የተመድ ጠቅላላ ጉባኤና ፕሬዝደንት ትራምፕ
ሐሙስ፣ መስከረም 15 2018
በጉባኤው ንግግር ያደረጉ አብዛኞቹ ስሜት የሚነኩ እንደነበሩ ቢገለጽም የተመድ ዋና ጽሕፈት ቤት መቀመጫ የሆነችው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ግን ለአንድ ሰዓት ፈጀ በተባለው ንግግራቸው የግል ቅሬታ፤ አልፈውም ዘለፋና ትችት መሰንዘራቸው ዳግም መነጋገሪያ አድርጓቸዋል።
ትራምፕ ምን አጋጠማቸው?
ትራምፕ ከግል ወቀሳቸው በተጨማሪም የመንግሥታቱ ድርጅት በጋራ የሚያሳልፋቸውን የአየር ንብረት ለውጥም ሆነ የስደተኞች ጉዳይን የሚመለከቱ ፖሊሲዎችን በአደባባይ ሲያጣጥሉ ተደምጠዋል።
በዚህም የተመድን ጨምረው የአውሮጳ መሪዎችን ሳይምሩ፤ የስደተኝነት ፖሊሲ እና ጽዱ የኃይል ምንጭ አጠቃቀምንም ሳይቀር ሲያጣጥሉ ተደምጠዋል።
ከመነሻው ንግግራቸውን የሚያነቡበት ቴሌፕሮምተር እንዳይሠራ ተደርጓል ሲሉ የወቀሱት ትራምፕ እሳቸውና ባለቤታቸው ሜላኒያ ትራምፕ ወደ ስብሰባው ለመምጣት በሚንቀሳቀሰው ደረጃ ላይ ሲወጡ አገልግሎቱ መቋረጡንም በአደባባይ አንስተው ተችተዋል። ለሌሎች መሪዎች የሠራው ቴሌፕሮምተር ለእሳቸው መበላሸቱን፤ የኤሌክትሪኩ ደረጃ ከግማሹ ሲደርሱ በመቆሙ ከነባለቤታቸው ደረጃውን ለመውጣት መገደዳቸውን የእሳቸው እና የተመድ ግንኙነት የመበላሸቱ ማሳያም አድርገው አቅርበዋል።
እርግጥነው እሳቸው ይህን ቢሉም በእሳቸው ምክንያት መንገድ ተዘግቶ የሁለት የሃገራት መሪዎች መቸገራቸው ሌላው መነጋገሪያ ሆኗል።
ትራምፕና የተመድ ግንኙነት
የትራምፕ ለተመድ ጉባኤ ያሰሙት ቅሬታ በዚህ አላበቃም ከ20 ዓመታት በፊት የቤት ግንባታ ሥራ የተሠማራ ኩባንያቸው የተመድን ሕንጻ አሳምሮ ለማደስ ጠይቆ እንዳልተፈቀደለትም አንስተው የቆየ ቁርሿቸውን ለአደባባይ አብቅተዋል።
የአውሮጳ ሃገራት እሳቸው በአሜሪካ ተግባራዊ ያደረጉትን ፖሊሲ እንዲቀዱና ድንበራቸውን እንዲዘጉ እንዲሁም ስደተኞችን እንዲያባርሩም ሲመክሩ ተደምጠዋል። ስደተኞችን በተመለከተው ንግግራቸውም በተለይ ብሪታንያን አንስተው ጠንካራ ትችት ሰንዝረዋል። ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ አንስተው ሰባት ጦርነቶችን ማስቆም እንደቻሉ የተናገሩት ዶናልድ ትራምፕ ለዚህ ሥራቸውን ከተመድ ሌላው ቀርቶ ስልክ እንኳ አልተደወለልኝም በማለትም ድርጅቱን አጥበቀው ተችተዋል።
የተመድ ከተቋቋመ ዘንድሮ 80ኛ ዓመቱን ያዘ። የመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤና የትራምፕን ገጠመኝና ንግግር በተመለከተ ሸዋዬ ለገሠ የዋሽንግተን ዲሲ ዘጋቢያችን አበበ በፈለቀን በስልክ አነጋግራለች።
ሸዋዬ ለገሠ/አበበ በፈለቀ
ታምራት ዲንሳ