1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ 4ተኛው ፓትርያርክ ዕረፍት የመታሰቢያ ዝግጅት በፍራንክፈርት

እሑድ፣ መጋቢት 11 2014

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጀርመንና አካባቢው ሃገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎሰ 4ተኛው ፓትርያርክን ዕረፍት አስመልክቶ በዛሬው ዕለት ከማለዳው ጀምሮ በፍራንክፈርት ምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሰፋ ያለ ልዩ የመታሰቢያ ዝግጅት አከናውኗል።

Deutschland | Äthiopisch-Orthodoxe Kirche | Abschied von Patriarch Abune Merkorios
ምስል Endalkachew Fekade/DW

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ 4ተኛው ፓትርያርክ ዕረፍት የመታሰቢያ ዝግጅት

This browser does not support the audio element.

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጀርመንና አካባቢው ሃገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎሰ 4ተኛው ፓትርያርክን ዕረፍት አስመልክቶ በዛሬው ዕለት ከማለዳው ጀምሮ በፍራንክፈርት ምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሰፋ ያለ ልዩ የመታሰቢያ ዝግጅት አከናውኗል። በጀርመንና አካባቢው የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አድባራት ተጠሪዎች ቅዱሳን አባቶች የሰንበት ትምህርትቤት ተማሪዎችና መዘምራን ርካታ ምዕመናንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተካፋይ በሆኑበት በዚሁ መርኃ ግብር ሥርዓተ ቅዳሴና ጸሎተ ፍትሃት የተካሄደ ሲሆን የቅዱስነታቸው የሕይወት ታሪክ እንዲሁም ለሀገሪቱና ለቤተክርስቲያኒቱ ሲኖዶሳዊ አንድነት ሁለንተናዊ ልማትና ዕድገት ያበረከቷቸው ጉልህ አስተዋጽዖዎችም ተወስተል::

የጀርመንና አካባቢው ሊቀ ጳጳስ አባ ዲዮናስዮስ ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስ፣ የበላዮቻቸውን መካሪ፣ የበታቾቻቸውን አክባሪ፣ በሥራ ታታሪ፣ በመንፈሳዊ አባትነታቸውና ትሑት ሰብዕናቸው አርኣያነት ያለው ቁጥብና አስተዋይ ነበሩ ሲሉ ገልጸዋቸዋል፡፡

በመርኃ-ግብሩ ላይ ተካፋይ የሆኑ ምዕመናን በቅዱስ ፓትሪያርኩ ሕልፈተ ሕይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸዋል:: በፍራንክፈርት የምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ መዊዕ ቀሲስ ልሳነወርቅ ውቤም ቅዱስነታቸው ጭምት ደግና አስተዋይ ለሌሎች የኃይማኖት አባቶችም መልካም አርዓያና ጥሩ ምሳሌ የሆኑ ለሁለት ተከፍሎ የቆየው ሲኖዶስ ዳግም አንድነቱ እንዲጠናከር የተጉ አባት ነበሩ ብለዋል::

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ 4ተኛው ፓትርያርክ ዕረፍት የመታሰቢያ ዝግጅት በፍራንክፈርትምስል Endalkachew Fekade/DW

"የቤተክርስቲያን ቀኖና ተጥሶ የሲኖዱሱ የበላይ ጠባቂነት ስልጣናቸውን አጥተው መንበራቸውን ተነጥቀውና ከሃገራቸው ተገፍተው በግፍ ለስደት ከተዳረጉ በኋላ በሞያሌና በኬንያ በአስቸጋሪ ሁኔታና በታላቅ ፈተና ቢያሳልፉም አሳዳጆቻቸውንና በዳዮቻቸውን አንድም ቀን ሳይከሱና ሳይወቅሱ በአርምሞና በዝምታ ራሳቸውን ቀጥተውና ለሌላውም አስተምረው ያለፉ ብጹዕ አባት ናቸው ብለዋል:: ይህንንም እግዚ አብሔር ቆጥሮላቸው ሐምሌ 25 ቀን በዕለተ መርቆሬዎስ ከምድረ አሜሪካ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ ጋር ወደ ኢትዮጵያ በገቡበት ወቅት ሕዝበ ምዕመናኑና ሊቃውንቱና ካህናቱ እጅግ ደማቅ አቀባበል እንዳደረጉላቸው አስታውሰው በአስደናቂ ሁኔታ እረፍታቸውም የካቲት 25 ቀን በሰማዕቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ ዕለት መሆኑ ዝምታቸው ከእግዚአብሄር ጋር እንዳገናኛቸው ምስክር ነው" ሲሉም መልአከ መዊዕ ቀሲስ ልሳነወርቅ ውቤ አብራርተዋል::

በፊት ስማቸው አባ ዘሊባኖስ ፈንታ የሚባሉት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ፣ በጎንደር ክፍለ ሀገር በደብረ ታቦር አውራጃ በአለታ ወረዳ አረጊት ኪዳነ ምሕረት በተባለችው ገዳም ሰበካ፣ ልዩ ስሙ ማር ምድር በ1930 ዓ.ም ከብላታ ፈንታ ተሰማና ከወ/ሮ ለምለም ገሰሰ ነው የተወለዱት:: ዕድሜያቸው ለትምህርት በደረሰ ጊዜ፣ በተወለዱበት ገዳም መሪጌታ ላቀው ከሚባሉ መምህር፣ ንባብና ዳዊት የተማሩ ሲሆን በተለያዩ ገዳማትም ንባብና ዳዊት ምዕራፍና ጾመ ድጓ የተማሩ ተምረዋል:: በጎጃም ዋሸራ፣ በእስቴ ወረዳ አጋጥ ደብረ ጽዮንና ታች ጋይንት ወረዳ በምትገኘው በስመ ጥሩዋ ቤተ ልሔምም፥ የቅኔ፣የምዕራፍ፣ጾመ ድጓና ድጓ፣የአቋቋምና ዝማሬ መዋሥዕት ትምህርታቸውንም ተከታትለው በመምህርነት ከተመረቁ በኋላ በአረጊት ኪዳነ ምሕረት ገዳም ለሰባት ዓመታት ያህል ድጓ አስተምረዋል፡፡ሥርዐተ ምንኵስናን ከመምህርነት ጋራ አጣምሮ ለመያዝ ያላቸው ፍላጎት ከፍ ያለ በመሆኑም በጣና ገዳም ዳጋ እስጢፋኖስ በመግባት ማዕርገ ምንኵስናን  በ1961 ዓ.ም. ተቀብለዋል::ከዚያ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በማቅናት፣ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ በቅዳሴና በማሕሌት እያገለገሉ ትርጓሜ ሐዲሳትንና አቡሻኽርን፣ ዘመናዊ ትምህርታቸውንም በቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ተከታትለዋል፡፡ በተጨማሪም ለመምህራን፣ የተደረገውን የስብከት ዘዴ ኮርስ ለሁለት ዓመታት ተምረው የምስክር ወረቀት መቀበላቸውን የሕይወት ድርሳናቸው ያመለክታል፡፡ አቡነ መርቆሬዎስ በሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ፣ ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም. ከተሾሙት 13 የቤተክርስቲያኒቱ ኤጲስ ቆጶሳት መካከል ለማዕርገ ፕትርክና ከበቁት የዛሬዎቹ ሁለቱ አባቶች አንዱ ናቸው፡፡ በሢመተ ጵጵስና ብቻ ሳይኾን በክህነቱም በተለያየ መቅደስ ማገልገላቸውም በመርሃግብሩ ላይ ተገልጿል::

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ 4ተኛው ፓትርያርክ ዕረፍት የመታሰቢያ ዝግጅት በፍራንክፈርትምስል Endalkachew Fekade/DW

በ1980 ዓ.ም. 4ኛ ፓትርያርክ ሆነው የተሾሙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፤ ወታደራዊው መንግሥት ወድቆ ኢህአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ በደረሰባቸው የፖለቲካ ጫና ነሐሴ 28/1983 ዓ.ም መንበራቸውን ለቀው በአሜሪካን አገር ለበርካታ ዓመታት መሰደዳቸው ይታወሳል ። ለ26 ዓመታት በቆዩባት አሜሪካም በውጭ የነበረውን የቤተክርስቲያኒቱን ሲኖዶስ ሲመሩ ቆይተዋል። ከሃገራዊ ለውጡ በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት የዕርቅ ጥረት ሐምሌ 25/2010 ዓ.ም. ወደ አገራቸው መመለሳቸው የሚታወስ ነው።ቅዱስነታቸው ባለፈው ወር ባጋጠማቸው የጤና እክል ምክንያት በሆስፒታል ተኝተው የሕምና ድጋፍና ክትትል ሲደርጋላቸው ቆይተው ባለፈው የካቲት 25 ቀን 2014 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል።ሥርዓተ ቀብራቸውም የቤተክርስቲያኗ ሥርዓተ ቀኖና በሚያዘው መልኩ መጋቢት 4/2014 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴደራል ተፈጽሟል።

እንዳልካቸው ፈቃደ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW