1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብሩንዲ ወቅታዊ ሁኔታ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 8 2007

እንደ ተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽንUNHCR ገለፃ ባለፈዉ ሳምንት ብቻ ከ 100 ሺህ የሚበልጥ የብሩንዲን ነዋሪ ሃገሩን ጥሎ ወደ ጎረቤት ሃገር ፈልሶአል።

Tansania Flüchtlinge aus Burundi
ምስል DW/P. Kwigize

የብሩንዲ ወቅታዊ ሁኔታ

This browser does not support the audio element.

በብሩንዲ አጎራባች ታንዛንያ ካጉዋንጋ በሚባለዉ ሥፍራ ላይ በአሁኑ ሰዓት ከ 50 ሺህ በላይ የብሩንዲ ስደተኞች ይገኛሉ፤ ቦታዉ ላይ ለሕይወት አስፈላጊ የሆነ መሰረታዊ ነገሮች እጥረት በመከሰቱ ሁኔታዉ እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም ተመልክቶአል። የመጠጥ ዉኃ እጥረት እና የመፀዳጃ ሁኔታዉ እንዲሁም የመጠለያ ሥፍራ እጥረት መኖሩን የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ገልጾአል።

ምስል Reuters/G. Tomasevic

ፕሬዚዳንት ፒየር እንኩሩንዚዛ ለ3ኛ ጊዜ ለፕሬዚዳንትነት እጩ ሆነው ለመቅረብ መዘጋጀታቸውን ተከትሎ እጅግ ከፍተኛ ተቃዉሞ ተቀስቅሶ ቢያንስ 25 ሰዎች መገደላቸዉ ይታወቃል። ባለፈዉ ረቡዕ የቡሩንዲ ጀኔራል እንኩሩንዚዛ ከሥልጣን ተባረዋል ብለዉ በማወጃቸዉ መፈንቅለ መንግሥቱ ደጋፊዎችና በመንግስት ወታደሮች መካከል ኃይል የቀላቀለ ትግል ተካሂዶ ነበር። የመፈንቅለ መንግስት ሙከራዉን የመሩት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸዉ መያዛቸዉ ትንናት አርብ ነበር ይፋ የሆነዉ።

ትናንት አርብ በይፋ የብሩንዲ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ መክሸፉ ከተነገረ በኃላ እጃቸዉን ለመንግሥት እንደሰጡ የተመለከተዉ አንዱ የመፈንቅለ መንግሥት መሪ ጀኔራል ጎድፍሯ ኒዮምባሬ «እጄን ለመንግሥት ለመስጠት የወሰንኩት ራሴ ነኝ ፕሪዚደንቱም እንደማይገሉኝ አምናለሁ »ማለታቸዉ ተመልክቶአል።

ባለፈዉ ረቡዕ የብሩንዲን መፈንቅለ መንግስት ጀኔራል ጎድፍሯ ኒዮምባሬ፤ ኢሳንጋኒሮ በተሰኘው የግል ራዲዮ ጣቢያ በሰጡት መግለጫ ፣ እንኩሩንዚዛ ከእንግዲህ በሥልጣን ላይ አይደለም የሚገኙት መንግሥታቸውም ፈርሷል ሲሉ ማስታወቃቸዉ ይታወሳል። ሆኖም ራሳቸው ፕሬዝዳንቱ ንኩሩንዚዛ በፌስቡክ በሰጡት መግለጫ መፈንቅለ መንግሥቱ «ከሽፏል » ብለዉ ነበር ።በዝያን ወቅት ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ፤ በቡሩንዲ ቀውስ ሳቢያ ታንዛንያ ውስጥ ከምሥራቅ አፍሪቃ ማህበረሰብ መሪዎች ጋር ለመምከር ታንዛንያ እንደሚገኙ ተነግሮ ነበር። ስለቡሩንዲ ጉዳይ ዳሬሰላም ላይ ከሚወያዩት የምሥራቅ አፍሪቃ ሃገራት አንዷ የሆነችዉ የታንዛኒያ ፕሬዝደንት ጃካያ ኪክዌቴ የተካሄደዉ መፈንቅለ መንግሥት የሀገሪቱን ችግር እንደማይፈታ በማመልከት ጉባኤዉ ማዉገዙን እንዲህ ሲሉ አመልክተዋል።

«ቡጁሙቡራ ዉስጥ አዳዲስ ለዉጦች መከሰታቸዉን ተረድተናል። ጉባኤዉ ቡሩንዲ ዉስጥ የተካሄደዉን መፈንቅለ መንግሥት በከፍተኛ ሁኔታ አዉግዟል። በጉባኤዉ እይታም ይህ የቡሩንዲን ችግር ሊፈታ አይችልም። መንግሥት ግልበጣዉን አንቀበልም። በከፍተኛ ደረጃ እናወግዘዋለን፤ ሀገሪቱም ወደሕገመንግሥታዊ ሥርዓት እንድትመለስ ጥሪ እናቀርባለን።»

ምስል Reuters/G. Tomasevic

መንግስት እንዳስታወቀው መፈንቅለ መንግሥቱን በመጠንሰስ የተጠረጠሩ በርካታ ሰዎች ታስረዋል ። ከመካከላቸው እጃቸዉን የሰጡት የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ጀኔራል ጎድፍሯ ኒዮምባሬና ሌሎች የመከላከያ ና የደህንነት ሚኒስቴር እንዲሁም የፖሊስ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይገኙበታል ። እንደ ሮይርስ ዘገባ መፈንቅለ መንግሥቱ መክሸፉና ኑኩሩንዚዛም መመለሳሳቸው እንደተሰማ በርክት ያሉ ነዋሪዎች በየጎዳናው ባንዲራ እያውለበለቡ ደስታቸውን ሲገልጡ ታይተዋል ።በአንፃሩ በርካቶች አደባባይ በመውጣት ተቃውሞአቸውን ሲያሰሙም ነበር ። የቡሩንዲ የፕሬዚዳንት እንኩሩዚዛን ለ 3ኛ ጊዜ እጩ ሆኖ የመቅረብ እቅድ በመቃወም፤ ብርቱ ተቃውሞ ከተቀሰቀሰ 2 ሳምንት በላይ መቀጠሉ ይታወቃል።

ቡሩንዲ ፤ በጎሣ በመከፋፈል በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ከተገደሉበት አሠቃቂ ውዝግብ ከተገላገለች 10 ዓመት ገደማ ቢሆንም፤ ለ 3ኛ ጊዜ ለምርጫ እጩ ሆኜ ልቅረብ ብለዉ የተነሣሱት ፕሬዚዳንት እንኩሩንዚዛ ፤ አገሪቱን ዳግመኛ ወደ የእርስ በርስ ጦርነት እንዳይዶልዋት አሥግቷል።

የአዉሮጳ ሕብረት እቅድ -ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎችን በወታደራዊ ኃይል ለመግታት የአዉሮጳ ሕብረት የያዘዉ እቅድና የብሩንዲን ወቅታዊ ሁኔታ ያየንበት የለቱን ትኩረት በአፍሪቃ መሰናዶ አጠናቀን ለጥግጅቱ አዜብ ታደሰ ነኝ ጤና ይስጥልኝ።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሃመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW