የቪኦኤ መዘጋት በቀድሞ የጣቢያው አንጋፋ ባልደረቦች እይታ
ሐሙስ፣ መጋቢት 18 2017
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካንን የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ እንዲፈርስ ማዘዛቸውን ተከትሎ ከአለም አቀፍ ስርጭቶች ውስጥ አንዱ የሆነው የአሜሪካ ድምጽ (VOA) መዘጋቱ እጅግ እንዳሳዘናቸው በጣቢያው ለረጅም አመታት የሰሩ የቀድሞ ባልደረቦች ግለጹ። አንጋፋወቹ የቀድሞ ጋዜጠኞች ት ዝታ በላቸው፣ አዲሱ አበበና ሰለሞን አባተ የጣብያው መዘጋት የአሜሪካ ድምጽን እንደ አንድ ታማኝ የመረጃ ምንጭ ለሚጠቀሙት አድማጮቹ ከፍተኛ ጉዳት መሆኑን ገልጸዋል። የጣብያውን የወደፊት እጣ ፈንታ በተመለከተም የተለያየ ተስፋና ምኞታቸውን አጋርተውናል።
ይሄን የጣብያውን መዘጋት መራር እውነት እንኳን ለመቀበል፣ ለማመን የተቸገሩት ደግሞ እድሜ ዘመናቸውን፣ ሙያ ክህሎታቸውን፣ ነፍስ መገዛታቸውን ለሬድዩ የሰጡ ያነጋገርኳቸው አንጋፋ የጣብያው የቀድሞ ጋዜጠኞች ናቸው። በጡረታ እስክትለቅ ድረስ ለአራት አስርተ አመታት የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ላይ ከጋዜጠኝነት እስከ ሃላፊነት ያገለገለችው አንጋፋዋ ጋዜጠኛ ትዝታ በላቸው በጣብያው መዘጋት የተሰማትን ሃዘን ገልጻለች።የዶናልድ ትራምፕን ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮን ከስርጭት አስወጣ
ይሄን አይነት መሰረታዊ የሚባል የስራ ቅነሳና ለውጥ በሁሉም አቅጣጫ በትራምፕ አስተዳደር እየተሰወሰደ መሆኑን ያስታወሰችው ትዝታ ፕሬዝዳንቱ ለጣብያው ካላቸው አሉታዊ አመለካከት አንጻር ብዙም የሚገርም ውሳኔ አለመሆኑን አስታውሳለች። ጣብያው ለአድማጮች የእውነት ምንጭ ከመሆኑ አንጻር መዘጋቱ በአድማጩ ላይ ያለው ጉዳት ሰፊ መሆኑን ነው የጠቆመችው።
የትራምፕ አስተዳደር በዲሞክራሲም ሆነ በመገናኛ ብዙሃን መብት ላይ የሚከተለው ፖሊሲ ከዚህ ቀደም የድሞክራትም ሆነ የሪፐብሊካን ፕሬዝዳንቶች ከሚያራምዱት የተለየ መሆኑን ያወሳችው ጋዜጠኛ ትዝታ፣ እንደ ሲኤንኤን ያሉ ትልልቅ ጣብያወችንም ጭምር ዘወትር ሲያብጠለጥሉ፣ ሲያዋክቡና ጫና ለመፍጠር ሲሞክሩ የሚታዩ መሆናቸውንም አውስታለች ። እናም ትዝታ በላቸው፣ አሜሪካ ውስጥ አሁን ያለው ሁነት በተለይ ከዲሞክራሲና ከህግ የበላይነት አንጻር የተጋረደው ጭለማ ይገፍ ዘንድ ምኞቷ ነው።
የአሜሪካ ድምጽ ሲነሳ አብሮ የሚነሳው ከ30 አመታት በላይ ድምጽና ስብዕናው ከአሜሪካ ድምጽ ጋር የተሰናሰለው ተወዳጁና አንጋፋው ጋዜጠኛ አዲሱ አበበ የአሜሪካ ድምጽ መታውቂያዬ መለያዬ ነው ይላል፣ እናም መዘጋቱን ሲሰማ እሱ እራሱ ስራ እንዳጣ ያህል ነው የቆጠረው።
ውስጡ ከማዘኑ ባሻገር ደግሞ ጣብያው ለኢትዮጵያ አድማጮቹ እውነተኛ የዜና ምንጭ ሆኖ ዘመናትን ከመሻገሩ አንጻር አሁን መዘጋቱ በመረጃ ፍሰት ላይ የራሱን አሉታዊ ጫና መፍጠሩ አይቀርም ብሏል። የቪኦኤና ሌሎች ጣቢያዎች ስርጭት መገታትና መዘዙ
ጋዜጠኛ አዲሱ ይሄው የትራምፕ አስተዳደር ውሳኔ አሜሪካ ከሌሎች እለይበታለሁ በምትለው ዲሞክራሲ የመናገር ነጻነት እና የህግ የበላይነት ጋ ተያይዞ የነበራትን አለማቀፍ ተቀባይነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ እንደሆነም ጠቁሟል። ሃገሪቷ እንደ የአሜሪካ ድምጽን የመሳሰሉ አለም አቀፍ ስርጭቶችን የጀመረችውና እስካሁንም የዘለቀችው የራሷን ፖሊሲና እሴት በአለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅና ተጽዕኖንም ለመፍጠር ጭምር መሆኑ መዘንጋት እንደሌለበት የገለጸው ጋዜጠኛ አዲሱ አበበ የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮም ተዘግቶ ይቀራል የሚል እምነት እንደሌለው ጠቁሟል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም የመገናኛ ብዙሃን ዘርፎች ለረጅም አመታት ያገለገለውና በአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮም ከ16 አመታት በላይ በተለያዩ ክፍሎችና ሃላፊነቶች አገልግሎ ጣብያው ከመዘጋቱ በፊት የለቀቀው አንጋፋው ጋዜጠኛ ሰለሞን አባተም ጣብያው በመዘጋቱ ማዘኑን አልሸሸገም። አዲስ ፕሬዝደንት፣ አዲስ ፓርቲና አዲስ ሃሳብ መምጣቱ ሊፈጠር የሚችል ክስተት መሆኑን የገለጸው ሰለሞን፣ የአሜሪካ ድምጽ ከአድማጮቹ የመረጃ ምንጭ ከመሆኑ ባልተናነሰ የአሜሪካ አንደበት ሆኖ የሚያገለግል መሆኑን አስታውሷል።
የሚሰጠው አስተያየት እንደ አሜሪካ ድምጽ ሳይሆን እንድ አንድ ውጪ እንዳለ ግለሰብ መሆኑን የገለጸው ጋዜጠኛ ሰለሞን አባተ የአሜሪካ ድምጽ ከሚሰጠው አገልግሎት አንጻር ብዙ መንገጫገጮች ያሉበት፣ ውስጡ ብዙ ሊፈተሽና ሊስተካከል የሚገባቸው ስንክሳሮችን የተሸከመ መሆኑን ጠቁሟል።
አበበ ፈለቀ
ኂሩት መለሰ
ፀሐይ ጫኔ