1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተስፋ ጭላንጭል የታየበት የሰላሌ ሰላም ዳግም መደፍረስ

ሥዩም ጌቱ
ዓርብ፣ ጥቅምት 29 2017

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ዳግም የተቀሰቀሰዉ አለመረጋጋት እንዳሳሰባቸዉ ነዋሪዎች አመለከቱ፡፡ ባለፈው ነሐሴ ህዝቡ አደባባይ ወጥቶ አካባቢዉ ላይ የሚካሄደዉ ግጭት አማሮኛል ሲል አደባባይ ከወጣ በኃላ መንግሥት በወሰደዉ እርምጃ የጸጥታ እጦት መዘዞች ቀንሰዉ እንደነበር እና አሁን ግን የፀጥታ ስጋት ዳግም መቀስቀሱን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ፎቶ ማህደር፤ ሰላሌ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን
ፎቶ ማህደር፤ ሰላሌ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞንምስል Seyoum Getu/DW

የተስፋ ጭላንጭል የታየበት የሰላሌ ሰላም ዳግም መደፍረስ

This browser does not support the audio element.

የተስፋ ጭላንጭል ታይቶበት የነበረው የሰላሌ ሰላም ዳግም መደፍረስ

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከሰሞኑ ዳግም እየደፈረሰ በመጣው የአከባቢው አለመረጋጋት ስጋት እንዳሳሰባቸዉ የአከባቢው ነዋሪዎች አመለከቱ፡፡ ባለፈው ነሃሴ ወር መጀመሪያ ህዝቡ አደባባይ ወጥቶ እየተካሄደ ያለው ግጭት አማሮኛል በማለት አደባባይ ከወጣበትና መንግስት የስልክ አገልግሎትን ሙሉ በሙሉ ዘግቶ ወታደራዊ ኦፕሬሽን ከወሰደ በኋላ የጸጥታ እጦት መዘዞች ቀንሶ እንደነበር ያመለከቱት ነዋሪዎች አሁን ላይ ነባሩ ስጋት ዳግም መመለሱን ነው ያስረዱት፡፡ በርግጥ በአከባቢው እገታ እና ተያያዥ አፈናዎችጋብ ባለባቸው ወራት በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች መካከል የሚደረግ ግጭት  መቋጫ ያገኘበት ወቅት አለመኖን ነዋሪዎች በዘላቂነት ከስጋት ነጻ የሆኑበት ወቅት እንዳልነበርም ተናግረዋል፡፡

እገታና አፈና ጋብ ያለባቸው ወቅቶች

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የደገም እና ደብረሊባኖስ ወረዳዎች ነዋሪዎች ከጥቂት ሳምንታት በፊት አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ ሲሰጡ የተስፋና እፎይታ ድምጾች ተሰምተው ነበር፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ በተለይም ከነሃሴ ወር ወዲህ የእገታ ወንጀሎች በእጅጉ ቀንሰው ነዋሪዎቹም በሰላም ተኝተው ማደር ጀምረው ነበር፡፡

ለደህንነታቸወ ሲባል ስማቸውና ማንነታቸው እንዳይገለጽ ጠይቀው አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪዎቹ “ሰው እያፈኑ ገንዘብ የማስከፈሉ ትግባር አሁን አሁን ትንሽ ተገቷል፡፡ ይሄን ለውጥ ያየነው ፈረስ ለጉመን ነሐሴ 11 አከባቢ ህዝቡ ሁሉ ወጥቶ ምሬታችንን ገልጸን አቤት ካልን ወዲህ ነው፡፡ ከእገታ አንጻር ሌላው ደህና ሆኗል” ሲሉ መናገራቸዉ ይታወቃል። …. ከዞኑ ደብረልባኖስ ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላው ነዋሪም “አሁን እንደ ከዚህ በፊቱ ምንም እንቅስቃሴ የለም፡፡ ዝምታ የሰፈነ ይመስላል፡፡ ሰውን እንደልቡ ገቢያ መውጣትን ጨምሮ ያለሀሳብ እየተኛ እንደውም ምሽትም እስከ ሦስት ሰዓት ድረስ መንቀሳቀስ ተችሏል እንደልብ፡፡ አነስተኛ ስጋቶች የምንሰማው ኩዩ እና ደገም ወረዳዎች አከባቢ ነው፡፡ አሁን ደህና ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ፎቶ ማህደር፤ ሰላሌ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞንምስል Seyoum Getu/DW

ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ዳግም የደፈረሰው ሰላም

ነዋሪዎች ተስፋ ያደረጉትና ወደ ነባሩ ሰላማዊ እንቅስቃሴያቸው የመለሳቸው የመሰለው ሁኔታ ግን ከአንድ ወር ከሁለት ሳምንት በላይ ያሻገራቸው አልሆነም፡፡ ባለፈው ሳምንት በተለይም በዞኑ ወጫሌ ወረዳን ጨምሮ በተለያዩ አከነባቢዎች ታውኳል ባሉት የጸጥታ መደፍረስ የነዋሪዎች ስጋት ዳግም አገርሽቷል፡፡ ስሜ ይቆይ ብለው አስተያየታቸውን የሰጡን የደብረጽጌ ነዋሪ ስጋታቸውን ከገለጹ የዞኑ ነዋሪ መካከል ናቸው፡፡ “እንደው አሁን ደግሞ መላቅጡ ጠፍቷል፡፡ ለአንድ ወር ግድም ፍጹም ሰላም ተመልሶልን ሌሊቱን በሙሉ እንደልብ መተኛት ጀምረን ነበር፡፡ አሁን ግን በዚህም በዚያም ሰው እያለቀ ስጋቱ ተመልሶብናል፡፡ አጎራባች ወረዳችን ወጫሌ ላይ ባለፈው ሳምንት ዓርብ የበርካታ ሰው እልቂትን ያስከተለው ግጭት የጸጥታው ችግር ማገርሸትን ያሳየ ነው፡፡ በዚያ ያለቀው ሰው ብዙ ነው፡፡ ተሽከርካሪዎችም ተቃጥለዋል፡፡ እርቅ እንዲወርድ ሰላምም እንዲሰፍን ጠይቀን ነበር። ግን ሰሚ አጣን። አሁን ከፈጣሪ ብቻ መፍትሄውን እንጠብቃለን” ብለዋል፡፡

በዳግም ስጋቱ መፈናቀሎች

አስተያየት ሰጪ የመረጃ ምንጫችን እንዳሉት ባለፈው ሳምንት ባገረሸው ግጭት፤ በዚህ በአዝመራ ወቅት ሰዎች ከገጠር እየተፈናቀሉ መረጋጋትንም እያጡ ነው፡፡ “በወጫሌ ወረዳ ጉምብቹ የሚባል ከሙከጡሪ በስተምዕራብ የሚገኝ አከባቢ ሰው ከገጠር ተፈናቅለዋል፡፡ በተለይም ይህ ወደ ጉሌሌ ወረዳ በሚወስደው መስመር ላይ ጉዳዩ ይከፋል፡፡ ተፋላሚዎች ታግሰው ችግሮቹን በሰላም እልባት ቢፈልጉለትና ከማህበረሰቡም ጋር ቢወያዩ ለኛ ምርጫችን ነው፡፡በእልቂት ኪሳራ እንጂ ምንም አይገኝም፡፡አሁን ባለፈው ዓርብ ለቅዳሜ አጥቢያ እኛ ጋር እንደ ዝናብ ከግራም ከቀኝም በሚዘንብ ጥይት እንዴት እንሆናለን ብለን ፈጣሪን እየተማጸን ነዉ ያደርነዉ፡፡ በዚህም ጀግና እና አዋቂዎች እናጣለን። የእኛ ነገር የገደለ ወንድምሽ-የሞተው ባልሽ- መከራሽም በዝቶ ከቤትሽ አልወጣ እንደሚባለው ነው” ሲሉ የግጭቱን ውስብስብ ተጽእኖ አስረድተዋል።

በዞኑ የያያ ጉሌሌ ወረዳ ነዋሪም ተመሳሳይ ስጋታቸውን ነው ያጋሩን፡፡ “አሁን ሰው ከትንንሽ ከተሞች ወደ ገጠር ለአጭር ሰዓታት ለቅሶ ለመድረስ እንኳ የምንቀሳቀሰው በትልቅ ስጋት ነው፡፡ ሰላም የተረጋጋ የመሰለው ለአጭር ጊዜ ነው፡፡ ሰው ከከተማ ገጠር ሆዶ ማደር የማይታሰብ ነው” ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንምስል Solomon Muche/DW

ዶይቼ ቬለ በነዋሪዎቹ አዲስ ስጋት ላይ ከባለስልጣናት በተለይም ከዞኑ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ኃላፊ አቶ ሰለሞን እና ከኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልሰመረም፡፡

ባለፈው ሳምንት እንደዘገብነው፤ በሰሜን ሸዋ ዞን ወጫሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪን ጨምሮ በርካቶች የተገደሉበት ጥቃት የ48 ሰዎች ህይወት መቅጠፉን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለፈረሰንሳዩ የዜና ወኪል (AFP) ሲያረጋግጥ፤ ጉዳዩ በምርመራ ሂደት ላይ ነው ብሏል፡፡ በጥቃቱ መንግስት ሸነ ያለውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ኃላፊነት መውሰዱም አይዘነጋም፡፡ በሰሜን ሸዋ ዞን በተለይም ከአዲስ አበባ ወደ አማራ ክልል በሚወስደው መንገድ ላይ እንዲሁም በመላው ዞኑ የሸገር ከተማን እስከሚያዋስኑ ስፍራዎች የእገታ ተግባራቱ በርካቶችን ማማረሩ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW