1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቤንዚን እጥረት በአማራ ክልል ያስከተለው ኢኮኖሚያዊ ጫና

ዓርብ፣ መስከረም 10 2017

አንድ ሊትር ቤንዚን በቤንዚን ማደያ 83 ብር እየተሸጠ በሕገ-ወጥ መንገድ ተመሳሳይ መጠን ያለውን ቤንዚን ከ150 ብር በላይ ገዝቶ መስራት ለባለንብረቶቹ አትራፊ እንዳልሆነ ተናግራል፡፡ የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ፋንታው ፈጠነ ለቤንዚን እጥረት የክልሉ የፀጥታ እጦት በነዳጅ ጫኞች ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩን ዘርዝረዋል፡፡

Äthiopien Bahir Dar 2024 | Thema Treibstoffknappheit
ምስል Aleminew Mekonnen/DW

በአማራ ክልል ያለው የነዳጅ እጥረትና ህገወጥነት  በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ እንደሆነ ነዋሪዎችና አሽከርካሪዎች ተናገሩ፣ አንዳንድ የባለሶስት እግር አሽከርካሪዎች በቤንዚን እጥረት ምክንያት ስራቸውን አቁመዋል፣ የንግድና ገበያ ልማት ቢሮ በበኩሉ ህገወጥነት መኖሩን አምኖ ለነዳጅ እጥረት መፈጠር የተለያዩ ችግሮች መኖራቸውን አልክቷል፡፡

በአማራ ክልል ባለፈው አንድ ዓመት በተፈጠረው ሰፋ ያለ የነዳጅ እጥረት በሥራቸው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደፈጠረባቸው አንዳንድ የክልሉ  ነዋሪዎችና አሽከርካሪዎች ይናገራሉ፣ በተለይ በቤንዚን የሚንቀሳቀሱ ተሸከርካሪዎች በግብዓቱ እጥረት ምክንያት ከገበያ ውጪ እንደሆኑ አንድ የባህር ዳር ከተማ አሽከርካሪ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡

የቤንዚን እጥረት በአሽከርካሪዎች ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ

“ቤንዚን በጣም አሳሳቢ ሆኗል፣ እኔ በቤንዚን እጥረት ምክንያት ሥራ ካቆምኩ አንድ ወር አስቆጥሪየሁ፡፡” እንደ አስተያየት ሰጪው ቤንዚን ከማደያ እያገኙ አይደለም፣ ይልቁንም ከማደያ ከሚሸጥበት በእፍ በህገው መንገድ እንደሚገዙ አመልክተዋል፤ ያም ሆኖ ግን አትራፊ እንዳልሆኑ ነው የተናገሩት፡፡ “ሥራ ፈትቶ ከቤት ከመዋል ይሻላል” ከሚል ስራውን እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

ሌላ የባለሶስት እግር አሽከርካሪ ወጣትም ሁለቱን ሊትር ቤንዚን እሰከ 350 ብር እንደሚገዛ ጠቁሞ ይህ በነዳጅ ማደያ ከ160 ብር አይበልጥም ነበር ብሏል ። በመሆኑም ስራ ላለማቆም ስንል ነው የምንሰራው ሲል አስተያየት ሰጥቷል፡፡የነዳጅ እጥረትና የጥቁር ገበያ መስፋፋት በአማራ ክልል

ስለቤንዚን እጥረት የነዋሪዎች አስተያየት

የጎንደር ከተማ ነዋሪ በሰጡን አስተያየት የቤንዚን እጥረት የተፈጠረው በህገጥ መንገድ ከማደያዎች ስለሚሸጥ ነው፣ ይህ ደግሞ በትራንስፖርት ታሪፍ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል ነው ያሉት፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪው የነዳጅ እጥረት በከተማው ማደያዎች የለም፣ ይልቁንም ከፍተኛ የሆነ ህገወጥነት እንዳለ ነው ያስረዱት፡፡ በሌሊት በበርሚል እየተቀዳ ወደ ሕገ-ወጥ ንግድ እንደሚሄድ ሁሉም እንደሚያውቅ ገልጠዋል፡፡ “የነዳጅ እጥረት ቢኖር ኖሮ እንዴት ማደያ ላይ የለም ተብሎ በየቦታው በሀይላንድ ላስቲክ ያለከልካይ በይፋ በሕገ-ወጥ መንገድ በከፍተኛ ዋጋ ይሸጣል?’ ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ፋንታው ፈጠን ምስል Aleminew Mekonnen/DW

ሌለ ነዋሪ ደግሞ ብዙ አሽከርካሪዎች በርካታ ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ በመሆኑ በህገው መንገድ ከሚሸጥ ነዳጅ ገዝቶ ለመስራት ከባድ በመሆኑ መንግስት ጠንካራ ክትትል ሊያደርግ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡የኤሌክትሪክ እጦትና የነዳጅ እጥረት በሰሜን ወሎ ዞን

አንድ ሊትር ቤንዚን ማደያ ላይ 83 ብር እየተሸጠ፣ በህገወጥ መንገድ ተመሳሳይ መጠን ያለውን ቤንዚን ከ150 ብር በላይ ገዝቶ መስራት ለባለንብረቶቹ አትራፊ እንዳልሆነ ተናግራል፡፡ ባሶስት እግር አሽከርካሪዎች በስራቸው እስከ 6 ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ ናቸው ፤ እና እንዴት ነው በዚህ ገበያ አትርፈው ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ? ሲሉ ነው እኚህ አስተያየት ሰጪም የጠየቁት፡፡

የንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስተያየት

የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ፋንታው ፈጠነ  ለቤንዚን እጥረት አንዱ ምክንያት በክልሉ ያለው የፀጥታ እጦት በነዳጅ ጫኞች ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩን አመልክተው ሌሎች ምክንያት ዘርዝረዋል፡፡

ነዳጅ ሲሞላምስል Aleminew Mekonnen/DW

ማደያዎች የመጣላቸውን ነዳጅ (በዋናነት ቤንዚን)ን ለታለመለት ዓላማ ያለማዋልና የቁጥጥር ማነስ እንደሚታይ ገልጠዋል፤ ከሽያጭ ስርዓት ውጪ የቤንዚን ሸጥ መኖሩንም አስረድተዋል፡፡ ነዳጅ መሸጥ ያለበት በቴክኖሎጂ ግብይት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ፋንታው ይህ ባለመሆኑ ለነዳጅ ብክነትና እጥረት ምክንያት ሆኗል ነው ያሉት፡፡ የመጣውን ነዳጅ በተገቢው መንገድ አለማስተዳደርም ሌላው ምክንያት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡የነዳጅ እጥረት በኦሮሚያ ክልል

ከነዳጅ ማደያ ውጪ ነዳጅ መሸጥ ትክክል እንዳልሆነ የተናገሩት ምክትል ኃላፊው፣ በሕገ-ወጥ ገበያ የሚገኘው ነዳጅ ምንጩ ማደየዎች መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ የዚህ ምክንያቱ በየደረጃው ያለው የሚመለከተው አካል የክትትልና የቁጥጥር ስራው ደካማ መሆን ነው ብለዋል፡፡ ችግሮቹ ቀድመው የተለዩ በመሆናቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ችግሮቹን ለመፍታት እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በአማራ ክልል የሚገቡ የነዳጅ ዓይነቶች ፣ናፍጣ፣ ቤንዚንና ነጭ ጋዝ መሆናቸውን ያብራሩት አቶ ፋንታው አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በክልሉ እያጋጠመ ያለው የቤንዚን ነዳጅ ነው፡፡

 

ዓለምነው መኮንን

ኂሩት መለሰ

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW