የተባባሰዉ የዲሞክራቲክ ኮንጎ ግጭትና ምክንያቱ
ቅዳሜ፣ ጥር 24 2017
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እየተባባሰ የመጣው ኃይል የቀላቀለ ብጥብጥ በሃገሪቱ አለመረጋጋት እና ሰፊ ግጭት እንዳያስከትል ስጋት አሳድሯል። በሩዋንዳ የሚደገፉት M 23 ተብለው የሚታወቁት አማጺ ቡድኖች፤ የምሥራቃዊ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ቁልፍ ከተማ የሆነችውን ጎማን፤ በያዝነዉ ሳምንት ሰኞ ጥር 19 ቀን 2017 ዓም ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠራቸውን ተከትሎ፤ በዴሞክራቲክ ኮንጎ አለመረጋጋት እና ሁከት ሰፍኗል።
በዋና ከተማዋ ኪንሻሳ ተቃዋሚዎች በሩዋንዳ፣ ፈረንሳይ፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና ኬኒያ ኤምባሲዎች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል። ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች መኖሪያ የሆነችው ጎማ፤ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ እና አስተዳደር ውስጥ ወሳኝ ሚና ትጫወታለች።
በዚህ ሳምንት መጀመርያ፤ ምስራቃዊ ጎማ ከተማ ላይ ተባብሶ በቀጠለዉ ብጥብጥ፤ የከተማው ከፍተኛ የእስር ቤት ተሰብሮ እስረኞች፤ በመዉጣታቸዉ ግርግሩን ይበልጥ አባባሶታል። በእስር ላይ የነበሩ ከ 4,000 በላይ ታራሚዎች፤ እስር ቤቱን ለቀዉ ሲወጡ፤ የከተማዋ ነዋሪዎች ለደህንነታቸው ሲሉ ፤መኖርያ ቤት ቆልፈዉ እንዲሸሸጉ እና በፍርሃት ቆፈን እንዲዋጡ ዳርጓቸዋል።
በምሥራቅ ኮንጎ በመንግሥት ኃይሎች እና በ M-23 ቡድን ታጣቂዎች ውጊያው በመቀጠሉ የእርዳታ ድርጅቶች በደህንነት ስጋት ምክንያት ሠራተኞቻቸው ሁሉ ከጎማ በማስወጣት ላይ መሆናቸው ተዘግቦ ነበር። የእርዳታ ሰራተኞ ከተማዋን መልቀቅ የጀመሩት
በሩዋንዳ የሚደገፈው M 23 ታጣቂ ቡድን ትልቋን የምሥራቃዊ ኮንጎ ከተማ ጎማን ተቆጣጥረናል ማለታቸዉን ተከትሎ ነበር።
በምስራቃዊ ኮንጎ የሚታየዉ ግጭት ምክንያት ምንድን ነው?
የዲሞክራቲክ ኮንጎ ብረታ ብረት እና ቆርቆሮ ጨምሮ እንደ ወርቅን እና ኮልታን የመሳሰሉ ተንቀሳቃሽ ስልኮች እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ባትሪዎችን ለማምረት አስፈላጊ የተባሉ ማዕድኖች የሚገኙባት በተፈጥሮ ሃብት የበለፀገች አገር ናት።
የታጠቁ ቡድኖች፤ ሀገር ውስጥ ሚሊሻዎች እንዲሁም የውጭ ተዋናዮች፤ የግዛቱን ሀብት ለመቆጣጠር ሲፋለሙ ደም መፋሰስን ቀስቅሰዋል። በዚህም ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በግጭት ስትታመስ ከ1994ቱ የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት እልቂት ጀምሮ ከ30 ዓመታት በላይ ቆይታለች። የምስራቅ አፍሪቃ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ ጄን ባፕቲስት እንደሚሉት የ M 23 አማጽያን ጉዳይ መቼም መፍትሄ የሚያገኝ አይደለም።
«M 23 አማፅያን እንዲዋጉ ያደረጋቸው ህጋዊ ምክንያቶች አሏቸዉ። ቦታዉ የገዛ ሀገራቸው አካል ነው፣ በሀገራቸው የትኛውንም አካባቢ ተዋግተዉ የመያዝ መብት አላቸዉ። ለመዋጋት ወደ ውጭ ሀገር ሄደው አያውቁም። ስለዚህ ዓለም አቀፉ መፍትሄ አያስፈልግም። ህብረተሰቡ ግን ያወግዛቸዋል፤ ምክንያቱ ደግሞ ከመንግሥት ጋር ችግር ዉስጥ ናቸዉ። እና ይህ መቼም መፍትሄ አያገኝም።»
ለዓመታቶች በዘለቀዉ በዚህ ኃይል የቀላቀለ ግጭት፤ የሀገሪቱ ዜጎች ለመከራ ተዳርገዋል። ከ 7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። በሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ዘገባ መሰረት ጅምላ እልቂቶች ፣ ጾታዊ ጥቃቶች፤ ህጻናትን ለዉትድርና መመልመልን ጨምሮ፤ ብዙ ዘግናኝ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ ቆይተዋል።
የወቅቱ ቀውስ ዋና መነሻ፤ በቱትሲ ጎሳዎች የሚመራው የM 23 አማፂ ቡድን እንደገና የኃይል እርምጃዉን በመጀመሩ ነው። በጎርጎረሳዊዉ 2012 ዓ.ም፤ ይህ ታጣቂ ቡድን አካባቢዉን ተቆጣጥሮ፤ ስልጣን በመያዝ ጎማ ከተማን ቢቆጣጠርም፤ በጎርጎረሳዊዉ 2013 ዓ.ም በኮንጎ ጦር እና በተመድ ሃይል መባረሩ አይዘነጋም። M 23 በጎርጎረሳዉያኑ 2021 በምስራቅ ኮንጎ የሚገኙትን የቱትሲ ጎሳ አባላት ከመድልዎ እና ከጥቃት እጠብቃለሁ ሲል ዳግም ብረት አነሳ።
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መዲና ኪንሻሳ ላይ የሚገኙት መሪዎች፤ ቡድኑ የሀገሪቱን የበለፀገ የማዕድን ሀብት በተለይ ደግሞ ሩዋንዳ እና ዩጋንዳ አዋሳኝ ግዛቶች ላይ ያለዉን ለመቆጣጠር ለሚጥሩ፤ የውጭ ኃይሎች፤ ተላላኪ ብቻ ነው፤ ሲሉ ይገልጻሉ።
በአሁኑ ወቅት በኮንጎ ምሥራቃዊ ክፍል፤ እግራቸዉን ለመትከል የሚፈልጉ፤ ከ100 በላይ የተለያዩ የታጠቁ ቡድኖች ይገኛሉ። በጎርጎረሳዉያኑ 2013 ናይሮቢ ኬንያ ላይ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በM 23 አማፂያን መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነትን ጨምሮ፤ ቀጣናውን ለማረጋጋት የተደረገው ጥረት በተደጋጋሚ መክሸፉ የሚታወቅ ነዉ።
የሩዋንዳ ሚና ምንድን ነዉ ?
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኅይል የቀላቀለ ግጭት፤ የሩዋንዳ ተሳትፎ ዓለም አቀፍ የውጥረት ነጥብ ነው። የሩዋንዳ መሪዎች M 23 አማፂያንን እንደማይደግፉ ደጋግመው ቢናገሩም፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለሙያዎች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እንደገለፁት፤ ከጎርጎረሳዉያኑ 2012 ዓ.ም ጀምሮ ሩዋንዳ M 23ን በሎጅስቲክስ፣ በጦር መሳሪያ አቅርቦት እና ተዋጊዎችንም ጭምር በመስጠት እንደምትደግፍ በግልፅ ተናግረዋል።
የእዚህ ታሪክ ምንጭ በከፊል በጎርጎረሳዉያኑ 1994፤ 800,000 ሰዎች የተገደሉበት እና የቱትሲ ጎሳ አባላት በሁቱ ጎሳዎች የተገደሉበት የሩዋንዳዉ የዘር ጭፍጨፋ ነዉ። የሩዋንዳዉ የዘር ጭፍጨፋ በፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ከቆመ በኋላ፤ በርካታ የሁቱ ሚሊሽያዎች ከሩዋንዳ ወደ ዲሞክራቲክ ኮንጎ መግባታቸዉ ተመልክቷል። የካጋሜ አስተዳደር፤ በሩዋንዳ በተካሄደው የዘር ማጥፋት ወንጀል የተሳተፉ አንዳንድ የሁቱ ቡድን አባላት፤ በሩዋንዳ ደህንነት ላይ ቀጥተኛ ስጋት ፈጥረዋል ሲል ይገልጻል።
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግስት በበኩሉ፤ M 23 በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች የተፈጥሮ ሀብቱን ለመዝረፍ ሩዋንዳ ግጭቱን እንደ ሽፋን ተጠቅማለች ሲል ይከሳል። በዓለም አቀፍ የስትራቴጂ ጥናት ተቋም የአፍሪቃ ቀንድ ዳይሬክተር ዶ/ር ሀሰን ካነንጄ፤ ለ DW እንደተናገሩት፤ ሩዋንዳ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን በቅርቡ በሰላም ለቃ ትወጣለች ማለቱ ዘበት ነዉ።
«ሩዋንዳ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ ነበረች፤ ሁልጊዜም ትኖራለች። ሀገሪቱ በማዕድኑ ጉዳይ ላይ ብቻ ሳይሆን፤ ለሩዋንዳ ስልታዊ እና ብሄራዊ ጥቅምም አላት" ሲሉ ለDW ተናግረዋል። "ነገር ግን ማዕድኖቹ እሳቱን ያቀጣጥላሉ" ብለዋል። ካነንጄ እንደተናገሩት፤ ተፎካካሪ አማፂ ቡድኖች ተጨማሪ “የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ክፍሎች ለመያዝ” ምክንያት ይሰጣሉ።»
የኮንጎ ግጭት ይስፋፋ ይሆን?
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሩዋንዳ መካከል የነበረዉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፤ ከባድ የሚባል አይነት ነበር። በቋፍ ላይ የነበረዉም ይህ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፤ ባለፈዉ ጥር 18 ቀን 2017 ዓ.ም ተቋረጠ። ክልላዊ ሃገራት እና መንግሥታት፤ የሁለቱን ሃገራት መንግሥታት ለማስታረቅ ጥረቶች ቢያደርጉም ትንሽ መሻሻል እንኳ አላመጡም።
እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግምት፤ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተቀሰቀሰዉ ኃይል የቀላቀለ ግጭት፤ ወደ ሰፊ ክልላዊ ቀውስ ሊያድግ ይችላል። በዓለም አቀፍ የስትራቴጂ ጥናት ተቋም የአፍሪቃ ቀንድ ዳይሬክተር ዶ/ር ሀሰን ካነንጄ ጨምሮ አንዳንድ ባለሙያዎች ይህ አይከሰትም ይላሉ።
«እኛ ምናልባት በተፋላሚ ወገኖች መካከል ማለትም በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግሥት እና በ M 23አማጽያን መካከል ዉግያ ሲባባስ እና አንዳንድ የአካባቢው አገሮች ለሁለቱም ቡድኖች በየዘርፉ ድጋፋቸዉን ሲጨምሩ ልናይ እንችላለን። »
ምንም እንኳ ይህ ክስ ዉድቅ ቢደረግም፤ ዩጋንዳ ልክ እንደ ሩዋንዳ ሁሉ በምስራቅ ኮንጎ የታጠቁትን ቡድኖች ትደግፋለች። ይህ በእንዲህ እንዳለ በዲሞክራቲክ ኮንጎ ከምስራቅ ሰሜን ኪቩ የመጡ ስደተኞች ወደ ጎረቤት ሀገራት እየሰደዱ ነው። ሁኔታዉ የድንበር አለመረጋጋት ስጋትን ጨምሯል።
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሚንቀሳቀሰዉ በM23 መሪዎች ላይ ማዕቀብ ተጥሏል፣ የውጭ ጣልቃ ገብነትን በተመለከተም ማስጠንቀቂያዎች ተሰጥተዋል። ይሁን እንጂ የዓለም አቀፉ ምላሽ ጥንካሪ አልባ በመሆኑ፤ የአፍሪቃ ማኅበረሰቦች የግጭቱን መዘዝ እና መፍትሄዉን እንዲሸከሙ አድርጓቸዋል። ከ100 ሚሊዮን በላይ ለሚሆነው ለዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ህዝብ ደግሞ ጉዳቱ ከባድ ሆንዋል።
አዜብ ታደሰ /አንድሪዉ ዋሲኬ
ፀሐይ ጫኔ