1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተስተጓጎለዉ የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ምርት  

ማክሰኞ፣ የካቲት 8 2014

ግዙፉ የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ለአንድ ሳምንት ያህል ስራ ማቆሙን የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን አረጋገጠ፡፡ የስኳር ኮርፖሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ረታ ደመቀ በተለይም ለዶይቼ ቬለ እንደገለፁት ፋብሪካው ስራውን ያቆመው ከየካቲት 03 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡

Kuba Zuckerrohrfeld
ምስል picture alliance/Arco Images GmbH

ፋብሪካው ስራ ለማቆም የተገደደዉ በነዳጅ ማመላለሻ ላይ በደረሰ የደህንነት ችግር ነዉ

This browser does not support the audio element.

ግዙፉ የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ለአንድ ሳምንት ያህል ስራ ማቆሙን የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን አረጋገጠ፡፡ የስኳር ኮርፖሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ረታ ደመቀ በተለይም ለዶይቼ ቬለ እንደገለፁት ፋብሪካው ስራውን ያቆመው ከየካቲት 03 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አባይ ጮመን ወረዳ ለሚገኘው ለፋብሪካው ስራ ማቆምም አከባቢው ላይ የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮች ነዳጅ ለማጓጓዝ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱ ዋናው ምክኒያት ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ ቀደምም በ100 ሄክታር ገደማ የፋብሪካው ሸንኮራ አገዳ ማምረቻ ስፍራ እና ቢያንስ ሶስት የፋብሪካው ትራክተሮች ላይ የቃጠሎ ጉዳት መድረሱ ተነግሯል፡፡

በአገሪቱ ትልቁ የስኳር ፋብሪካ የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ የማምረት ስራውን ያቆመው ባለፈው ሳምንት አጋማሽ እሮብ የካታት 3 ቀን 2014 ዓ.ም. በጎርጎሳውያኑ ፌብሯሪ 9 ነው፡፡ የጸጥታ ችግሮች ደጋግሞ በሚያንዣብብበት ኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ከአዲስ አበባ በሰሜን-ምዕራብ 350 ኪ.ሜ. ገደማ ላይ የሚገኘው ፋብሪካው ለሳምንት ያህል ስራ ለማቆም ያስገደደውም የነዳጅ ማጓጓዣ መንገዶች ላይ ያለው የደህንነት ችግሮች መሆኑን የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ረታ ደመቀ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡

በዓመት እስከ 270,000 ቶን ስኳር የማምረት አቅም ያለው ግዙፉ የስኳር ፋብሪካ ስራውን እንዲያቆም ምክኒያት ባይሆንም ከዚህ ቀደም የሸንኮሮ አገዳ እና ውስን ትራክተሮች ላይ ቃጠሎ መድረሱን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ጉዳቱን ያደረሱ አካላት ማንነት በጸጥታ ኃይሎች ይገለጽ እንደሆነ እንጂ ኮርፖሬሽኑ በዚህ ላይ እርግጠኛ ሆኖ መናገር እንደማይችልም አክለዋል፡፡ ትናንት በፋብሪካው ስፍራ የደረሰው በቂ ያሉት ነዳጅ ፋብሪካውን ወደ ስራው እንሚመልሰውም ተናግረዋል፡፡

አቶ ረታን ከፋብሪካው ውጪም ቢሆን በአከባቢው የሚያጋጥሙ የፀጥታ ችግሮች በፋብሪካው ህልውና ላይ ሊያሳርፍ የሚችለውን አደጋ ጠይቀናቸዋል፡፡ የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ በቀለ ደቻሳ እንደሚሉት ግን የነዳጅ ማመላለስ ስራው የተቋረጠው በጸጥታ ችግር አይደለም ባይ ናቸው፡፡ 

“ችግሩ የፀጥታ ሳይሆን የግብዓት ችግር ነበር፡፡ ለፋብሪካው ነዳጅ በሚያቀርበው ኖክ እና በትራንስፖርት አጓጓዦች መካከል በተፈጠረ ችግር ነው በቂ ነዳጅ በሰዓት ባለመድረሱ ፋብሪካው ስራውን ያቆመው፡፡ ይሄ ደግሞ በተደረገው ውይይት ተፈቶ አሁን ነዳጆም ፋብሪካው ጋ ደርሷል፡፡ እንደ ዞኑ የፀጥታ ችግር ይኖራል፡፡ ግን ለፋብሪካው ስራ ማቆም ምክኒያት አልሆነም፡፡ ህይወቱን በፋብሪካው ላይ የመሰረተ ማህበረሰብ ከ13 ሺህ በላይ ነው፡፡ ህዝቡ ተደራጅተው ፋብሪካውን ከጸጥታ ኃይል ጋር እየጠበቀ ነው፡፡ ባለፈው የሸንኮራ አገዳ እና ተሸካርካሪዎችን የማቃጠል ሙከሪያ ከሽፏል፡፡ አሁን በፋብሪካው ዙሪያ ምንም ችግር የለም፡፡” ከዚህ ቀደም በውስን የፋብሪካው ሸንኮራ አገዳ እና ትራክተሮች ላይ የማቃጠል አደጋ ያደረሱት ግን “ሸነ” ያሉት በአከባቢው በሽምቅ ውጊያ የሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ጦር መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በዞኑ የፀጥታ ችግሮች መኖራቸውን ያልሸሸጉት ኃላፊው ባሁን ወቅት ግን ለፋብሪካው ስራ መደናቀፍ የሚያበቃ የፀጥታ ችግር አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ 

በኦሮሚያ በተለያዩ አከባቢዎች የሚንቀሳቀሰውና በአገሪቱ ምክር ቤት “ሸነ” በሚል ስም በሽብርተኝነት የተፈረጀውና እራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ጦር” ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ ከተለያዩ የፀጥታ መደፍረሶች ጋር ስሙ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡

 

ስዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW