1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የባቡር ፕሮጀክቶች ፈተና 

ረቡዕ፣ ጥቅምት 5 2012

ኢትዮጵያ ካለችብት የኢኮኖሚ ጥገኝነት ተላቃ አንድ እርምጃ ወደ ፊት እንድትራመድ ታስቦ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ትግበራ ባስገባቻቸው ሜጋ ፕሮጀክቶቿ ወደ ሁለት ጫፍ በተለጠጡ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተይዛለች።

Addi Abeba Straßenbahn
ምስል DW/Y. Gebreegziabher

የባቡር ሥራ ከመጀመሩ አደጋ መከሰቱ ጥራቱን አጠያያቂ ያደርገዋል

This browser does not support the audio element.

በአንድ በኩል ግዙፍ መዋእለ ንዋይ የሚጠይቁ  በአንድ ጊዜ በርካታ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ስትነሳ የኢኮኖሚ አቅሟን ታሳቢ ያላደረገ እና በጥልቅ ጥናት ላይ ያልተመሰረተ መሆኑ ሲነገር ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ፤ ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ  እና የሌሎች ባለድርሻ አካላትን ጥምረት በሚሹ ፕሮጀክቶች ላይ የማማከርና የመምራት ልምድ ባልነበረበት ሁኔታ ውስጥ መጀመሩ ከፍተኛ የሃገር ሀብት እንዲባክንና ሌሎች ኢኮኖሚውን የሚገዳደሩ የጎንዮሽ ችግሮችን ለማስተናገድ ተገዳለች። ተገንብቶ ለመጠናቀቅ የእጥፍ ያህል ጊዜ እየወሰደ የሚገኘውና በግንባታ ሂደቱ ከሀገር ውስጥ የፋይናንስ ስጋት ፣ ከውጭ ግብፅ ለማድረስ የምትሞክረው ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ጫና የተጋረጠበት የህዳሴ ግድብን ጨምሮ የስኳር ፋብሪካዎች እና የባቡር መስመር ዝርጋታዎች ያሉበትን ሁኔታ እንደ አንድ ማሳያ ማንሳት ይቻላል።
ለ2007 የምርጫ ዋዜማ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦላቸው ወደ ግንባታ ከገቡት ውስጥ የአዋሽ -ወልድያ - ሃራ ገበያ የባቡር መስመር ግንባታን በተመለከተ የመንግሥት አጠቃላይ እቅድ እና በጊዜ ሂደት በግንባታው አፈጻጸም ላይ የተፈጠረውን ችግር በንጽጽር ሲታይ የመንግሥትን የማስፈጸም አቅም በምን ደረጃ እንዳለ አመላካች ስለመሆኑ የኢኮኖሚ ባለሞያ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ወንዳፈራሁ ሙሉጌታ ገልፀዋል።

ምስል picture-alliance/Photoshot/Xinhua/S. Ruibo

 ኢትዮጵያ የምትገነባቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታው የሚወስደው ጊዜ፣ በጀትና በተፈላጊ የጥራት ደረጃ የተገደቡ አለመሆናቸው ተጨማሪ ዋጋ እንድትከፍል አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ እንዳስገባት የሚናገሩት ደግሞ የግንባታ ባለሞያው አቶ ሚካኤል ሽፈራሁ ናቸው። የአዋሽ ወልድያ ሃራ ገበያ የባቡር መስመር ምንም እንኳ ግንባታው ወደ መጠናቀቁ ቢቃረብም የኤሌክትሪክ አቅርቦት ባለማግኘቱ ሥራ ሊጀምር አልቻለም። በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ተገዝተው ለግንባታው ሥራ ላይ የዋሉ ንብረቶች ለዝርፊያ መጋለጣቸውም ከሰሞንኛው አነጋጋሪ ጉዳዮች አንደኛው ክስተት ሆኗል። በግንባታ ሂደት በመሰል ሁኔታ የሚፈጠሩ ችግሮች ፕሮጀክቶችን በአግባቡ ካለመምራት የሚመጡ እንደሆነ ነው አቶ ሚካኤል የሚያስረዱት። መንግሥት ያለቅድመ ዝግጅት የተለጠጠ የግዙፍ ፕሮጀክቶች የግንባታ እቅድ ይዞ ወደ ትግበራ መግባቱ አሁን ለተፈጠሩ ችግሮች ዋንኛው ምክንያት ሆኗልም ባይ ናቸው። ሜጋ ፕሮጀክቶችን ለጀማሪዎች ሰጥተው እየገነቡ እንዲማሩበት መደረጉም ለማረም የሚያስቸግር ስህተት ነበር ሲሉም ሃሳባቸውን ያጋራሉ።


ሜቴክ የህዳሴውን ግድብ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራ እየተማረ እንዲሠራ መደራጉ በጥራት እና የጊዜው ሰሌዳ ላይ በፈጠረው መስተጓጎል መንግሥት ለጣልያኑ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ሚሊዮን ዶላሮችን ካሳ እንዲከፍል ተገዷል። ከድሬዳዋ ጂቡቲ የሚወስደው የባቡር መስመር ሥራ ከመጀመሩ አደጋ ማስተናገዱም ፕሮጀክቶቹ ከፍተኛ የግንባታ ጥራት ችግር ውስጥ እንዳሉ የሚያመላክት ነው በማለት የኢኮኖሚ ባለሞያው ረዳት ፕሮፌሰር ወንድይፍራው ሙሉጌታ ይገልጻሉ። ኢትዮጵያ በእነዚሁ ከአቅም በላይ ተለጥጠው ተጀመሩ በተባሉ ሜጋ ፕሮጀክቶቿ በአግባቡ ባለመከናወናቸው ብቻ በቀጣይ ለተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ዓለም አቀፍ ብድርና ድጋፍ የማግኘቷ ነገር አጠያያቂ ሊሆን እንደሚችልም ረዳት ፕሮፌሰር ወንድይፍራው ስጋታቸውን ይገልጻሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገነቡ ፕሮጀክቶች ከመነሻቸው የህዝቡን የመልማት ፍላጎት መሠረት አድርገው አለመነሳታቸውም ፕሮጀክቶቹ በሚገነቡባቸው አካባቢዎች የባለቤትነት ስሜት እንዳይኖር አድርጓል፤ ለብልሽት እና ስርቆትም ዳርጓል የሚል እምነት አላቸው። በሌላው በኩል እነዚህ ሁሉ ነገሮች ፕሮጀክቶቹ በሚገጥማቸው የቴክኒክ ችግር በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ በሚያሳድሩት አሉታዊ ተጽጥኖ ልክ መንግሥት ለወስናቸው ፖለቲካዊ ውሳኔዎች የበለጠ ኪሳራ ይዞ መጥቷል ባይ ናቸው አቶ ሚካኤል።

ምስል DW/Mekonne


አገሪቱ አሁን ለገጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት መፍትሄ ለማግኘት የወጭ ምርቶቿን በብዛትም ሆነ በጥራት ማሳደግ ይጠበቅባታል። በዚያው ልክ የወጭ ምርቱን ለቅሸባ የዳረገውን የመጓጓዣ ዘርፍን  መፈተሽም እንዲሁ። የወጪም ሆነ ገቢ ምርቶችን ደህንነት በማስጠበቅ እና ኢኮኖሚውን ጤናማ በማድረግ ረገድ  የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር መስመር ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ይጠበቃል። ሆኖም የባቡር መስመሩን ለማስተዳደር ኮንትራት ለወሰደው የቻይና ኩባንያ የሚከፈለው ክፍያ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከድጥ ወደ ማጡ እንዳያደርገው ተሰግቷል።
የኢትዮ ጅቡቲ የምድር ባቡር ድርጅት እንደጎርጎርሳዊያኑ አቆጣጠር በ2018 ለዚሁ የቻይና ኩባንያ 60 ሚሊዮን ዶላር በውሉ መሠረት ከፍሎታል። በዚሁ ዓመት ከባቡሩ የተገኘው ገቢ ግን  718 ሚሊዮን ብር ብቻ ነበር። ይህ ሁኔታ ደግሞ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት በተመሳሳይ መልኩ ሊቀጥል እንደሚችል ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።
የኢቲዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ሰርካ እንደሚሉት ከሆነ ድርጅቱ ይህን ያህል የውጭ ምንዛሪ ለማውጣት የተገደደው የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ በማተኮሩ ነው። የኢትዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር መዳረሻ ጣቢያ በተለይ በአዲስ አበባ ያለውን ተገልጋይ ታሳቢ አለማድረጉ ይታወቃል። አቶ ጥላሁን እንደሚሉትም ዋና አላማው ጂቡቲ ያለውን ጭነት ማንሳት ታሳቢ ያደረገ ስለነበር ነው።  መንገደኞችን በተመለከተ ምንም እንኳ አዋጭ ባይሆንም ከመሃል አዲስ አበባ ወደ ባቡር ጣቢያዎች ለማድረስ ሌሎች የመጓጓዣ አማራጮችን ለመጠቀም ማቀዳቸውንም አመልክተዋል። 
በጊዜ፣ በበጀት እና በጥራት እንከን የገጠማቸው የኢትዮጵያ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ከፈተናቸው ወጥተው ኢኮኖሚዋን ይታደጉ ይሆን?

ምስል Getty Images/AFP/M. Medina

ዝርዝር መሰናዶውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ታምራት ዲንሳ

ሸዋዬ ለገሠ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW