1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብራንድንበርጉ አካባቢያዊ ምርጫ ውጤትና አንድምታው

ማክሰኞ፣ መስከረም 14 2017

FDP ከSPD እና ከአረንጓዴዎቹ ፓርቲዎች ጋር የሚያቀራርቡት ጥቂት ጉዳዮች ብቻ ናቸው። በዚህም FDP በበርሊኑ ጥምር መንግሥት ውስጥ መቀጠል አለመቀጠሉ እያነጋገረ ነው። ፓርቲው ከጥምሩ መንግሥት እንዲለቅ የሚወተውቱት የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ጥምረቱ እስከ መጪው ገና ይቀጥላል ብለው አያምኑም ።

LTW Brandenburg
ምስል Fabrizio Bensch/REUTERS

የብራንድንበርጉ ምርጫ ውጤትና አንድምታው

This browser does not support the audio element.

«በብራንድንቡርጉ የምርጫ ውጤት በጣም ተደስቻለሁ ።SPD በጣም ጥሩ ውጤት አግኝቷል። ለውጤቱም ዲትማር ቮይድከን እንኳን ደስ አለዎ እላለሁ። በህብረት መቆምና ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል። እናም ለሚቀጥለው ዓመቱ አጠቃላይ ምርጫ የምናደርገው ይህንኑ ነው። ይኽውም መታገል በወሳኝነት እና በኅብረት በመቆም እንዲሁም ሀገራችን የተጋረጡባትን ችግሮች እንዴት እንደምናስወግድ ትኩረት መስጠት አለብን» 
የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልትስ ፓርቲያቸውየሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ በጀርመንኛው ምህጻር SPD የብራንድንቡርጉን ምርጫ ማሸነፉ ከተረጋገጠ በኋላ ደስታቸውንና የገለጹበትና የወደፊቱ የፓርቲያቸው ትኩረት ምን መሆን እንዳለበት የጠቆሙበት አስተያየታቸው ነበር ። ከሦስት ሳምንት በፊት  SPD  በሁለቱ የምሥራቅ ጀርመን ግዛቶች በቱሪንገንና በዛክሰን አንሀልት በተካሄዱ አካባቢያዊ ምርጫዎች ካገኘው አሸማቃቂ  ውጤት ጋር ሲነጻጸር  የብራንድንቡርጉ ውጤት ለሾልዝና ለፓርቲያቸው እንዲሁም ለደጋፊዎቻቸው ትልቅ እፎይታን አስገኝቷል። ሆኖም ወደ ስልጣን ማማው እንዲጠጋ የማይፈለገው  «አማራጭ ለጀርመን» በጀርመንኛው ምህጻር AFD ፣SPD  ባሸነፈበትም በእሁዱ ምርጫ ከፍተኛ ድምጽ ማግኘቱ የቀደመውን ስጋት ሊቀንስ አልቻለም ።ምክንያቱም ቀኝ ጽንፈኛውና ስደተኞችን ጀርመን መግባታቸውን የሚቃወመው ፓርቲው በእሁዱ ምርጫ ሁለተኛ ደረጃን ቢይዝም ያገኘው ድምጽ ግን ብዙ ነው። በጀርመኖቹ በዛክሰን አንሀልት እና ቱሪንገን ፌደራዊ ግዛቶች የተካሄደው ምርጫ ውጤትና መዘዙ

SPD ና FDP ያገኙት ተቀራራቢ ውጤት

SPD በብራንድንቡርጉ ምርጫ 30.9 በመቶ ድምጽ አግኝቶ ነው ያሸነፈው፤በዚህ ውጤት መሠረትም ከግዛቲቱ ምክር ቤት መቀመጫዎች 32ቱን ይወስዳል። ሁለተኛውን ደረጃ የያዘው አማራጭ ለጀርመን ፓርቲ ደግሞ 29.2 በመቶ ድምጽ በማግኘት 30 የግዛቲቱን ምክር ቤት መቀመጫዎች ይይዛል። ይህ ውጤትም በሁለቱ የምሥራቅ ጀርመን ግዛቶች ከዚህ ቀደም ካሸነፋቸው መቀመጫዎች ጋር ሲደመር በምሥራቅ ጀርመን እጅግ ጠንካራው የፖለቲካ ኃይል ያደርገዋል።   ባለፈው እሁድ በሰሜን ጀርመንዋ ፌደራዊ ግዛት ብራንድንቡርግ ብቻ ነበር አካባቢያዊ ምርጫ የተካሄደው። 2.1 ሚሊዮን መምረጥ የሚችሉ ዜጎች የሚገኙባት ግዛቲቱ ከ16 የጀርመን ፌደራል ግዛቶች አንዷ ናት ።ሆኖም በምሥራቅ ጀርመን ግዛቶች የሚካሄዱ ምርጫዎች ውጤት በሀገሪቱ ብሔራዊ  ፖለቲካ ላይ ቀላል የማይባል ተጽእኖ ማሳደሩ እንደማይቀር ነው የሚነገረው።

ኦላፍ ሾልዝ የጀርመን መራኄ መንግሥትምስል Fabian Sommer/dpa/picture alliance

ኦላፍ ሾልዝ ግን የብራንድንቡርጉን ድል በአጠቃላዩ ምርጫ ላይም መድገም እፈልጋለሁ ነው ያሉት። 
«በአጠቃላዩ ምርጫ እንካፈላለን እኔም በብራንድቡርግ የተሳካልንን ለመድገም እፈልጋለሁ ።SPD በፉክክሩ ጠንካራ ፓርቲ ነው። እናም ቀኝ ጽንፈኞች በሀገራችን ምንም እድል እንደሌላቸው ለማረጋገጥ የሚቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ»ሲሉ ተናግረዋል።  
አንጋፋዎቹ ፓርቲዎች የሚገፉት አማራጭ ለጀርመን ከሦስት ሳምንት በፊት በቱሪንገንና በዛክሰን አንሀልት በተካሄዱ ምርጫዎች ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ነባሮቹንና ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ አላቸው ሲባሉ የቆዩትን ፓርቲዎች አስደንግጧል። ይህንኑም በብራንድቡርግም ደግሞታል። ምንም እንኳን AFD ሁለተኛ ደረጃን ቢያገኝም ፓርቲው በውጤቱ  እጅግ መርካቱን ነው የፓርቲው መሪ አሊስ ቫይድል የተናገሩት።በጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የፓርቲው ስራ አስኪያጅ ቤርንት ባውማን መጪው የኛ ነው ብለዋል።ከጀርመኑ የብራንድንቡርግ ፌደራዊ ግዛት ምርጫ ምን ይጠበቃል?


«ይህ አነስተኛ ደረጃ ብቻ ነው ። ከምርጫ ወደ ምርጫ እየተጓዝን ነው።በቅርቡ 38 በመቶ ድምጽ ባሸነፍንበት በቱሪንገን የመረጡንን ወጣቶች ተመልከቱ ። መጪው ጊዜ የኛ ነው።»

በብራንድንቡርጉ ምርጫ ሁለተኛ ደረጃ ያገኘው የአማራች ለጀመርን ፓርቲ መሪዎች ምስል Christoph Soeder/dpa/picture alliance

የአረንጓዴዎቹና የነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ አይሸነፉ ሽንፈት 

ከሶሣል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ጋር ተጣምረው የፌደራል ጀርመንን መንግሥት የሚመሩት ለአካባቢ ጥበቃ የሚሟገተው የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ እና ለዘብተኛው የነፃ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ FDP በብራንድንቡርጉ ምርጫ እንደቀደሙት ሁለቱ የምሥራቅ ጀርመን ፌደራል ግዛቶች ሁለ በብራንድንቡርግም ለሦስተና ጊዜ አይሸነፉ ሽንፈት ገጥሟቸዋል። ሁለቱም ፓርቲዎች በብራንድንቡርግ ግዛት ምክር ቤት ውስጥ መቀመጫ ለማግኘት የሚያስችላቸውን አምስት በመቶ ድምጽ እንኳን ማግኘት አልቻሉም። የጀርመን አረንጓዴዎቹ ፓርቲ መሪ ሪካርዳ ላንግ ዲሞክራሲያዊ የሚባሉ ፓርቲዎች ዝቅ ብለው በተቃራኒው ጸረ ዴሞክራሲ የሚባሉት ከፍ ያሉበትን ውጤት እንዴት መመከት እንደሚቻል ግምት ውስጥ ማስገባትና ዴሞክራሲም የሰዎችን ሕይወት እንደሚቀይር ማሳየት እንደሚገባ አሳስበው ውጤቱ ይህ ሊሆን የቻለበትን ምክንያትም ጠቁመዋል። 
«ሰዎች እየተደመጥን ነው ብለው አይሰማቸውም።በሌሎቹ ብቻ ሳይሆን በኛ በአረንጓዴዎቹም ላይ ተመሳሳይ አመለካከት አላቸው።እኛ አረንጓዴዎቹ በፌደራል መንግሥትም ሆነ በፌደራል ግዛቶች የምንገኝ በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል የሚገኙ ሰዎችን ሕይወት እውነታ ቀረብ ብለን መመልከት ይኖርብናል። ግልጽ ነው አሉታዊ አካሄድ አለ። ይህንን አሁን ልንሰብረው ይገባል። እናም አሁን በዚህ ላይ በጋራ በማተኮር ከዚህ ለመውጣት በአንድነት እንታገላለን»

 
ሌላው ተሸናፊ ፓርቲ FDP ከምርጫው ውጤት በኋላ የተረጋጋ አይመስልም። ፓርቲው ለመጥፎው ውጤት ራሱ ያለበትን ጥምር መንግሥት ወቅሷል። የፓርቲው ዋና ፀሐፊ ብያን ዲር ሳራይ ደግሞ«በአሁኑ ጊዜ የነጻነት ወዳድ  ፣አዎንታዊ እና የጠንካራ ሠራተኛ ገጽታ የነበረው ፓርቲያችን በርሊን በሚካሄዱ የጥምር መንግስቱ በርካታ  ጸቦች ምክንያት ተሸሽገዋል። የዛሬ ምሽት እጅግ አስቸጋሪ ነው። ይሁንና አዎንታዊውን ሁኔታ በማሰብ በመታገል እንቀጥላለን። በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ስለውጤቱ እንወያያለን እንመዝነዋለንም። ይህ ብቻ አይደለም ወቅታዊውን የፖለቲካዊ ሁኔታም በዝርዝርና በጥልቀት በFDP ኮሚቴዎች እንመረምራለን ። የግድ ውሳኔዎች ላይ መደረስ አለበት።»ብለዋል

የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ አባል የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አና ሌና ቤርቦክ የብራንድንቡርጉን ምርጫ ውጤት ከፓርቲያቸው አባላት ጋር ሲከታተሉምስል Frank Hammerschmidt/dpa/picture alliance

የጥምሩ መንግሥት እጣ ፈንታ 


ከተጣማሪዎቹ ፓርቲዎች መለያ ቀለም ጋር ተያይዞ የትራፊክ መብራት በመባል የሚታወቀው ጥምረት ፤  ቀይ የSPD ቢጫ የFDP እንዲሁም አረንጓዴ የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ቀለሞች ይወክሏቸዋል/ የእነዚህ ፓርዎች  ጥምረት የሚንቀጠቀጥ ተድርጎ ነው በብዙዎች የሚቆጠረው። ምንም እንኳን ሦስቱ ፓርቲዎች ተጣምረው ጀርመንን መምራት ከጀመሩ ሦስት ዓመታት ቢቆጠሩም የነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ወደ ግራ ከሚያዘነብሉት ከሶሻል ዴሞክራቶቹና አረንጓዴዎቹ ፓርቲዎች ጋር የሚያቀራርቧቸው ጥቂት ጉዳዮች ብቻ ናቸው። በዚህ የተነሳም FDP በበርሊኑ ጥምር መንግሥት ውስጥ መቀጠሉ እያነጋገረ ነው። ፓርቲው ከጥምሩ መንግሥት እንዲለቅ የሚወተውቱት የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ጥምረቱ እስከ መጪው ገና ይቀጥላል ብለው አያምኑም ። የፓርቲው መሪ ግን ስለወደፊቱ እንነጋገርበታለን ሲሉ  ነው መልስ የሰጡት።

የጀርመን ጥምር መንግሥት መለያ የትራፊክ መብራት ምስል Dwi Anoraganingrum/Geisler-Fotopress/picture alliance


በብሔራዊ ደረጃ ከ5 ሕጋዊ መራጮች አንዱ ብቻ በአሁኑ መንግሥት ስራ ደስተኛ ነው። በብራንድንቡርጉ የምርጫ ዘመቻ ወቅት ደግሞ ትልቁን ቦታ የያዙት የታመመው, ኤኮኖሚ እና ፍልሰትእ እንደነበሩ የዶቼቬለዋ የዛቢነ ኪንካርትዝ ዘገባ ጠቁሟል። 

ወቅቱ እንደሚባለው ለSPDም ቢሆን ውሳኔ ላይ መድረስ ያለበት ነው። ለ11 ዓመታት ብራንድንቡርግን የመሩት የብራንድንቡርጉ መሪ ዲትማር ቮይድከን ማሸነፉ የቻሉት ራሳቸውን ከጥምሩ መንግሥት በማራቃቸው መሆኑ ይነገራል። ከሾልዝ ጋር እንኳን ፎቶ አለመነሳታቸው ነው የተገለጸው። ወደፊትም በግዛታቸው ፖለቲካ ብቻ እንደሚጠመዱ ነው ያሳወቁት። ፓርቲያቸው ካሸነፈ በኋላ ቪድከ ባሰሙት ንግግር ከውጤቱ ምን መማር እንደቻሉ ተናግረው ነበር 
«ለማንኛውም ስኬታማ ምርጫ መሠረቱ ከምንም በላይ ኅብረት ነው። ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ ቁርጠኝነት ነው።ለዚህም ወደ ክርክሩ በአስፈላጊ አዎንታዊ አመለካከት መግባቱ ጠቃሚ ነው። ይህንንም እንደ SPD ስለ ሀገራችን የወደፊት እጣ ያለንን በጎ አመለካከት ከእውነታው ጋር አዋህደን ነው ወደዚያ የምንገባው።»
የብራንድንቡርጉ ምርጫ ውጤት በሚቀጥለው ዓመቱ አጠቃላይ ምርጫ ላይ ሊያስድር የሚችለው ተጽእኖ ማነጋገሩ ቀጥሏል ። 

ኂሩት መለሰ
ታምራት ዲንሳ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW