1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳ ኅብረት የማዕቀብ እርምጃ

ማክሰኞ፣ የካቲት 15 2014

የኅብረቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት እንደሚሉት አዳዲሶቹ ማዕቀቦች ደግሞ ህገ ወጥ ባሉት በአማጽያን ለተያዙ ሁለቱ ግዛቶች እውቅና በመስጠቱ ሂደት የተሳተፉትን የሩስያ ባለስልጣናት ፣ባንኮችን ለጦር ኃይሉ የሚደረግ የፋይናንስ ድጋፍንም ያካትታል።ራሳቸውን ከዩክሬን የገነጠሉት ሁለቱ ግዛቶች ከኅብረቱና ኅብረቱም ከነርሱ ጋር የሚያካሂደውን ንግድም ይጨምራል።

Frankreich | Sondertreffen von G7 Außenminister
ምስል Michel Euler/Pool)/AP/picture alliance

የተባባሰው ዩክሬንና ሩስያ ቀውስና የአውሮጳ ኅብረት እርምጃ

This browser does not support the audio element.

የዛሬው አውሮጳና ጀርመን ዝግጅታችን በተባባሰው የዩክሬን ሩስያ ቀውስና በአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት እርምጃዎች ላይ  ያተኩራል። 

ከወራት ወዲህ የዓለምን ትኩረት በእጅጉ የሳበው የዩክሬን ሩስያ ቀውስ አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ በረድ ያለ መስሎ ከከከረመ በኋላ ትናንት ማምሻውን መልኩን ቀይሯል።  የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከዩክሬን እንገንጠል ለሚሉ ራሳቸውን ራሰ ገዝ ሪፐብሊኮች ብለው ለሚጠሩት ዶኔትስክና ሉሃንስክ ትናንት እውቅና ከሰጡ በኋላ የምዕራባውያን ትዕግስት የተሟጠጠ ይመስላል። ወታደሮችዋን ወደ ዩክሬን ድንበር ያስጠጋችውና የተወሰኑትንም ወደ ሁለቱ ግዛቶች ያስገባችው ሩስያ ፣ዩክሬንን ትወራለች የሚል ስጋት ያሳደረባቸው ምዕራባውያን  እስከ ዛሬ በዛቻ ያነሱት የነበረውን ማዕቀብ አሁን በሩስያ ላይ ለመጣል እየተዘጋጁ ነው። ዩክሬን ሩስያን በማዕቀብ ቅጡልኝ ስትል ፣ እስከ ትናንት ድረስ ማዕቀብ ለአሁኑ አያስፈልግም ቅድምያ ለሰላማዊ መፍትሄ እንስጥ ሲል የቆየው የአውሮጳ ኅብረት ከትናንት ማታ በኋላ የእስከዛሬውን አቋሙን ቀይሯል። ለሁለቱ የዩክሬን ግዛቶች እውቅና በሰጠችው በሩስያ ላይ ምን ዓይነት ማዕቀቦችን እንደሚጥሉ ለመወሰን ዛሬ ፓሪስ ፈረንሳይ ውስጥ የህብረቱ አባል ሀገራት አምባሳደሮች  ተነጋግረዋል።ማምሻውን ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ያሳልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። የስብሰባው አስተናጋጅ የፈረንሳይ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዦ ኢቭስ ለድርዮ የሩስያውን ፕሬዝዳንት እርምጃ አውግዘው በዩክሬን ሉዓላዊነትና አንድነት ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ሲሉ ኮንነውታል። 
« ክቡራትና ክቡራት ፕሬዝዳንት ፑቲን ለራስ ገዝ ሪፐብሊኮቹ ዶኔትስክና ሉሀንስክ እውቅና ለመስጠት መወሰናቸውን ተገንዝበናል።ይህን በብርቱ እንደምናወግዘው መናገር እንፈልጋለን።ይህ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የጣሰ ነው። በዩክሬን ሉዓላዊነትና አንድነት ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ነው። ይህ ሩስያ ዓለም አቀፍ ሃላፊነቶቿን ወደ ጎን ያለችበት እርምጃ ነው።ይህ ሩስያ የፈረመችውን የሚኒስኩን ስምምነቶች መጣስ ነው።ስለዚህ ሁኔታው በጣም ከባድ ነው።»
ካሉ በኋላ ለሩስያ ሦስት መልዕክቶችን እንልካለን ብለዋል።
« በመጀመሪያ በሩስያ ተቀባይነት የሌለው እርምጃ ላይ ጠንካራ አቋም እንደያዝን ፣ከዩክሬን ጋር እንደምንተባበር መልዕክት ማስተላለፍ ነው። የፈረንሳይ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ትናንት ለሊት ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ጋር ተነጋግረዋል። ሌላው ደግሞ አውሮጳውያን ዛሬ የሚያስተላልፉት የአንድነት መልዕክት ነው። የማዕቀብ እርምጃዎችን እንወስዳለን። ዛሬ ከሰዓት በኋላ ከአውሮጳውያን ባልደረቦቻችን ጋር ምን ዓይነት እርምጃዎችን እንደምንወስድ በጋራ ለመወሰን እንነጋገራለን።»
በዚሁ መሰረት 27ቱ የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራትዛሬ ማምሻውን ጠንከር ያሉ የቅጣት እርምጃዎችን ይወስናሉ ተብሎ ይጠበቃል።ኅብረቱ ሞስኮ ዩክሬንን ከወረረች ከባድ መዘዞችን የሚያስከትል ማዕቀቦችን እንደሚጥል በተደጋጋሚ ሲያስጠነቅቅ ቆይቷል። ሆኖም የአውሮጳ ኅብረት ከሩስያ ጋር በኃይልና በንግዱ መስክ ያሉትን ጥብቅ ግንኙነቶች ግምት ውስጥ በማስገባት ማዕቀቦቹን ለማቅለልም ይፈልግ ነበር። የአውሮጳ ኅብረት ባለስልጣናትና ዲፕሎማቶች እንደሚሉት የኅብረቱ አባል ሀገራት በሩስያ ላይ መጣል አለበት ስለሚባለው ማዕቀብ ተመሳሳይ ሀሳብ የላቸውም።አንዳንድ አባል ሀገራት ማዕቀቡ የሩስያው ፕሬዝዳንት በምስራቅ ዩክሬን በሚወስዱት እርምጃ ላይ ብቻ የተገደበ እንዲሆን ይፈልጋሉ።ሌሎች ደግሞ ከቅርብ ሳምንታት በፊት የተነጋገሩባቸውን ማዕቀቦች ሙሉ በሙሉ በሩስያ ላይ እንዲጣሉ ይሻሉ። የሩስያ የቅርብ ወዳጅ የሚባሉት ኦስትሪያ ሀንጋሪ እና ኢጣልያ ሩስያ ሙሉ ማዕቀብ የሚጣልባት ጦሯ ዩክሬንን በግልጽ ሲወር ብቻ ነው የሚል ያልተጻፈ ስምምነት አላቸው። የባልቲክ፣የማዕከላዊና የምሥራቅ አውሮጳ ሀገራት ግን፣ ሩስያ ወረራ ባታካሂድም ዩክሬን ላይ ወታደራዊ ጥቃት እስከሰነዘረች ድረስ በአስቸኳይ ማዕቀብ ይጣልባት ነው የሚሉት።ምዕራቡ ዓለም ሩስያ የክሪምያን ልሳነ ምድር ከዩክሬን በኃይል ከወሰደች በኋላ በጎርጎሮሳዊው 2014 በሩስያ የኃይል የባንክ አገልግሎትና የመከላከያ ዘርፎች ላይ ያነጣጠሩ የኤኮኖሚ ማዕቀቦችን ጥሎባት ነበር።
የኅብረቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት እንደሚሉት አዳዲሶቹ ማዕቀቦች ደግሞ ህገ ወጥ ባሉት በአማጽያን ለተያዙ ሁለቱ ግዛቶች እውቅና በመስጠቱ ሂደት የተሳተፉትን የሩስያ ባለስልጣናት እንዲሁም ባንኮችን ለጦር ኃይሉ የሚደረግ የፋይናንስ ድጋፍንም ያካትታል። ራሳቸውን ከዩክሬን የገነጠሉት ሁለቱ ግዛቶች ከኅብረትና ኅብረቱም ከነርሱ ጋር የሚያካሂደውን ንግድም ይጨምራል። ማዕቀቦቹ  የሩስያ ባንኮችን የዓለም አቀፍ የገንዘብ ዝውውር መሰረት ከሆነው ስዊፍት ከተባለው ኔትዎርክ ማስወጣትንም ሊጨምር ይችላል ተብሏል።እነዚህን የመሳሰሉት ማዕቀቦች የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት መሪዎች ብራሰልስ ውስጥ በሚያካሂዱት ልዩ ጉባኤ ሊወሰኑ ይችላሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው። መሪዎቹ መቼ እንደሚሰበሰቡ ግን እስካሁን ይፋ አልተደረገም።ከኅብረቱ ውጭ አባል ሀገራትም የበኩላቸውን እርምጃ እንደሚወስዱ እየተናገሩ ነው።ከመካከላቸው በኅብረቱ ውስጥ ተሰሚነት ያላት ጀርመን የአጸፋ ያለችውን እርምጃ ወስዳለች። የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ከሩስያ ወደ ጀርመን ለተዘረጋው ኖርድ ስትሪም ሁለት ለተባለው የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ስራ እውቅና የሚሰጥበትን ሂደት ማስቆማቸውን ዛሬ አስታውቀዋል። ሾልዝ ዛሬ በርሊን ውስጥ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ  እንዳሉት ሂደቱ ቆመ ማለት ኖርድ ስትሪም ሁለት ሥራ አይጀምርም።
« የፌደራል ኔትወርክ ኤጀንሲ ስለ ጋዝ መስመሩ ደኅንነት ባቀረበው ሪፖርት ላይ የሚያካሄደውን ትንተና እንዲያቆም ዛሬ የፌደራሉን  የኤኮኖሚ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ጠይቄያለሁ። ይህ ቴክኒካዊ ጉዳይ ሊመስል ይችላል።ሆኖም ለጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ምንም ዓይነት እውቅና እንዳይሰጥ ለማረጋገጥ የተወሰደ አስፈላጊ ሕጋዊ፣ አስተዳደራዊ እርምጃ ነው። ይህ እውቅና ወይም ሰርተፊኬት ሳይገኝ ኖርድ ስትሪም ሁለት ስራ ሊጀምር አይችልም።»
የጋዝ ማስተላለፊያ ፕሮጀክቱ ስራ ተጠናቋል። ሆኖም ቧንቧው ጋዝ ማስተላለፍ ከመጀመሩ በፊት ከጀርመን ባለሥልጣናት  የስራ ሂደት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ያስፈልጋል።ዩናይትድ ስቴትስ የዚህ ፕሮጀክት ዋነኛ ተቃዋሚ ናት፤ ፕሮጀክቱ አውሮጳን በኃይል ፍላጎቷ ምክንያት የሩስያ ጥገኛ ያደርጋታል የሚል ስጋት ስላላት ። የአሜሪካኑ ፕሬዝዳንት ጆባይደን የሩስያ ታንኮችና ወታደሮች የዩክሬንን ድንበር ጥሰው ከገቡ፣ ፕሮጀክቱ ስራ የመጀመር እድል አይኖረውም ሲሉ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ አስጠንቅቀው ነበር። ኖርድ ስትሪም ሁለት ስራ ቢጀምር ከሩስያ ፣በዩክሬን በኩል አድርጎ ወደ ጀርመን የሚተላለፈው የጋዝ መጠን ከእስካሁኑ በሁለት እጥፍ እንዲጨምር ያደርጋል ተብሏል። 
እስከ ቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ ድረስ  ከሶቭየት ኅብረት ግዛቶች አንዷ የነበረችው ዩክሬን ከሶቭየት ኅብረት መፈረካከስ በኋላ በጎርጎሮሳዊው ነሐሴ 1991 ነበር ነጻነትዋን አውጃ ራስዋን የቻለች ሀገር የሆነችው። መጀመሪያ ላይ ኤኮኖሚዋ የሞስኮ ጥገኛ የነበረው ዩክሬን ቀስ በቀስ ወደ ምዕራቡ ዓለም ማማተር ጀመረች። ከአውሮጳ ኅብረትና ኔቶም ጋር መነጋገረ ያዘች። እነዚህ ተደማምረው የ2004ቱን ብርቱካናማ አብዮት ካቀጣጠሉ በኋላ መፍቅሬ አውሮጳው ቪክቶር ዩሽቼንኮ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሆኑ። እስከ 2010 ድረስም ስልጣን ላይ ቆዩ።የሩስያ ወዳጅ ቪክቶር ያኑኮቪች ዩሽቼንኮ ከተኩ በኋላ ደግሞ ከዚህ ቀደም ዩክሬን ከአውሮጳ ኅብረት ጋር የተፈራረመችውን የትብብር ስምምነት አስቆሙ። እርምጃው ተቃውሞ አስነስቶ እርሳቸውም ከጥቂት ሳምንታታት በኋላ ከስልጣን ተነሱ። ከዚያ በኋላ ሩስያ ከዩክሬን ጋር የሚያዋስናትን የክሪምያ ልሳነ ምድር ተቆጣጠረች።ሩስያ ክሪምያን ደም ሳይፈስ ነበር የያዘችው። ይሁንና ምስራቅ ዩክሬን በሚገኙት ዶኔትስክና ሉሃንስክ በተባሉት ራስ ገዝ ግዛቶች በሩስያ ይደገፋሉ ከሚባሉ አማጽያን ጋር በተካሄደው ጦርነት ግን የተመድ እንደሚለው ከ13 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወት አልፏል። በጎርጎሮሳዊው 2015 በየካቲት ወር በፈረንሳይ ና ጀርመን ሸምጋይነት ሩስያና ዩክሬን የሚኒስኩን የተኩስ አቁም ስምምነት ለመፈራረም በቁ።ሆኖም ከ20 ጊዜ በላይ የተኩስ አቁሙ በመጣሱ ስምምነቱ ባለበት እንደቆመ ነው።ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ አዳዲስ አባላትን መመልመል የጀመረው የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ በጎርጎሮሳዊው 2008 ቡዳፔስት ሃናጋሪ ውስጥ ባካሄደው ጉባኤው ዩክሬን የኔቶ አባል ልትሆን እንደምትችል ተስፋ ሰጠ። ዩክሬን የኔቶ አባል መሆንዋ ለሩስያ ህልውና አደጋ ነው የምትለው ሞስኮ  ኔቶ ዩክሬንን አባል አደርጋለሁ ማለቱን ተቃውማለች። ይህም በአሁኑ ቀውስ ካነሳቻቸው ጥያቄዎች አንዱ ነው።ከዚህ ሌላ ሞስኮ ኔቶ በአጠቃላይ ወደ ምሥራቅ አውሮጳ ሀገራት መስፋፋቱን እንዲያቆምም ነው የምትጠይቀው።ከተወሰኑ ወራት በፊት አንስቶ ሩስያ ታንኮችን መድፎችንና ተዋጊ ሄሊኮፕተሮችን ዩክሬን ድንበር ላይ አከማችታለች።አሜሪካ እንደምትለው ሩስያ ድንበር ላይ ያሰፈረቻቸው ወታደሮች ከ15o ሺህ በላይ ናቸው።ከሩስያ ሌላ በጎረቤት ቤላሩስም ከ100 ሺህ በላይ ለውጊያ የተዘጋጁ ወታደሮች በተጠንቀቅ ላይ ናቸው ።እነዚህ  ዩክሬን ለመወረር የተደረጉ ቅድመ ዝግጅቶች ናቸው ቢባልም ሩስያ ግን ወታደሮች በዚያ የሚገኙት ለወታደራዊ ልምምድ ነው ትላለች።በአንጻሩ ኔቶም በሌሎች የምስራቅ አውሮጳ ሀገራት ኃይሉን እያጠናከረ ነው።በዚህ መሀል ትናንት ማታ ፑቲን ለዶኔትስካና ለሉሃንስክ እውቅና መስጠታቸው ቀውሱን አባብሶ ምዕራባውያን በሩስያ ላይ ጠንካራ ማዕቀቦችን ለመጣል ተዘጋጅተዋል።  ፑቲን ራሳቸውን ከዩክሬን ገንጥለናል ለሚሉት ሁለቱ ግዛቶች እውቅና ከሰጡ በኋላ ቀድሞም በሩስያ ጠንካራ ማዕቀቦችን እንደምትጥል ስትዝት የነበረችው የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ጆባይደን ፣በሁለቱ ግዛቶች ላይ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰትና የንግድ ግኙነት ገደብ እንዲጣል ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ሰጠተዋል።ዛሬ የተባባሰው የዩክሬን ቀውስ በሚቀጥሉት ቀናት ወዴት ሊያመራ እንደሚችል የሁሉም ጥያቄና ስጋት ሆኖ ቀጥሏል።

ምስል Maxim Shemetov/REUTERS
ምስል Johanna Geron/Sergei Guneyev/AFP
ምስል Sven Hoppe/REUTERS
ምስል Sputnik/AP/picture alliance

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW