1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ፍላጎት

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 3 2016

ጠቅላይ ሚኒስትሩ "አብረን መኖር ካሰብን ፣ ሰላም ካሰብን ፣ ሚዛኑን በጠበቀ መንገድ እየተጋራን መኖር አለብን እንጂ ያ ካልሆነ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ያጣላል" ሲሉ በጉዳዩ ላይ ገፋ ተደርጎ የተያዘ የተጠቃሚነት ፍላጎት መኖሩን አመልክተዋል።

ቀይ ባህር
ዶልፊን የተባሉ የዓሳ ዝርያዎች በቀይባሕርምስል W.Poelzer/WILDLIFE/picture alliance

በቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ፍላጎት

This browser does not support the audio element.

የባሕር በር ጉዳይ

የበለፀጉ ታላላቅ ሀገራት የንግድ እና ወታደራዊ ጥቅሞቻቸው ማስጠበቂያ ማዕከል ባደረጉት ቀይ ባሕር እና አካባቢው ኢትዮጵያ ፍትሐዊ የአለም አቀፍ ንግድ መከወኛ የውኃ በር የማግኘት መብቷ እንዲረጋገጥ ጉዳዩ የሕዝብ መወያያ አጀንዳ እንዲሆን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጠየቁ።
በብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባደረጉት ዘለግ ያለ ንግግር "የቀይ ባሕር ጉዳይ በደንብ ንግግር ያስፈልገዋል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "ቀይ ባሕር እና ዓባይ የኢትዮጵያን ሁኔታ የሚበይኑ፣ ከኢትዮጵያ የተቆራኙ፣ ለኢትዮጵያ እድገትና ጥፋት መሠረት ናቸው" ብለዋል።
ከቀይ ባሕር ለመገልገል ወይም ለመጠቀም አካሄዱ "በተቻለ መጠን በሰላማዊ መንገድ" መሆኑን ያብራሩት ዐቢይ አሕመድ ፌደሬሽን፣ ኮንፌደሬሽን ወይም የመሬት ልውውጥ ወይም ከግዙፍ የኢትዮጵያ ተቋማት ለኤርትራድርሻ መስጠት አማራጭ የውኃ በር ማግኛ ሥልቶች መሆናቸውን ዘርዝረዋል።

በጉዳዩ ላይ ሀሳባቸውን ያጋሩ አንድ የአለምአቀፍ ሕግ እና ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ የኢትዮጵያ የኤርትራ የባሕር በሮችን የመጠየቅ መብት በሕግ የተገደበ ቢሆንም "በሰጥቶ መቀበል መርህ የኤርትራን ጥቅም በማክበር ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥቅም እንድታስከብር የሚያስችል እድል አለ" ብለዋል።
ይህንን ግን የሚገኘው የወደብ ጥቅም ተመጣጣኝነት ፣ መተማምን እና በሁለቱ ሀገራት መንግሥታት ደረጃ ያንን የማድረግ ፍላጎት አለ ወይ? የሚለው አስቸጋሪ ሊያደርገው ይችላል ሲሉ ገልፀዋል።

"የባሕር በርለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው"

"የቀይ ባሕር ጉዳይ በደንብ ንግግር ያስፈልገዋል። ግጭት ግን አንፈልግም። የባሕር በር ያስፈልጋል አያስፈልግም ፣ ለምን ያስፈልጋል? ትርፍ ጥያቄ ነው ወይ ? አሁናዊ ጥያቄ ነው? እነዚህን ጉዳዮች በደንብ ማየት ያስፍልጋል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የጎረቤት ሀገራት ሁሉ በዓባይ ውኃ ላይ እየተመለከታቸው የቀይ ባሕርም ጉዳይ ይመልከታቸዋል፣ ነገር ግን ኢትዮጵያ የቀይ ባሕርን ጉዳይ በሕዝብ እንደራሴዎች ደረጃ እንኳን መወያየት እንደ ነውር እናስባለን " በማለት "ለመነጋገር እንዴት እናፍራለን" ሲሉ ጠይቀዋል።
ይህ ጉዳይ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ቢያጋጨንስ በሚል ሥጋትና ጥያቄ መኖሩንና ነገሩ ለውይይት አለመብቃቱን ያብራሩት  ዐቢይ በከፍተኛ ቁጥር እያሻቀበ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ "የመልክዓ ምድር እሥረኛ" ሆኖ መኖር አይችልም ሲሉ ለጉዳዩ የተሰጠውን ትኩረት አመልክተዋል።
"በዓባይ ጉዳይ ማንም ፈርቶን አያውቅም" በማለት ዓባይ ላይ ሌሎች ደፍረው የመወያየታቸውን ያህል ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ጉዳይ ደፍራ ልትወያይበት የተገባ መሆኑንም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ለሁሉም ጎረቤቶቿ ሀገራት ውኃ ሰጪ የመሆኗን ያህል ፣ ከየትኛውም ጎረቤት ሀገር ውኃ የማታገኝ መሆኗንም ዘለግ ባለው ንግግራቸው ጠቅሰዋል።
"አብረን መኖር ካሰብን ፣ ሰላም ካሰብን ፣ ሚዛኑን በጠበቀ መንገድ እየተጋራን መኖር አለብን እንጂ ያ ካልሆነ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ያጣላል" ሲሉም በጉዳዩ ላይ ገፋ ተደርጎ የተያዘ የተጠቃሚነት ፍላጎት መኖሩን አመልክተዋል።"ይሄ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው" ሲሉም ተደምጠዋል።

የአለምአቀፍ ሕግና ዲፕሎማሲ ተንታኝ አስተያየት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያደረጉት ማብራሪያ ከኤርትራ መሪዎች ጋር ከተነጋገሩና ከተስማሙ በኋላ የተደረገ ስለመሆን አለምሆኑ የተገለፀ ነገር የለም። ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ፎረም የተባለውና ስምንት ሀገራትን ያቀፈው ስብስብ ውስጥ አባል እንድትሆን ጠይቃ በጎ ምላሽ አላገኘችም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚህ የውኃ በር የማግኘት ጉዳይ ላይ ከተለያዩ ጋዜጠኞችና ባለሃብቶች ጋር በቤተ መንግሥት ስለመነጋገራቸው በአለምአቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጭምር ተዘግቧል። ወደ ስልጣን በመጡ ሰሞኑም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ሆነው በተለያዩ መድረኮች ሀሳቡን አንስተዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ሀሳባቸውን የሰጡን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ተንታኝ "ሌሎች ትልልቅ ሀገሮች በአከባቢው ያለውን ሁሉን አቀፍ ፋይዳ ተመልክተው ስምሪት የሰጡበት" አካባቢ መሆኑን ጠቅሰው  ኢትዮጵያም ይህንን ለአለም አቀፍ ንግድ የሚሆን የባሕር  የማግኘት መብትን ብታነሳ ተገቢ መሆኑን ጠቅሰዋል። ከሕግ አንፃር ግን ሌላ አተያይ ያለው መሆኑን እኒሁ ባለሙያ ጠቅሰዋል። "በእርግጥም ታሪካዊ አመጣጡ የምጽዋ እና የአሰብ ወደብ የኢትዮጵያ አካል የነበረ ቢሆንም ላለፉት ሠላሳ አመታት ወደን፣ ፈቅደን ፣ ተስማምተን ሰጥተናል" 

ግብጾች ቀይ ባህርን ለቱሪዝም ዘርፍ በከፍተኛ ሁኔታ ይጠቀሙበታልምስል Givaga/Zoonar/picture alliance


አማራጭ የባሕር በር ማግኛ ስልቶች ምንድን ናቸው ?

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ኢትዮጵያን የከበቡየባሕር በሮችን በመጋራት፣ በኢንቨስትመንት፣ በረጂም ዓመት ኪራይ ይሁን በሌላ አማራጭ መጠቀም የሚቻልበት እድል ተዳሷል። የባሕር በር አለመኖር ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሊኖራት የሚችል ያሉትን የፖለቲካ ተጽዕኖም ይገድባል ሲሉ ተደምጠዋል።
የሕግና ዲፕሎማሲ ተንታኙ እንደሚሉት መተማመን፣ ተመጣጣኝ ተጠቃሚነት እና በሁለቱ መንግሥታት በኩል ያለ ዝግጁነት ይህንን ፍላጎት በማሳካትም ይሁን ባለማሳካት ረገድ ትልቅ ጥያቄ ነው። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የባህር ኃይልን አስፈላጊነት ማመን እንደሚያስፈልግ፣ ኢትዮጵያ አሰብን ልትወስድ ነው የሚለውን ትርክት ማረም እንደሚገባ አብራርተዋል። የኢትዮጵያ ዋና ስትራቴጂዎች ሰላም እና አንድነት ፣ የሕግ የበላይነት እና እርቀ ሰላም መሆናቸውንም በዚሁ ሰፊ ማብራሪያቸው አትተዋል።
ጎረቤት ሀገራት አንድ ሀገር መሆን ቢችሉ የሚል ፍላጎት እንዳላቸውም በንግግራቸው ተስተውሏል። በአካባቢው ያለው የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ ፖለቲካ በኢትዮጵያ በኩል የተዘነጋ መሆኑን በመጥቀስም የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ ቢያንስ የውይይት ትኩረት እንዲሆን ጥሪ አድርገዋል።

ሰሎሞን ሙጬ

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW