የቤንዚን ዋጋ መናር በኬንያ የቀሰቀሰው የተቃውሞና የመንግሥት ምላሽ
ቅዳሜ፣ ግንቦት 15 2018
ኬንያውያን ባለፉት ጥቂት ዓመታት መንግሥታቸው ከሸቀጦች ዋጋ እና ከግብር ጋር በተገናኘ ሊያደርግ የሞከራቸውን ጭማሪዎች በተቃውሞ እንቅስቃሴያቸው ሲያስቀለብሱ የመጀመሪያቸው አይደለም። ፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር በመደራደር ተቀብለው በሀገራቸው ተግባራዊ ለማድረግ የሞከሩት የፋይናንስ ማሻሻያ የሚያስከትለውን መዘዝ ባጤኑ ዜጎቻቸው ውድቅት መደረጉን ተከትሎ ከሽፏል። ሩቶም በአደባባይ ወጥተው ከሥልጣን ይውረዱ እያለ ያወገዛቸውን ሕዝብ ይቅርታ ጠይቀዋል።
ሰሞኑንም በነዳጅ ላይ የተደረገው ጭማሪ የሕዝብ መጓጓዣ አገልግሎቶችን ሥራ ሲያስቆም ሕዝቡም በዚህ የኑሮ ውድነት እጥፍ እንድከፍል ተገድጃለው በማለት ተቃውሞውን ሲገልጽ ተስተውሏል። ከአምስት ቀናት በፊት በዋና ከተማዋ ናይሮቢ የሚገኙ ዋና ዋና መንገዶች ባዶ በመሆናቸው በርካታ የሕዝብ መጓጓዣዎችን የሚጠቀሙ ወገኖች በያሉበት መንቀሳቀስ ሳይችሉ ቀርተዋል፤ ንግድ ቤቶችና ትምህርት ቤቶችም ተዘግተው ተማሪዎችም ከቤት እንዲውሉ ተገደዋል።
የዋጋ ጭማሪውን የተቃወሙት የሚቃጠሉ መከላከያዎችን ተክለው መንገዶችን በመዝጋት ዋና ከተማዋ ጭር እንድትል ማድረጋቸውን ተከትሎም የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኪፕቹምባ ሙርኮመን 348 ሰዎች መታሰራቸውን በወቅቱ ተናግረዋል። እንደ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገለጻም፣ ይህን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን ተከትሎ በተደረገው አገር አቀፍ የትራንስፖርት አድማ ምክንያት በተነሳው ተቃውሞ የአራት ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል። በርካቶችም ተጎድተዋል።
ኬንያእንደ አብዛኞቹ የአፍሪቃ ሃገራት ከባሕረ ሰላጤው አካባቢ ሃገራት በሚገባ የነዳጅ ዘይት ላይ ጥገኛ ናት። የተጠቀሰው አካባቢ ደግሞ በኢራን ፤ እስራኤል እና አሜሪካ ጦርነት ምክንያት የመርከቦች መተላለፊያ መንስመር የሆነው የሆርሙዝ ሰርጥ የፍልሚያ ሜዳ በመሆኑ ሃገራት እንደወትሮው የሚሸምቱትን የነዳጅ ዘይት ማጓጓዝ ተስኗቸዋል። በዚህ መሀል ነው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የኬንያ መንግሥት የነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ ማድረጉን ይፋ ያደረገው።
የነዳጅ ዋጋ መጨመሩ እንደተሰማ ኬንያውያን ማታቱ የሚሏቸው አብዛኛው ዜጋ የሚጠቀምባቸው የሕዝብ መጓጓዣዎች ሳይቀሩ ሥራ አቆሙ፤ ተሳፋሪዎች ለወትሮው 100 እና 150 የኬንያ ሽልንግ የሚከፍሉባቸው ርቀቶች 300 ሽልንግ ገቡ። በዚህ ሕዝቡ መቆጣቱን ለሮይተርስ የተናገረው ከተጠቃሚዎች አንዱ «ኑሮ ከአቅማችን በላይ ሆኗል፤ ፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ የትም ሆነው ይህን የሚሰሙ ከሆነ እባክዎ የነዳጅ ዋጋ ይቀንሱልን» ሲል ብሶቱን መግለጹ ተጠቅሷል።
የኬንያ ባለሥልጣናት በነዳጅ ላይ ያደረጉት የ20 በመቶ ጭማሪ ከዚህ በፊት ተደርጎ የማይታወቅ ከፍተኛው እንደሆነ ነው የተገለጸው። ያ ደግሞ ከኑሮ ውድነት ጋ የሚታገለውን የኬንያ ሕዝብ ቁጣ ቀሰቀሰ። የመጓጓዣ አገልግሎት ሰጪዎች ነዳጅም አንገዛም አንንቀሳቀስምም አሉ። ተጽዕኖውን በየቤቱ ብቻ ሳይሆን ወደ የመንግሥት ተቋማትም ዘለቀ። አዝማሚያውን የተገነዘበው የኬንያ መንግሥት መፍትሄ ለማፈላለግ ከመጓጓዣ አገልግሎት ሰጪዎች ጋር ተቀምጦ ተነጋገረ።
የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ኪፑቹምባ ሙርኮሜን፤ «በመንግሥት እና በባለድርሻ አካላት መካከል በከፍተኛ ደረጃ ድርድር እንደሚያስፈልግ፣ እነዚህ ድርድሮችም በሚቀጥለው ሳምንት ውስጥ ከአሁን እስከ መጪው ማክሰኞ፣ ባለው ጊዜ ውስጥ እንዲካሄድ፤ በዚህ ጊዜም አድማው ለአንድ ሳምንት እንዲቆም፣ በመንግስት እና በባለድርሻ አካላት መካከልም ለሚደረገው ምክክር እና ድርድር ፋታ እንዲሰጥ ለማድረግ ተስማምተዋል።»
የኢነርጂ እና የነዳጅ ሚኒስትሩ ኦፒዮ ዋንዳይ በበኩላቸው፤ ከድርድሩ በኋላ በአንድ ሊትር ናፍጣ ላይ የአስር የኬንያ ሽልንግ ቅናሽ መደረጉን ይህ ደግሞ የኬንያ መንግሥት የሸማቾችን ችግር በንቃት እየተከታተለና እርማት እየወሰደ መሆኑን እንደሚያሳይ ተናገሩ። በእርግጥም ከጭማሪው የተወሰነ ቅናሽ አደረገ፤ አድማውም ለጊዜው ቆመ።
ትናንት ዓርብ ዕለት ደግሞ የኬንያ የሕዝብ መጓጓዣ ኦፕሬተሮች ፤ መንግሥት ከናፍጣ ዋጋ ላይ ከአራት በመቶ በላይ መቀነሱን ካሳወቀ በኋላ በሚቀጥለው ሳምንት የታቀደውን አድማ አቋርጠዋል። ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ትናንት ይህንኑ የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ ለሕዝባቸው በቴሌቪዥን ወጥተው ተናግረዋል።
"በሚቀጥለው የዋጋ አወጣጥ ዑደት፣ የሚጨምረውን ዋጋ ለማረጋጋት እና ለተጠቃሚዎች ተጨማሪ እፎይታ ለመስጠት በሰኔ እና ሐምሌ ወር በሚኖረው ዑደት የናፍጣን ዋጋ በአስር ሽልንግ እንቀንሳለን። በሦስተኛ ደረጃ፣ በመንግሥት-ለመንግሥት የአቅርቦት ማዕቀፍ አማካኝነት፣ በዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለት መስተጓጎል ቢኖርም በመላ አገሪቱ ያልተቋረጠ የነዳጅ አቅርቦት እንዲኖር፤ የተረጋገጠ የነዳጅ አቅርቦት እንደሚኖረን ማድረግ ችለናል።»
ሩቶ እንዳሉት መንግሥታቸው በሚያዝያ እና እና ሰኔ መካከል የነዳጅ ዋጋን ለመቀነስ ቢያንስ 28.1 ቢሊዮን የኬንያሽልንግ አውጥቷል። ታዛቢዎች እንደሚሉት ተጨማሪው ቅነሳ በኬንያ መንግሥት ፋይናንስ ላይ ሌላ ጉዳት ማስከተሉ አይቀርም። ምንም እንኳን አዲሱ ጭማሪ እንደሚነሳ ሩቶ ቢናገሩም አሶሲየትድ ፕረስ እንደሚለው ኬንያ ውስጥ ያለው የነዳጅ ዋጋ ቀድሞውኑ ከሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት ይበልጥ ውድ ነው።
በመጪው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2027 ነሐሴ ወር ዳግም ለምርጫ ውድድር ለመቅረብ ያቀዱት ሩቶ ሥልጣን ላይ በቆዩባቸው ዓመታት የኑሮ ውድነትን ባባሱ እርምጃዎቻቸው ተደጋጋሚ ተቃውሞዎችን አስተናግደዋል። በጎርጎሪዮሳዊው 2024 መላ ሀገሪቱን በተቃውሞ ሲነሳባቸው የ2.7 ቢሊየን ዶላር የግብር ጭማሪ እቅዳቸውን ለመሰረዝ ተገደዋል።
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ