1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የብሩህ ትውልድ መስራቾቹ ጥንድ ሳይንቲስቶች

ረቡዕ፣ መጋቢት 6 2015

ዶክተር ብርሀኑ ቡልቻ በአሜሪካው የጠፈር ምርምር ናሳ ፤ ጨረቃ ላይ ውሃ የሚፈልግ መሳሪያ የሰሩ ሳይንቲስት ናቸው።ባለቤታቸው ዶክተር ፀጋ ሰለሞን ደግሞ የክትባት እና የመድሃኒት ተመራማሪ ናቸው።ጥንዶቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ተማሪዎች በተለያዩ ዘርፎች ስልጠና የሚሰጥ ብሩህ ትውልድ/Brighter Generation/የተሰኘ መርሃግብር መስርተዋል።

 Ethiopian American NASA Scientist Dr.Berhanu Bulch and Dr.Tsega Solomon
ምስል፦ privat

መርሀ ግብሩ በውጭ የሚኖሩ ሙህራንን የሚያሳትፍ ነው

This browser does not support the audio element.


አሜሪካ የሚኖሩ ሁለት ጥንድ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሳይንቲስቶች በኢትዮጵያ ለሚገኙ ተማሪዎች በተለያዩ ዘርፎች  የገፅ ለገፅ እና የበይነመረብ ስልጠና በመስጠት ትውልድን ለመቅረፅ የሚያስችል ብሩህ ትውልድ የተሰኘ መርሀግብር  መስርተዋል። የዛሬውን የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅት በጥንዶቹ ሙያዊ  አበርከቶት እና በመሰረቱት መርሀግብር  ላይ ያተኩራል። 
ዶክተር ብርሀኑ ቡልቻ  በአሜሪካው የጠፈር ምርምር  ናሳ /NASA /  ጨረቃ ላይ ውሃ የሚፈልግ መሳሪያ የሰሩ ሳይንቲስት ናቸው።ባለቤታቸው ዶክተር ፀጋ ሰለሞን ደግሞ  ባዮኬሚስት እና የፕሮቲን ምህንድስና ተመራማሪ ሳይኒትስት ናቸው።ጥንዶቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ተማሪዎች  እነሱ ያገኙትን ዕድል እንዲያገኙ ለማድረግ እና ለማብቃት በተለያዩ ዘርፎች ስልጠና የሚሰጥ ብሩህ ትውልድ/Brighter Generation/የተሰኘ መርሃግብር መስርተዋል።
በዚህ መርሀግብር በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን  ጋር  በመሆን   በተለያዩ ዘርፎች  የገፅ ለገፅ እና በበይነመረብ የቨርቹዋል ስልጠና በኢትዮጵያ ለሚገኙ ተማሪዎች ይሰጣል።በቅርቡም ለሁለተኛ ጊዜ በአራት የተለያዩ የማስልጠኛ ጣቢያዎች  ለሶስት ሳምንት ስልጠና ያገኙ130 ተማሪዎችን በአዲስ አበባ ከተማ አስመርቀዋል።ለመሆኑ ይህንን መርሀግብር  የመጀመሩ ሀሳብ እንዴት መጣ?ዶክተር ብርሃኑ ቡልቻ።
«በ2022 ታህሳስ መጨረሻ  ኢትዮጵያ በሄድንበት ጊዜ ያየናቸው ሰፊ ችግሮች አሉ።እና እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልዶ እንድጎ ሌላ ሀገር እንደሄደ ሰው፤ እኔም የበኬሌን  ሃላፊነቴን መወጣት አለብኝ ብዬ አስባለሁ። እንዲሁም በተመሳሳይ ዶክተር ፀጋ  እዚህ አሜሪካ ውስጥ ብታድግድም ለኢትዮጵያ ግን በጣም ቅርብ የሆነ ግንኙነት አላት።እና በተቻለ መጠን ሁለታችንም ሀገር መለወጥ እንፈልጋለን። እና ግን እንደኛ ብዙ ምኞት እና ፍላጎት ያላቸው ሰዎች አሉ።በዲያስፖራው ውስጥ የሚገኙ በጣም የተማሩ  አቅም ያላቸው።ነገር ግን ይህንን ዕድል አግኝተው ኢትዮጵያ ውስጥ ትውልድን ለመስራት ባለው እርቀት  እዚህ ሀገር ባለው «ቢዚ» የሆነ «ላይፍ ስታይል» ይህንን ማሳካት ለብዙ ሰው ይከብዳል። ስለዚህ እኛ ያሰብነው ይህንን ነገር እኛ ብቻችንን ከምንሰራው ከኛ ጋር ሆነው ሰዎችን የምናሰራበት «ፕላትፎርም» ብንፈጥር በጣም ብዙ ሰዎችን አሳትፈን ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ተማሪዎችን  «ሸፕ» ማድረግ እንችላለን ብለን ያስብነው ፕሮጄክት ነው።»በማለት አመሰራረቱን አብራርተዋል።
ይህ መርሃግብር ሁለት ክፍሎች ያሉት ሲሆን የመጀመሪያው በውጭ ተወልደው ያደጉ ወይም በልጅነታቸው የወጡ እና ሁለተኛው ትውልድ የሚባሉትን ኢትዮጵያውያን ወደ ኢትዮጵያ በመውሰድ ገፅ ለገፅ እንዲያስተምሩ ማድረግ ነው።ሁለተኛው ደግሞ በየትኛውም ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በቨርቹዋል በበይነመረብ የሚያስተምሩበት ነው።
በዚህ መሰረት በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ ሁለተኛ ዙር ተመራቂዎችን  በማሰልጠን የተሳተፉት አሜሪካን ሀገር ከሚገኘው ከታዋቂው የማሳቹሴት የቴክኖሎጅ ተቋም /MIT / የመጡ በጎ ፈቃደኛ ተማሪዎች ናቸው። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እስካሁን 9 የሙከራ መርሀግብሮች  መጀመራቸውን  የሚናገሩት ዶክተር ብርሃኑ፤ በመጭው ሰኔ ግን ወደ 50 ለማሳደግ መታቀዱን አመልክተዋል። 
የብሩህ ትውልድ መርሃ ግብር ከየትምህርት ቤቱ በትምህርታቸው ጎበዝ የሚባሉና ጥሩ ውጤት ያላቸውን የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን መርጦ በማሰልጠን ላይ ያተኮረ  ሲሆን፤ ዓላማውም ዶክተር ፀጋ ሰለሞን እንደሚሉት የአካባቢውን ችግር የሚፈታ ትውልድ  ማፍራት ነው።
«የኛ ፐሮገራመም ለየት የሚያደርገው የአንድ ቀን ወርከሾፐ አይደለም።ኮርሰ ነው።የምናስተምረው ደግሞ አስፈላጊ የሆኑ ትምህረቶችን ነው። »ካሉ በኋላ፤ንባብ ፣ፅሁፍ፣ የአደባባይ ንግግር ፣በጥልቀት  ስለማሰብ፣ ጥሩ መሪ ስለመሆን እና የአካባቢን ችግር ስለመፍታት መሆኑን አብራርተዋል። 
ኢትዮጵያ ተወልደው በ12 ዓመት ዕድሚያቸው ወደ አሜሪካ ያቀኑት ዶክተር ፀጋ  ምንም እንኳ የኢትዮጵያን የትምህርት ስርዓት ችግር ኖረው ባያዩትም ከተለያዩ ሰዎች ያገኙት መረጃ በችግሩ ላይ መፍትሄ ለማምጣት እንዲሰሩ አድርጓቸዋል።
ሳይንቲስቷ ከአሜሪካው ቨርጂኒያ ዩንቨርሲቲ በኬሚስትሪ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ፣ከሜሪላንድ ዩንቨርሲቲ በባዮኬሚስትሪ እና በባዮፊዚክስ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ይዘዋል። በአሜሪካ ብሄራዊ  የደረጃዎች እና የቴክኖሎጅ ተቋም/NIST/  ተመራማሪ ሆነው ሰርተዋል።በአሁኑ ወቅት ደግሞ ክላክሶ ስሚዝ ክሊኔ /GlaxoSmithKline/ በተባለ የመድሃኒት እና የክትባት ምርምር ድርጅት በመድሃኒት እና ክትባት ምርምር ላይ በመስራት ላይ የሚገኙ ሳይንቲስት ናቸው። ሳይንቲስቷ በፕሮቲን ምህንድስናም ጠለቅ ያለ ጥናት ሰርተዋል።«ምን ላይ ያተኩራል ብዙ ጊዜ ፕሮቲን ከምንመገበው ምግብ ጋር ነው የምናያይዘው ግን ጠለቅ ብለን ስናስበው ፤ከሰውነታችን ጋር እንዴት ነው የሚያያዘው ብለን በምናስብበት ጊዜ ያለን ዲኤንኤ ለፕሮቲን የሚሰጠው መረጃ ፕሮቲኖች የሚሰሩበት ነው።እና ብዙ ጊዜ እነዚህ ፕሮቲኖች ኮዳቸው ትክክል ካልሆነ የሆነ ስህተት ከተፈጠረ «ሚዩቴሽን» ይባላል። ወደ በሽታ ይቀየራል።ፕሮቲኑም ትክክለኛ ስራውን አይሰራም።»በማለት ገልፀዋል።
በዚህ ሁኔታ ፕሮቲን በሰውነት ውስጥ በትክክለኛ መንገድ ተፈጥሯዊ ስራውን ማከናወን ሲያቅተው የሚመጡ በሽታዎችን ለማከም የሚቻልበትን መንገድ በጥናቱ አመልክተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በጎርጎሮሳዊው የዘመን ቀመር በ1969 ዓ/ም በአፖሎ11 የምርምር መርሀ ግብር ኒል አርምስትሮንግ እና በዝ አልድሪን ጨረቃን ለመጀመሪያ ጊዜ ረግጠዋል። በኋላም እስከ 1972 የአፖሎ 17 ተልዕኮ ድረስ ለአምስት ጊዜ ያህል ወደ ጨረቃ ጉዞ ተደርጓል።ከአፖሎ 17  ወዲህ ግን የሰው ልጅ ድጋሜ ወደ ጨረቃ ሄዶ አያውቅም።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የአሜሪካው የጠፈር ምርምር ጣቢያ በእንግሊዝኛው ምህፃሩ /NASA/  የሰው ልጆችን ዳግመኛ ወደ ጨረቃ ለመላክ አርቲሜስ የሚባል የምርምር መርሀግብር ጀምሯል። ዶክተር ብርሀኑ ቡልቻ የዚህ ምርምር አካል ናቸው።
እሳቸው እንደሚሉት የአሜሪካው የጠፈር ምርምር ናሳ፤ ላለፉት ስምንት አመታት ከማርስ ወደ ጨረቃ ጥናት ፊቱን አዙሯል።በዚህ ጥናትም በሚቀጥሉት  ሦስት እና አራት ዓመታት  ናሳ ፤ ወደ ጨረቃ ዳግም ሰው ለመላክ አቅዷል።ከዚያ በፊት ግን ለሰው ልጆች የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማሟላት የተለያዩ ጥናቶች እየተሰሩ ነው።ከነዚህም መካከል የዶክተር ብርሃኑ  ጥናት አንዱ ነው።«አሁን በተጀመረው በአዲሱ የአርቲሜስ ሚሽን የሰው ልጅ መልሶ ወደ ጨረቃ ማዕድንን ፍለጋ፣ የሰው ልጅ ለህይወቱ የሚያስፈልጉትን ነገር ለማስተካከል እንዲሁም የሰውን ልጅ እንዴት እንጠብቀዋለን፣ ከመሬት ካለው ህይወቱ አውጥተን ሌላ ቦታ እንዴት እንወስደዋለን፣ የሚሉ ትልልቅ ጥያቄዎችን ለመመለስ የተደረገ  ጅማሬ ነው። እንደሚታወቀው የሰው ልጅ ለመኖር ከሚያስፈልጉት ነገሮች አንዱ ደግሞ ውሃ ነው።ስለዚህ የኔ ጥናት ጨረቃ ላይ ያለውን ውሃ ማሰስ ነው»ሲሉ አብራርተዋል።በመሆኑም እሳቸው ከሚመሩት የናሳ የምርምር ቡድን ጋር በመሆን በጨረቃ ላይ የውሃ ክምችት የት እንዳለ በትክክል የሚለይ አነስተኛ ክብደት እና በመጠን ያለው መሳሪያ  አዘጋጅተዋል። ይህንን ውሃ አሳሽ መሣሪያ በሁለተኛው ዙር የአርቲመስ ተልዕኮ ወደ ጨረቃ ለመላክም፤ በአሁኑ ወቅት ከበረራ በፊት ያሉ  ሙከራዎችን እና መመዘኛዎችን  በማጥናት ላይ ናቸው። ተመራማሪው እንደሚሉት  ይህ መሳሪያ ለወደፊቱም ጨረቃ ላይ ውሃ ከመፈለግ ባለፈ ውሃ ውስጥ መርዛማ ነገሮችን ለመለየት እንዲሁም የተለያዩ ሞሎኪሎችን በማጥናት ግብዓት መስጠት የሚችል ነው።ይህ መሣሪያ በቀጣይም  በሌሎች ፕላኔቶች ውስጥ በሚገኙ ጨረቃዎች ላይ ናሳ ለሚያደርገው ምርምር አጋዥ ሆኖ ያገለግላል።«ናሳ ከጨረቃ ያለፈ «ኢንተርስት» አለው።ስለዚህ በሚቀጥለው ደግሞ በኛ ፕላኔት ሲስተም ውስጥ የተለያዩ ጨረቃዎች አሉ ።አሁን ለምሳሌ ሳተርን ፣ጁፒተር እያንዳንዳቸው ከ50 በላይ ጨረቃዎች አሏቸው።አንዳንዶቹ ጨረቃዎች ውሃ እንዳላቸው ጥሩ ግምቶች አሉ።ጥናቶቹም የሚያሳዩት እንደዛ ነው።» በማለት መሳሪያው ለቀጣይ ጥናት ሊጠቅም እንደሚችል አመልክተዋል። 

ዶክተር ብርሃኑ ቡልቻ የናሳ ሳይንቲስት ምስል፦ Michael Guinto/Cover-Images/IMAGO
ዶክተር ፀጋ ሰለሞን ትውልደ ኢትዮጵያዊት ሳይንቲት ምስል፦ Privat
ዶክተር ፀጋ ሰለሞን የብሩህ ትውልድ መስራች ምስል፦ Privat
ዶክተር ብርሃኑ ቡልቻ የናሳ ሳይንቲስት እና የብሩህ ትውልድ መስራች ምስል፦ privat

ከስድስት ዓመት በፊት  ናሳን የተቀላቀሉት ዶክተር ብርሃኑ ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተወልደው ባደጉባት በአዲስ አበባ ከተማ ሚኒልክ ከፍተኛ 2ተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አሜሪካ ተሻግረው በ2010 ዓ/ም ከቨርጂኒያ ኮመንዌልዝ ዩንቨርሲቲ በኤለክትሪክ ምህንድስና እና በፊዚክስ አግኝተዋል።የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ በቨርጂኒያ ዩንቨርሲቲ በኤለክትሪክ ምህንድስና ተመርቀዋል።በማሳቹሴት የቴክኖሎጅ ተቋም ተመራማሪ መሀንዲስ ሆነው ሰርተዋል።በአሁኑ ወቅት ደግሞ ናሳ በማገልገል ላይ ይገኛሉ።በዚህ የምርምር ጣቢያ  ባላቸው የላቀ አፈፃጸም 5 ሽልማቶችን አግኝተዋል።ከተማሪነት ጊዜያቸው ጀምሮ በሳይንሱ ዘርፍ ችግር ፈች ስራዎችን የመስራት ህልም እንደነበራቸው የሚገልፁት ተመራማሪው ለዚህ ህልማቸው ናሳ ተስማሚ ቦታ ሆኖ አግኝተውታል።«ብበዛት መሬት የወረደ ነገር ከሚሰሩ ድርጅቶች  አንዱ ናሳ ነው።«ኢምፖሲብል» የሚባሉ በአዕምሮ ለማሰብ የሚከብዱ ስራዎችን ነው የሚሰራው። እና የዚህ አካል በመሆኔ በጣም ደስተኛ ነኝ።» ለዚህም ጠንክሮ መስራትን ፣አርቆ ማሰብን እንዲሁም ትጋትን ባህሪያቸው ማድረጋቸውን ገልፀዋል። 

ተመራማሪው ለወደፊቱም በኢትዮጵያ እየሰሩ ያሉትን ትውልድ የመቅረፅ ስራ ከማጠናከር ባሻገር  በአፍሪቃ ደረጃ ሌሎች ስራዎችን የመስራት ዕቅድም አላቸው።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ሁለቱን ሳይንቲስቶች ጨምሮ  በተለያዩ መስኮች በርካታ ሙህራንን ያፈራች ቢሆንም፤ መሬት ላይ ወርዶ የህዝቡን ህይወት የሚለውጥ ስራ አልሰሩም የሚል ወቀሳ በተለያዩ መድረኮች ተደጋግሞ ይነሳል።በወቀሳው የሚስማሙት ዶክተር ብርሃኑ ለዚህም በርካታ ምክንያቶች መኖራቸውን ገልፀዋል። ስለሆነም  እሳቸው እና ባለቤታቸው በጀመሩት የብሩህ ትውልድ መርሀግብር  በመሳተፍ ትውልድን የሚቀርፅ እና ሀገርን የሚያሳድግ  ስራ ለመስራት በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ሙህራን ዕድሉን እንዲጠቀሙበት አሳስበዋል።

 

 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።


ፀሀይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW