1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ነው የተባለ የድምፅ ቅጂ ይፋ ሆነ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 22 2011

ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ በአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራሮች ላይ እርምጃ መውሰዳቸውን ያረጋግጡበታል የተባለ የድምፅ ቅጂ ይፋ ሆነ። የድምፅ ቅጂው ከአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋር በስልክ የተደረገ ነው ተብሏል። በመልእክት ልውውጡ «ሁሉም ከጸጥታ ቢሮ የሚሰጠውን መመሪያ እንዲጠብቅ» ትዕዛዝ ሲተላለፍ ይደመጣል።

Äthiopien | Diskussion über Bürger Sicherheitslage
ምስል፦ DW/A. Mekonnen

ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ በአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራሮች ላይ እርምጃ መውሰዳቸውን ሊያረጋግጥ ይችላል የተባለ የድምፅ ቅጂ ይፋ ሆነ። የድምፅ ቅጂውን ይፋ ያደረጉት የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉቀን ሰጥየ ናቸው። አቶ ሙሉቀን ሰጥየ ጥቃቱ በተፈጸመበት ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ከብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ጋር ቢያንስ ሶስት ጊዜ በስልክ መነጋገራቸውን ገልጸዋል። ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው እንደሆነ በተነገረለት የመልዕክት ልውውጥ ክልሉን በሚያስተዳድረው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራሮች ላይ እርምጃ መወሰዱን ሲናገሩ ይደመጣል። 

በቴሌቭዝን ጣቢያው በተላለፈው ድምፅ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው መሆናቸው የተገለጸው ሰው «በአዴፓ አመራሮች ላይ የሕዝቡ ሰላማዊ እና የመኖር መብቱ ጥያቄ ውስጥ ስለገባ፤ የሕዝብን ጥያቄ ለማንሳት በመቸገራቸው፤ የሕዝቡን ጥያቄ በመቀልበሳቸው በድርጅቱ አመራሮች ላይ እርምጃ ተወስዷል። እንዳትደነግጥ» ሲሉ ይደመጣል። አቶ ሙሉቀን ግን በወቅቱ በመደናገጣቸው ምክንያት «እርምጃ የተወሰደው እነ ማን ላይ ነው?» ብለው አለመጠየቃቸውን ለአማራ ቴሌቭዥን ጋዜጠኛ ተናግረዋል።
በመልእክት ልውውጡ «ሁሉም ከጸጥታ ቢሮ የሚሰጠውን መመሪያ እንዲጠብቅ» ትዕዛዝ ሲተላለፍ ይደመጣል። በዚሁ የድምፅ ቅጂ «እዚህ አካባቢ ማኅበረሰቡ ወደ ቤቱ እንዲገባ፤ የአካባቢው የጸጥታ ኃይል እና ሚሊሻ ደግሞ ራሱን እንዲቆጣጠር» የሚል ትዕዛዝ ጭምር ይገኝበታል። 

የአማራ ክልል እና የፌድራል መንግሥት ባለሥልጣናት ተሞክሮ ከሽፏል በተባለው መፈንቅለ-መንግሥት የጥቃት ዒላማ ከነበሩ ተቋማት መካከል የአማራ  ብዙኃን  መገናኛ ድርጅት እንደሚገኝበት በተደጋጋሚ ተናግረዋል። የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫም ይኸንኑ አረጋግጧል። ዋና ሥራ አስኪያጁ በባለሥልጣናቱ ላይ እርምጃ ተወሰደ በተባለበት ወቅት ተቋማቸው በልዩ ኃይል ይጠበቅ እንደነበር ተናግረዋል። ዘግየት ብሎም በመከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ሥር መግባቱን ኃላፊው አስረድተዋል። በአማራ ቴሌቭዥን ጣቢያ ይፋ በሆነው የመልዕክት ልውውጥ አቶ ሙሉቀን «ካሜራ እንላክ?» የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ ወደ እንግዳ ማረፊያ እንዲላክ ምላሽ ሲሰጥም ይደመጣል። 

በቢሯቸው ሳሉ አሳምነው ደውለው ያደረጉትን ንግግር በስልካቸው መቅረፃቸውን የተናገሩት አቶ ሙሉቀን 55 ሰከንዶች የሚረዝመውን የድምጽ ቅጂ በአማራ ቴሌቭዥን ጣቢያ በተላለፈው ቃለ-መጠይቃቸው መካከል እንዲሰማ አድርገዋል። 

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በባሕር ዳር ከተማ በተፈጸመው ጥቃት የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን፣ የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ-ሕግ ምግባሩ ከበደ እና የርዕሰ መስተዳድሩ የሕዝብ አደረጃጀት አማካሪ እዘዝ ዋሴ ሕይወታቸው አልፏል። የሦስቱ ባለሥልጣናት ቀብር በባሕር ዳር ከተማ ተፈጽሟል። 

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ጥቃቱ «የአማራ ሕዝብ መንግሥት፣ ጠንካራ ፓርቲ እና አመራር እንዳይኖረው» የተፈጸመ ነው ሲሉ ኮንነዋል። ድርጊት አቀነባብረዋል የተባሉትን ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ከሰላም ግንባታ እና ደሕንነት ቢሮ ኃላፊነታቸው የማንሳት ውሳኔ ነበር የሚለውን አስተባብለዋል።  

ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነውን «በግሉ ሳይሆን ተቋሙን ገምግመናል» ያሉት አቶ ዮሐንስ የክልሉ የሰላም ግንባታ እና ደሕንነት ቢሮ «ከውስጥም ከውጭም ያንዣበቡብንን አደጋዎች ለመከላከል በተለይ ደግሞ ሕግ እና ሥርዓት እንዲጠበቅ ለማድረግ» በፓርቲው እና በመንግሥት ድጋፍ ቢደረግለትም ስኬታማ አልሆነም ሲሉ ተችተዋል። 

አቶ ዮሐንስ «ከፖሊስ፣ የልዩ ኃይል እና የሚሊሻ መደበኛ አደረጃጀት ውጪ ያለ ኃይል ሕጋዊ እና ሥርዓት ያለው ሆኖ እንዲንቀሳቀስ ፍላጎት ነበረን። ግን ኢ-መደበኛ የሚመስሉ እንቅስቃሴዎች ይደረጋሉ። ይኸ ልክ አይደለም መስተካከል አለበት ብለን ነው። በአጠቃላይ በየአካባቢው በተለያየ ሥም የተደራጁ እንዲሁም ደግሞ ከመንግሥት መዋቅር ጎን ለጎን ታጥቀው ለመንቀሳቀስ የሚሞክሩ ኃይሎች በተለያየ ቦታ ሲንቀሳቀሱ እነዚህ መቆም አለባቸው፤ ወንድሞቻችን ናቸው፤ ማስተማር እና ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ መግባት አለባቸው፤ የማንም መሳሪያ መሆን የለባቸውም፤ ከዚህ ውጪ ደግሞ ሕግን የሚጥሱ ካሉ ሕግ እና ሥርዓት እንዲይዙ እና መልክ መያዝ አለበት የሚል ነገር በተደጋጋሚ ለተቋሙ ተነግሮት ተቋሙ ኢንኢፊሸንት የመሆን ወይም ደግሞ የማስፈጸም አቅሙ ዝቅተኛ የመሆን ሁኔታ ተከስቷል» ሲሉ ለአማራ ቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል። 
ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው አባል የነበሩበት የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ ልክ የዛሬ ሳምንት የተፈጸመውን ድርጊት «ምንም አይነት የሞራል፤ የሕግና የፖለቲካ አመክንዮ የሌለው» ሲል ኮንኗል። ማዕከላዊ ኮሚቴው «ድርጊቱ የክልሉን መንግሥትና ህዝብ እንዲሁም አገራችንን ለከፋ አደጋ የሚያጋልጥ፤ የተጠናና በዕቅድ የተመራ፤ የራሱ አደረጃጀት የነበረው እና አገራዊ ሥርዓቱን በኃይል በመናድ የመንግሥት ስልጣንን በኃይል ለመቆጣጠር» የተሞከረ መፈንቅለ-መንግሥት ብሎታል።

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW