የቤኔዲክት 16ኛ ስንብትና የቀብር ሥርዓት ዝግጅት
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 25 2015
በ95 ዓመታቸው በጎርጎሪዮሱ አዲስ ዓመት ዋዜማ ቅዳሜ ዕለት ያረፉት የሮማ ካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን የቀድሞው ርእሰ-ሊቃነ-ጳጳሳት ቤኔዲክት 16ኛን በሺህዎች የሚቆጠሩ ምእመናን ቫቲካን ቅዱስ ጴጥሮስ ውስጥ እየተሰናበቱ ነው። የቤኔዲክት 16ኛ የቀብር ሥርዓት ሐሙስ፤ ታኅሣሥ ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚፈጸም ነው የተነገረው። ትናንት ከ70 ሺህ በላይ ዛሬ ደግሞ 85 ሺህ ሰው የቤኔዲክት 16ኛ አስክሬንን ዕያየ ለመሰናበት ቫቲካን ውስጥ ወደሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል መጥቶ ነበር። ደቡብ ምሥራቅ ጀርመን ባቫሪያ ግዛት ውስጥ ሲወለዱ ዮሴፍ ራትስሲንገር የሚል ስም የተሰጣቸው ቤኔዲክት 16ኛ የቀብር ስርዓትየፊታችን ሐሙስ እንደሚከናወን ተገልጧል።
ቤኔዲክት 16ኛ የካቶሊክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት የሆኑት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2005 ነበር። በ2013 ደግሞ በጤና እክል የተነሳ ከርእሰ ሊቃነ ጳጳሳትነት ራሳቸውን አግልለዋል። ያን በማድረግም በካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ታሪክ ከ600 ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያው ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነዋል። ቤኔዲክት 16ኛ በሕይወት እያሉም ነበር ሌላ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት የተመረጠው። ይህ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን የርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ምሥጢራዊ ምርጫ ልማድ ላይ ምን ያስከተለው ለውጥ አለ?
ቤኔዲክት 16ኛ በቤተክርስቲያኒቱ የመሪነት ዘመናቸው ለቤተ ክርስቲያኒቱ እድገት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ጉልህ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ። በዚያው መጠን ደግሞ በሳቸው ዘመን ቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ የወሲብ ቅሌት ክሶች ውዝግብ ውስጥ ገብታ ለረዥም ጊዜ የመነጋገሪያ ርእስም ሆኖ ነበር። እሳቸውን የተኩት የአሁኑ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ጉዳዮች ላይም ጣልቃ ይገቡ ነበር ይባላል። ቤኔዲክት 16ኛ በይበልጥ የሚታወሱት በምንድን ነው?
ለጥያቄዎቹ መልሶቹን በድምፅ ከተያያዘው ቃለ መጠይቅ ማድመጥ ይቻላል።
ተኽለ እዝጊ ገብረ ኢየሱስ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ