እግር በመተካት እንደሆነ አጫውቶናል። `` እኛ ቤት በሁሉም ነገር ሙዚቃ አለ። እኔ ከልጅነቴ ጀምሮ እሷን እያየሁ ነው ያደኩት። ልጅ ሆኜ ብሔራዊ ትያትር እገባ ነበር። እናቴ ለሙያዋ ያላት ፍቅር ከልጅነቴ ጀምሮ እያየሁ ስላደኩ በሷ እግር ተተክቼ ነው ወደ ሙያው የገባሁት። በባሕላዊ ውዝዋዜ በአገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ጭፈራዎችን እጫውታለሁ።``
የእናቱን ፈለግ በመከተል ወደ ውዝዋዜ ሙያ የገባው ቢንያም እሸቱ በሙያው እየቆየ ሲሄድ የማጠናከሪያ ስልጠናዎችን እንደወሰደ ነግሮናል። በመሆኑም በተለያዩ ትያትር ቤቶችና ከአገር ውጭም ጭምር ባህላዊ ውዝዋዜዎችን ማቅረቡን ነግሮናል።
ከበሮ ሃይማኖታዊና ባሕላዊ ሥነ-ስርአቶች ከምናደምቅባቸው ባሕላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች አንዱ ነው። ቢንያም የባሕላዊ ከበሮም ተጫዋች እንደሆነም አጫውቶናል።
ለሙዚቃ የሚሆኑ ግጥሞችን መጻፍ ሌላው ቢንያም እሽቱ የሚሞካክረው የጥበብ ዘርፍ ነው። ውዝዋዜና የከበሮ ምት እየሰራ ጎን ለጎን ለጥቂቶች ይሁን እንጂ የሙዚቃ ግጥሞችን ጽፎ ለአልበም አብቅቷል። ``ውዝዋዜም እየሰራሁ ግጥም እሞክርነበር። እውነት ለመናገር በዚህ መስክ ብዙ አልሰራሁም። እንደው ይነገር ከተባለ ግን ከጸጋው ተክሉ ጋ የመጀሪያ ስራዬ ለድምጻዊት ሰላማዊት ተስፋዬ ``ምላሽ`` የሚል ግጥም የሰራሁት እኔ ነበርኩ። ከዛ የጃኪ ጎሲ ``ቀዳማዊት`` የሚል ነበር። ለግጥምና ዜማ ደራሲ እንዲሁም ዘፋኝ ለሆነው ለጸጋው ተክሉ `` ማን ልበል`` የሚል ዘፈን ግጥሙ የኔ ነው።``
ሙሉ ዝግጅቱን የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
አዜብ ታደሰ