1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቦረናዋ ሴት እንድትደበደብ የወሰኑና ድርጊቱን የፈጸመው ተቀጡ

ሥዩም ጌቱ
ማክሰኞ፣ ኅዳር 24 2017

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ቦረና ዞን ዋጪሌ ወረዳ ከወራት በፊት በአደባባይ ገበያ ስፍራ እንጨት ላይ በባሏ ታስራ በአሰቃቂ ሁኔታ የተደበደበችው እናት ላይ በደል ያደረሱ ከሰባት እስከ አራት ዓመት እስራት እንዲቀጡ ተወሰነባቸው ።

Hände
ምስል Colourbox

ጥፋተኞች ላይ ውሳኔ ተላለፈ

This browser does not support the audio element.

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ቦረና ዞን ዋጪሌ ወረዳ ከወራት በፊት በአደባባይ ገበያ ስፍራ እንጨት ላይ በባሏ ታስራ በአሰቃቂ ሁኔታ የተደበደበችው እናት ላይ በደል ያደረሱ ከሰባት እስከ አራት ዓመት እስራት እንዲቀጡ ተወሰነባቸው ። መሰል ጥቃት በሁሉም ሴት ልጅ ላይ እንደሚወሰድ ስነልቦናዊ ጥቃት የሚወሰድ እንደመሆኑ ቅጣቱን ከዚህም በላይ በከበድ ተገቢ ሊሆን እንደሚችል ግን የስነጾታ ባለሙያ ይገልጻሉ ።

ጥፋተኞች ላይ የተሰጠው ውሳኔ

ከሁለት ወር በፊት  በቦረና ዞን ዋጪሌ ወረዳ አንዲት የሶስት ልጆች እናት በባሏ አደባባይ እንጨት ላይ ታስራ እንድትደበደብ ምክንያት የሆኑ አራት ሰዎች ላይ የተመሰረተው ክስ አሁን ውሳኔ አግኝቷል፡፡ አራቱ ተከሳሾች ላይ ውሳኔ የተላለፈውም ተከሳሾቹ የግል ጠበቃ አቁመው በፍርድ ሂደቱ እራሳቸውን ስከላከሉ ከቆዩ በኳላ ነው ተብሏል፡፡ በአደባባይ ድብደባውን የፈጸመው የተበዳይዋ ባለቤት አንደኛው ተከሳሽ እና ሴቲቱ እንድትደበደብ ውሳኔውን አስተላልፈዋል የተባሉ ሁለተኛ ተከሳሽ ሽማግሌ በስድስት ዓመት ከአራት ወር እስር እንድቀጡ ስወሰንባቸው፤ በሶስተኛ ተከሳሽነት ስማቸው የተመዘገበ ሌላው ሽማግሌ በተጨማሪነት ተጎጂዋ ከተደበደበችም በኋላ እንድትታሰር በማድረጋቸው በ7 ዓመት ከሁለት ወር እስራት እንድቀጡ ነው የተወሰነው፡፡ በአራተኝነት የተከሰሱት ደግሞ ተጎጂዋ የተደበደበችበት ቀበሌ የጸጥታ እና ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆኖ ሳለ ተጎጂዋ የጠየቀችውን አቤቱታ ችላ በማለትና በጉዳቷም ውስጥ ተባባሪ በመሆን ተከሰው በአራት ዓመት እና አምስት ሺህ 500 ብር መቀጮ ተላልፎበታል፡፡

ተጎጂዋን የመታደግ የመጀመሪያው ጥረት

ጉዳዩ መከሰቱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ ለጉዳዩ አጽእኖት ሰጥተን ስንከታተል ነበር ሲሉ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ መብራቴ ባጫ ተጎጂዋን ከመታደግ ጀምሮ ተገቢው ያሉት ፍትህ እንዲሰጥ ጥረት መደረጉን አስረድተዋል፡፡ "እውነት ነው የተደረገው ነገር የማህበረሰቡን እሴት የሚቃረንና አጠቃላይም የኦሮሞን ህዝብ የማይገልጽ ነው” ያሉት ወ/ሮ መብራቴ ጉዳቱ በአንዲት ግለሰብ ላይ ደረሰ እንደተባለ የባለሙያዎች ቡድን የተፈጸመውን እንዲያጣሩ ወደ ስፍራው መላካቸው አስረድተዋል፡፡ በስፍራው የደረሱ ባለሙያዎችም የጉዳቱን አፈጻጸም በትክክል ከተረዱ በኋላ በቀጥታ ተጎጂዋን ወደ መርዳ ነው የተሄደውም ብለዋል፡፡ "ጉዳቷን ለይተን እንደቢሮ በቂ ህክምና እንድታገኝ ከማድረግ ጀምሮ እንደቢሮው የቻልነውን ተገቢ ድጋፍ አድርገናል” ነው ያሉት፡፡

ብዙውን ጊዜ ሴቶች በጦርነት ወቅትም የአስገድዶ መደፈር ሰለባዎች ናቸው ። ተጎጂዋን የመታደግ የመጀመሪያው ጥረት በደለኞችን በመቅጣት ይጀምራልምስል Nariman El-Mofty/AP/picture alliance

ፍትህን የማረጋገጥ ጥረት ጅማሮ

በመቀጠልም ጥፋቱን የፈፀመው ሰው በሚገባው ደረጃ ወደ ሕግ ቀርቦ ውሳኔ ማግኘት ነበረበት ያሉት የቢሮ ኃላፊዋ፤ የኦሮሚያ ሴቶች ቢሮ ከክልሉ ፍትህ ቢሮ እና ጠቅላይ ፍረድ ቤት ጋር ተቀናጅቶ ችግሩ እስከተፈጠረበት ወረዳ ጠንካራ ክትትል ነበር ነው ያሉት፡፡ በተደረገው ክትትልም ተጎጂዋ ላይ ድብደባ በመፈጸም ጉዳት ካደረሰው ግለሰብ ውጪ ያሉት በዋስ ተለቀው እንደነበርና እንደገባ ወደ እስር እንዲገቡ በማድረግ የሰውና የሃኪም ማስረጃ በማጠናከር ተገቢው ቅጣት አጥፊዎች ላይ እንዲተላለፍ መሆኑም ነው የተነገረው፡፡

"ከአካላዊ ጉዳት በተጨማሪ የደረሰባት ስነልቦናዊ ጉዳት አለ፡፡ ከዚህ በፊት የደረሰባት ጫናም ነበር፡፡ ጉዳት ያደረሰባት ባለቤቷ አብሯት ልጆች ስያሳድግ አልነበረም፡፡ ብቻዋን ነው ልጆች ያሳደገችውና በዚያ ላይ ትልቅ ትንሹ በሚመለከትበት ገቢ ላይ ወጥታ ያ በደል ስደርስባት ነበርና ሁሉም ተገቢ ቅጣት ማግኘት አለበት የሚል አቋም ይዘን ሰራን” ነው ያሉት፡፡ "የህግ ክፍላችን አጥፊዎች በተሸለ ቅጣት እንዲቀጡ ተገቢውን የህግ አንቀጽ ጠቅሰው ክሱን በመከታተል አንድም ተጎጂዋን ፍትህ ለመስጠት ብሎም ሌላው ለማስተማር ተገቢው ቅጣት እንዲተላለፍ ሰርተናልም” ብለው በተለይም በወቅት የተፈጠሩት ተከሳሶችን በዋስ የመልቀቅና በአገር ሽማግሌዎች እርቅ ለመፈጸም የተደረጉ ጥረቶች እንዲከሽፉ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ በዚህም ተከሳሾቹ ከሰባት ዓመት እስከ አራት ዓመት በሚደርስ እስርና የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፍትህን የማረጋገጥ ጥረት ጅማሮምስል alexlmx/Zoonar/picture alliance

የተላለፈው ውሳኔ ተገቢነት ማጠያየቁ

የሕግና ስነጾታ ባለሙያ የሆኑት ፋናዬ ገብረሕይወት ግን በዚህ ውሳኔ ላይ እርካታ የተሰማቸው አይመስልም፡፡ እንደሳቸው ገለጻ  በአንዲት ሴት ላይ የሚፈጸም ጥቃት በሁሉም ሴት ላይ የሚያነጣጥር ተደርጎ ሊወሰድ ስለሚገባ  ቅጣቶቹ ብርቱ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ "በቅርቡ ወደ ማህበራዊ ሚዲያ መጥተው የምንመለከታቸው ውሳኔዎች ህጉ ላይ መሻሻሎች እንደሚያስፈልግ የሚጠይቅ ነው፡፡ ባለው የሕግ ማዕቀፍ እንኳ የሌላና አጥቂዎችን የሚበረታታ ፍርድ ነው የሚሰጠው፡፡ አንዷ ሴት ላይ የሚፈጸም ጉዳትን ተከትሎ የሚሰጥ ውሳኔ  ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ሁሉም ሴቶች ላይ የሚሰጥ ውሳኔን ስለሚታይ እንደማህበረሰብ የሚያሳስብ ነው” ብለውታል ባለሙያዋ፡፡

በዚህ ላይ አስተያየታቸውን ያከሉት የኦሮሚያ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ኃላፊዋ ወ/ሮ መብራቴ ባጫ ግን ካለው ህግ አንጻር የተቻለ ሁሉ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡ "ቅጣቱ ያንሳል የሚል አለ፡፡ ነገር ግን ከአካል ጉደዳትም ባሻገር ስነልቦናዋ ጉዳቷን በማንሳት ነው ይህን ህል እንኳ ቅጣቱ እንዲከብድ ያደረግነው” በማለት ተደክሞበታል ያሉት ጉዳይ አስተማሪ ነው ብለው የሚምኑት ቅጣት ማግኘቱን አስረድተዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW