የቪኦኤና ሌሎች ጣቢያዎች ስርጭት መገታትና መዘዙ
ረቡዕ፣ መጋቢት 10 2017
በዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልዩ ትዕዛዝ ቮኦኤና ራድዮ ፍሪ ዩሮፕ ወይም ራድዮ ሊበርቲ እንዲሁም ራድዮ ፍሪ ኤዥያ የተባሉት ዓለም አቀፍ ጣቢያዎች ስርጭቶች መገታታቸውን «ለአሜሪካን ጠላቶች ትራምፕ ያበረከቱት ትልቅ ስጦታ» ብለውታል የራድዮ ፍሪ ዩሮፕ ወይም ራድዮ ሊበርቲ ጣቢያ ሃላፊ ስቴፋን ካፑስ ። ካፑስ «የኢራን አያቶላዎች ፣የቻይና ኮምኒስት መሪዎች፣ እና የሞስኮ እና ሚንስክ አምባገነኖች ከ57 ዓመታት አገልግሎት በኋላ ራድዮ ፍሪ ዩሮፕ ወይም ራድዮ ሊበርቲ ስርጭቱን ማቆሙ አስደስቷቸዋል ብለዋል። ለጠላቶቻችን ድል ማጎናጸፍ እነሱን ሲያጠናክር አሜሪካንን ደግሞ ያዳክማል» ሲሉ የእርምጃውን መዘዝም ጠቁመዋል።
ባለፈው አርብ ከተላለፈው የዶናልድ ትራምፕ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ በኋላ ከ1000 በላይ የአሜሪካ ድምጽ ሠራተኞች አስገዳጅ አስተዳደራዊ እረፍት እንዲወስዱ ተደርጓል። አንዲት እስያዊት ጋዜጠኛ ለዶቼቬለ እንደተናገረችው ሌሎች ከ500 በላይ ጋዜጠኞች ደግሞ ከስራ ተሰናብተዋል።
«እርምጃው ለፕሬስ ነጻነት ታላቅ ጉዳት ነው» ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን
ከ60 በሚበልጡ ቋንቋዎች የሚሰራጩ ዝግጅቶችን ማቆም በተለይም በሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን ነጻ ዘገባ ማቅረብ በማይቻልባቸው አምባገነን መንግስታት በሚገኙባቸው ሀገራት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ጉዳት ያደርሳል ሲሉ የድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን በምህጻሩ RSF የሰሜንና ደቡብ አሜሪካ ጉዳዮች ክፍል ባልደረባ ማረን ፋልዝግራፍ ተናግረዋል። ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ የትራምፕን እርምጃ «ለፕሬስ ነጻነት ታላቅ ጉዳት » ብለውታል።
«ይህ በእውነት በዓለም ዙሪያ ለፕሬስ ነጻነት ትልቅ ጉዳት ነው። የሚሆነው በእውነቱ በጣም ተለዋዋጭ ነገር ነው። ውሳኔው ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ውጭ ሀገራት ከሚሰራጩ ጣቢያዎች ነጻ መረጃ ያገኙ የነበሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ይጎዳል። »
የዚምባብዌ ምሳሌነት «የማይመች ድምጽ ታፈነ»
ይህ ምን ማለት እንደሆነ ዚምባብዌን በምሳሌነት በመውሰድ ማሳየት ይቻላል። በRSF የፕሬስ ነጻነት ደረጃ ሰንጠረዥ 116 ኛ ደረጃ ላይ በምትገኘው በዚምባብዌ የቴሌኮምኒኬሽን ጠለፋ፣በቴሌቪዥን የተቃዋሚዎችን ስም ማጥፋት እና የነጻ ጋዜጠኞች እስር የተለመደ ነው።
መረጃ ማግኘት አስቸጋሪ በሆነበት በዚምባብዌ ቪኦኤ በእንግሊዘኛ በሾናና እና በንድቤለ ቋንቋዎች ያሰራጫል። አንድ ዚምባብዌያዊ የቀድሞ የቮኦኤ ጋዜጠኛ በሀገርዋ ያለውን ችግርና ከቪኦኤ ስርጭት መቆም በኋላ የዚምባብዌ ባለስልጣናት ያሉትን ለዶቼቬለ ተናግሯል።
«መንግስት የሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙሀን እስካሁን የሰብዓዊ መብቶችና ሙስና የመሳሰሉትን ጉዳዮች ፈጽሞ ቦታ አይሰጧቸውም። የመንግስት ባለስልጣናትና ደጋፊዎቻቸው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሀን(በስርጭቱ መገታት) ደስታቸውን ሲገልጹ ነበር። ይህ ደግሞ ቪኦኤ ምን ያስል አስፈላጊ ሚድያ እንደሆነ የሚያመለክት ነው።»
የትራምፕን ልዩ ትዕዛዝ ለመደገፍ የወጣ መግለጫ ቪ.ኦ.ኤን «አክራሪ የአሜሪካ ድምጽ» በማለት አንቋሾ «ግብር ከፋዮች ከአሁን ወዲያ ለአክራሪ ፕሮፓጋንዳ አይከፍሉም» ብሏል።
የዶቼቬለ ዋና ስራ አስኪያጅ ፔተር ሊምቡርግ የትራምፕ እርምጃ ቻይና እና ሩስያ በክፍተቱ እንዲገቡ የሚጋብዝ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
«ትራምፕ ያደረጉት ፣ነጻነትን ማዳከምና አምባገነንነት ማጠናከር ነው። ይህ የኛም አውሮጳ የሚገኙ ባልደረቦቻችን እስካሁን ያለን ልምድ ነው። ክፍተቱ እንደተፈጠረ ቻይናና ሩስያ ይገባሉ። ይህ ያሳዝናል ።ለዚህም ነው አውሮጳ በአስቸኳይ አንድ ነገር ማድረግ አለበት ብዬ የማምነው።»
ዴቪድ ኤል /ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ