የብልፅግና ፓርቲ መግለጫ፤ የሌሎች ፓርቲዎች አስተያየት
ሰኞ፣ ነሐሴ 5 2017
የብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ "ለግድያ የሚፈላለጉ" ያላቸው በስም ያልጠቀሳቸው ኃይሎች" ኢትዮጵያን በሑከት ውስጥ የማቆየት፤ የሕዝብ ቅሬታዎችን ለዐመጽ የመጠቀም፣ ብሶት ቀስቃሽ አጀንዳዎችን የማራገብ" ያላቸውን ተግባራትን ለመፈጸም መጣመራቸውን ጠቅሶ ነቅፏል። ገዢው ፓርቲ "ይፈልጉት የነበረው" የተራዘመ ጦርነት በፕሪቶርያ ዘላቂ ግጭት የማቆም ስምምነት "የተጨናገፈባቸው" ያላቸው አካላት "ሌሎች ስልቶችን ወደ መሞከር ገብተዋል" ሲልም ከሷል።
ብልጽግና ፓርቲ ስላወጣው መግለጫ አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ ሦስት የፖለቲካ ድርጅቶች መግለጫው "ሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ተጨባጭ ኹኔታ በአግባቡ ያልዳሰሰ እና ችግሮችንም የማይፈታ" መሆኑን ገልፀዋል። የወጣው መግለጫ "የሀገር ውስጥ ችግሮች በሀቀኛ ድርድር እና ንግግር እንደሚፈቱ አጽንዖት ሰጥቶ አላመላከተም" ሲሉም አስታውቀዋል። ሰሎሞን ሙጬ ከአዲስ አበባ ዝርዝሩን ልኮልናል።
የገዢው ብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤት አባላት ከሐምሌ 30 እስከ ነሐሴ 02 ቀን 2017 ዓ.ም ካደረጉት መደበኛ ስብሰባ በኋላ የወጣው መግለጫ፣ የፕሪቶሪያ ዘላቂ ግጭት የማቆም ስምምነት በስም ያልተጠቀሱ አካላትን ይፈልጉት የነበረ የተባለን ጦርነት እንዳጨናገፈባቸው ይጠቅሳል።
የፓርቲው መግለጫ እነዚህ ኃይላት "ጽንፈኞችን በመጠቀም" የመንግሥትን ኃይልና የሕዝብን አንድነት ለመከፋፈል ጥረት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል ሲልም ያትታል።
"በየአካባቢው ግጭትን ማበራከት እና በዲጂታል ሚዲያ መንግሥትን ማሳጣት" ጠላቶቼ ያላቸው አካላት የተጠቀሙት ስልት መሆኑን ያመለከተው ብልጽግና ፓርቲ "ኢትዮጵያን የማዳከም ዕድላቸው ግን እየጠበበ ነው" ብሏል።
በዚህ መግለጫ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ተጠይቀው ፈቃደኛ ከሆኑ ፓርቲዎች መካከል የሕብር ኢትዮጵያ ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ አንዱ ናቸው።
"በተጨባጭ ከምድር ላይ ካለው ጋር የማይሄድ እና አሁንም በተለመደው መንገድ ተጨባጩን ኹኔታ በክህደት እና ለህገሪቱ ችግሮች ተጨባጭ መፍትሔ የሚሆን አቅጣጫ ያላመላከተ.... ወቅታዊ የሀገሪቱን ኹኔታ ያላገናዘበ ነው።"
"ሰላማዊ የፖለቲካ ዕድሎችን" አሟጥጦ እንደሚጠቀም የገለፀው ብልጽግና ፓርቲ "ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች አንሠራርተዋል" ሲል ደምድሟል። ለኦሮሞ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ኮንግረው ኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ግን ይህ አልተዋጠላቸውም።
"የስቀመጡት ነገር የሀገሪቱን ችግር ይፈታል የሚል ግምት የለንም። ሰላም የጠፋበት፣ ሁሉም አካባቢ ችግር ያለበት፣ ለመዘዋወር እና ምንም ለመፈጸም የሚያስቸግሩ ሁናቴዎች አሉ።"
ገዢው ፓርቲ እንዳለው "ኢትዮጵያን በሑከት ውስጥ የማቆየት፣ የሕዝብ ቅሬታዎችን ለዐመጽ የመጠቀም፤ ብሶት ቀስቃሽ አጀንዳዎችን የማራገብ፣ ሚዲያዎችን የሑከት መቀስቀሻ መሣሪያ የማድረግ፣ በውጭ ምንዛሬ እና በሸቀጦች በኩል የኢኮኖሚ አሻጥርን መሥራት" ጠላቶቼ ያላቸው ኃይሎች ሊፈጽሙት የተዘጋጁት ጉዳይ መሆኑን ጠቅሷል። ይህም በመሆኑ "ሰላማዊ አማራጮችን በሁሉም አቅጣጫ ለመሞከርና በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ለሚወስኑ ታጣቂዎች አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ፣ ሕግ ለማስከበር" መዘጋጀቱን አስታውቋል። የኢሶዴፓ ሊቀመንበር ዶክተር ራሔል ባፌ ግን ይህን ይጠራጠራሉ።
"በጎ ጎኑን አከናውነናል የሚለው በጣም ከፍ ብሏል ግን ማሳያዎች፣ ጥናቶች የሉም [መግለጫው ላይ]። ነገር ግን ሀገር ውስጥ ያለውን ነገር ከታጣቂዎችም፣ ሀገር ውስጥ ካሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ያለውን የሀገር ውስጡን ሁኔታ በሀቀኛ ድርድር እንደሚፈታ አጽንዖት ሰጥተው አላስቀመጡም።"
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሰሞኑን ይፋ ባደረገው የአንድ ዓመት ሪፖርቱ "በኢትዮጵያ ዘላቂ ፖለቲካዊ እና መዋቅራዊ መፍትሔ የሚያስፈልጋቸው ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈፀማቸውን ገልጿል።
የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ -ኮከስ "ጦርነት ያብቃ፣ ሠላምና ዲሞክራሲ ይስፈን" የሚሉ ጥሪዎችን በማስተላለፍ ሀገር አጣብቂኝ ውስጥ መሆኗን ሰሞኑን ገልጿል።
ከሳምንታት በፊት ቢሾፍቱ ውስጥ ውይይት ያደረጉ ከ50 በላይ ፓርቲዎች ደግሞ "በሀገራችን ላይ ያለው አሁናዊ የፖለቲካ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል" በማለት "መንግሥት በትጥቅ ግጭት ውስጥ ካሉ ኃይላት ጋር ወደ ድርድር እንዲገባ" መጠየቃቸው ይታወሳል።
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ