1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የቤት ረዳቶችን/ሠራተኞችን መብት የሚታደገው ደንብ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 16 2017

በኢትዮጵያ የቤት ረዳትነት / ሠራተኝነት / ተሰማርተው የሚገኙ ዜጎች በሀገሪቱ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ መሠረት እንዲስተናገዱ ለማድረግ የሚያስችል ደንብ በቅርቡ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጀምር የፌደራል የሥራ አና ከህሎት ሚንስቴር አስታወቀ።

Äthiopien Hawassa | Meaza Regassa und Endale Teklehawariat
ምስል፦ Shewangizaw Wogayahu/DW

የቤት ረዳቶችን/ሠራተኞችን መብት

This browser does not support the audio element.

የቤት ረዳቶችን/ሠራተኞችን መብት የሚታደገው ደንብ  

በኢትዮጵያ የቤት ረዳትነት / ሠራተኝነት / ተሰማርተው የሚገኙ ዜጎች በሀገሪቱ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ መሠረት እንዲስተናገዱ ለማድረግ የሚያስችል ደንብ በቅርቡ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጀምር የፌደራል የሥራ አና ከህሎት ሚንስቴር አስታወቀ። በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ የሚንስቴሩ የሥራ ሃላፊዎች ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩት የደንቡ ተግባራዊ መሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ የቤት አጋዦችን የሰብአዊ እና የሥራ ላይ መብቶችን ለማስጠበቅ ያስችላል። በዘርፉ በተሠማሩ ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ የሰብአዊ እና የሥራ ላይ መብት ጥሰቶች እየተባባሱ መምጣታቸውን የጠቀሱት የቤት አጋዦች ማህበር ሃላፊዎች በበኩላቸው የመመሪያው ተግባራዊ  መሆን የቤት ውስጥ ጥቃቶችን ለመቀነስ እንደሚረዳ ተናግረዋል።

የቤት ረዳቶችን መብት የሚታደገው ደንብ  

ወይዘሮ መዓዛ ረገሳ ለዓመታት በቤት ረዳትነት /ሠራተኝነት / ተሰማርተው መቆየታቸውን ይናገራሉ። አሁን ከሦስት ዓመታት በፊት የተቋቋመውን የሲዳማ ክልል የቤት ረዳቶች ማህበር በሊቀመንበርነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ። በቤት ሠራተኝነት የሥራ ዘርፍ መልካም አሠሪዎች ያሉትን ያህል ከድብደባ እስከ ደሞዝ መከልከል ጥቃቶችን የሚያደርሱ እንዳሉም ነው ሊቀመንበሯ የጠቀሱት። ጥቃቱ በቤት ውስጥ የሚፈጸም በመሆኑ መንግሥትም ሆነ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ጋር የመድረስ ዕድሉ ጠባብ እንደሆነ ያመለከቱት ወይዘሮ መዓዛ «በተለይ ያለዕረፍት ረጅም ሰዓት ማሠራት፣ ምግብና መደበኛ የመኝታ ቦታ አለማግኘት ከሚደርሱ በደሎችና የመብት ጥሰቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው » ብለዋል።

ንቡ መብቶችን ምን ያህል ያስከበራል ?

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በኢትዮጵያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በሀገር ውስጥ የቤት ረዳትነት የሥራ መስክ ተሰማርተው ይገኛሉ። ይሁንእንጂ የሥራ መስኩ እንደብዙዎች መተዳደሪያነቱ እስካሁን ተገቢውን ትኩረት ያላገኘ ፣ ሕጋዊ ሂደቶችንም ያልተላበሰ መሆኑ ነው የሚነገረው። በዘርፉ ተግዳሮት እና መፍትሄዎች ላይ በሀዋሳ ከተማ የመከሩት ባለድርሻ አካላት የቤት ረዳትነት ሥራ በሀገር አቀፉ የሠራተኞች አዋጅ እንዲካተት በሚያስችላቸው ደንብ ላይ ተወያይተዋል።

ቤይሩት በቤት ሥራ የተሰማራች ኢትዮጵያዊትፎቶ ከማኅደርምስል፦ AP

በያዝነው ዓመት ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው ደንብ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የቤት አጋዦችን የሰብአዊና የሥራ ላይ መብቶቻቸውን ለማስጠበቅ እንደሚያስችል የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሦስትዮሽ ግንኙነት ማስተባበሪያ ሃላፊ አቶ እንዳልክ ተክለሐዋሪያት ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አዋጅ 1156 የግል አገልግሎት ቅጥር የሥራ ሁኔታ ደንብ በሚንስትሮች ምክር ቤት አማካኝነት እንደሚያወጣ የጠቀሱት አቶ እንዳልክ «አሁን ለዚህ አጋዥ የሆነውን ረቂቅ ደንብ አዘጋጅተን እያወያየን እንገኛለን። የደንቡ ተግባራዊ መሆን ሙያው የቤት ረዳትነት ሥራ እንደሌሎቹ የሙያ ዘርፎች እንዲከበር ያደርጋል። የመብት ጥሰቶችንም ለመከላከል አጋዥ ይሆናል» ብለዋል። ግንዛቤ እንደተግዳሮት

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የባለድርሻ ተቋማት ተወካዮች በበኩላቸው በዘርፉ በተሰማሩ ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ የሰብአዊ እና የሥራ ላይ መብት ጥሰቶች እየተባባሱ መምጣታቸውን ተናግረዋል። የመመሪያው ተግባራዊ  መሆን የቤት ውስጥ ጥቃቶችን ለመቀነስ እንደሚረዳ በኢትዮጵያ ሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር የሀዋሳ ማዕከል የሕግ ባለሙያ አቶ መሠረት በቀለ ጠቅሰዋል።

የግንዛቤ ክፍቶች ባሉበት ማኅበረሰብ ውስጥ የሥራ መብቶችን ምን ያህል በሕግ አግባብ ብቻ ማስከበር ያስችላችኋል በሚል በዶቼ ቬለ የተጠየቁት በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሦስትዮሽ ግንኙነት ማስተባበሪያ ሃላፊው አቶ እንዳልክ «ከሕግ ክፍተት ቀጥሎ ያለው ችግር የግንዛቤ መሆኑን እናውቃለን። ደንቡን ወደ ሥራ ከማስገባት ጎን ለጎን የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚያስችል ሥራዎች እያከናወንን እንገኛለን። በተለይም በየክልሎች የተቋቋሙ የቤት ረዳቶች ማህበራትን ጨምሮ የመንግሥት ተቋማት እና የተለያዩ የሙያ ማህበራት አመራሮችና ባለሙያዎችን ጋር የውውይት መድረኮችን በማዘጋጀት ግንዛቤ እየፈጠርን እንገኛለን» ብለዋል።

ሲ-ቪ-ኤም በተባለ ዓለም አቀፍ በጎ አድራጊ ድርጅት ድጋፍ በተዘጋጀው በዚሁ ውይይት ላይ ከፌዴራል፣ ከሲዳማ ክልል የተወከሉ የመንግሥት ተቋማትና ከሙያ ማህበራት የተውጣጡ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ሸዋዬ ለገሠ

ፀሐይ ጫኔ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW