1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

​​​​​​​የተባባሰው የፈረንሳይ የፖለቲካ ቀውስና ስጋቱ

ማክሰኞ፣ መስከረም 27 2018

አሁን ዝቅተኛ የህዝብ ድጋፍ ያላቸው የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮ የኮርንዩን የስልጣን መልቀቂያ ተቀብለዋል። የፈረንሳይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የፖለቲካ ቀውሱ እንደተባባሰ ጊዜ ሳያጠፉ ፕሬዝዳንት ማክሮ ስልጣን እንዲለቁ አለያም ወቅቱን ያልጠበቀ የምክር ቤት ምርጫ እንዲጠሩ እየወተወቱ ነው። ማክሮ ግን ሁለቱንም ጥያቄዎች አይቀበሉም።

ተሰናባቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ሴባስትያን ለኮርንዩ ስልጣን መልቀቃቸውን በይፋ ሲናገሩ
ተሰናባቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ሴባስትያን ለኮርንዩ ስልጣን መልቀቃቸውን በይፋ ሲናገሩ ምስል፦ Eliot Blondet-Pool/SIPA/picture alliance

​​​​​​​የተባባሰው የፈረንሳይ የፖለቲካ ቀውስና ስጋቱ

This browser does not support the audio element.

 
«ዛሬ ሰኞ ጠዋት፣ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃላፊነቶቼን ለመወጣት እና መንግስቱንም ነገ በብሔራዊው ምክር ቤት ፊት ለማቅረብ የሚያስችሉኝ ሁኔታዎች አልተሟሉልኝም » በማለት ነበር  
የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሴባስትየን ለኮርኒዩ፣ መንግስታቸውን ባቋቋሙ ከ24 ሰዓታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ትናንት ስልጣናቸውን የለቀቁበትን ምክንያት የተናገሩት። ስልጣን በያዙ በ27ተኛው ቀን ከሃላፊነታቸው በፈቃዳቸው የተነሱት ለኮርኒዩ የ14 ሰዓት ከ26 ደቂቃ እድሜ ብቻ የነበረውን መንግሥታቸውንም አፍርሰዋል። ይህም መንግስታቸውን በፈረንሳይ የቅርብ ጊዜ ታሪክ እጅግ በጣም አጭር ጊዜ የቆየ መንግሥት አድርጎታል። 

ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለሳምንታት ከተካሄደ ምክክር በኋላ ባለፈው እሁድ ነበር  ለኮርኒዩ ሚኒስትሮችን የሾሙት።  ከተሾሚዎቹ ጋርም ትናንት ከሰዓት በኋላ የመጀመሪያ ስብሰባቸውን ለማካሄድ ቀጠሮ ይዘው ነበር ።  ይሁንና የአዲስ ተሿሚ ሚኒስትሮች ስም ዝርዝር ይፋ እንደተደረገ ፣ተቃዋሚዎችም አጋሮችም የተለያዩ አስተያየቶችን ሲሰንዘሩና ጥያቄዎችም ሲያዥደጉዱባቸው፣  ለኮርንዩ የስልጣን መልቀቂያቸውን ለማክሮን አስገቡ። ስልጣን ከያዙ ወር ሊደፍኑ 3 ቀናት ብቻ ሲቀራቸው ሳይታሰብ የስራ መልቀቂያ ያስገቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ለኮርኒዩ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት አጋሮችና ጠላቶች አዲሱን መንግሥት እንደሚገለብጡ መዛት ከጀመሩ በኋላ መሆኑንም ተናግረዋል።  ችግሩ ምክር ቤት ውስጥ መቀመጫ ያላቸው የተለያዩ ፓርቲዎች የሚያራምዱት የተለያየ አስቸጋሪ አቋም እንደሆነም ለኮርንዮ አልሸሸጉም። «የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉም በብሔራዊ ምክር ቤት ውስጥ ፍጹም አብላጫ ድምፅ ያላቸው ይመስል አቋም ይዘው ቀጥለዋል። በስተመጨረሻም ፣ ሰጥቶ ለመቀበል ዝግጁ እንድሆን አደረገኝ ።ሆኖም እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ የሌላውየፖለቲካ ፓርቲአጠቃላይ ዓላማና ፕሮግራም እዲሻሻል ይፈልጋል። ይህ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ የመሀል አቋም ካላቸው ፓርቲዎች ቡድን በሆኑ እና በተቃዋሚዎችም የሚደረግ ነው። »

ከርሳቸው የቀደሙትን ጠቅላይ ሚኒስትር ፍራንሷ ባይሩን ተክተው በመስከረም ወር የተሾሙት ለኮርኒዩ ባለፉት 21 ወራት ውስጥ ፣ስልጣን ከለቀቁት የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትሮች አምስተኛው ናቸው።  ፈረንሳይ በከባድየፖለቲካ ቀውስውስጥ በምትገኝበት በዚህ ወቅት ላይ ዝቅተኛ የህዝብ ድጋፍ ያላቸው የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮም ትናንትናውኑ የኮርንዩን የስልጣን መልቀቂያ ተቀብለዋል። ዶቼቬለ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው ፈረንሳይ የተማሩትና የሰሩት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር አቶ ፉአድ ኢስማኤል ፍሬድሪክ ሀገሪቱ አሁን የምትገኝበት የፖለቲካ ሁኔታ ፖለቲከኞችንም ሆነ ህዝቡንም ያስደነገጠ ከባድ ቀውስ መሆኑን ተናግረዋል። በርሳቸው አስተየያት ችግሩ እዚህ ደረጃ ሊደርስ የቻለው፣ከውጭም ከሀገር ውስጥም ባሉት ግፊቶች ምክንያት ነው።

የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮ ምስል፦ Jean-Christophe Verhaegen/AFP/dpa/picture alliance

ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጊዜ ሳያጠፉ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮ ስልጣን እንዲለቁ አለያም ወቅቱን ያልጠበቀ የምክር ቤት ምርጫ እንዲጠሩ እየወተወቱ ነው። ማክሮ ግን ሁለቱንም ጥያቄዎች አይቀበሉም። በዩሮ ከሚገበያዩ የአውሮፓ ሀገራት ሁለተኛ ትልቅ ኤኮኖሚ የምታንቀሳቅሰው ፈረንሳይ ፣የፋይናንስ ጉዳዮቿን ለማስተካከል  እየታገለች ነው። በአሁኑ ጊዜ የፈረንሳይ እዳ ከአጠቃላዩ የሀገር ውስጥ ምርት ገቢ ወደ 113.9 በመቶ አድጓል። የበጀት ጉድለቱ ደግሞ ባለፈው ዓመት ፣የአውሮፓ ኅብረት ከሚፈቅደው ከ3 በመቶው ገደብ ወደ እጥፍ ተጠግቷል።   
ስለለኮርኒዩ ስራ መልቀቅና ስለመንግስታቸውም መፍረስ አስተያየታቸው የሰጡ ፈረንሳውያን ጨዋታው ቆሞ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈለግ ጠይቀዋል። 
«በጣም አድካሚ ነው፤ መረጋጋት ያስፈልገናል፤ ግን የለንም፤ሁሉም ነገር ተዘግቷል፤ እንደ ህጻን የሚሆኑ ከሆነ ፣ለኔ እንደ አፀደ ህጻናት ነው። በጣም አድካሚ ነው። መረጋጋት ያስፈልገናል። በእውነት ጠንካራና ዘላቂ የሆነ ነገር ያስፈልገናል።» «በሁኔታው ተናድጄያለሁ፤ መንግስቱ የቆየው ለ14 ሰዓታት ከ26 ደቂቃ ነው። እንደሚመስለኝ  ቁም ነገረኝነትን ይወክላሉ ተብለው ለሚታሰቡት ለፖለቲከኞች ይህ ተቀባይነት የለውም። »

«እኔ አላውቅም ትንሽ ተሰላችተናል። የሚሆነው ሁሉ አይስበንም፤ የሚሰራ መፍትሔ ያለ አይመስልም። ምን እንደሚሆንም አናውቅም።» 

ተሰናባቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ሴባስትያን ለኮርንዩ ምስል፦ Sarah Meyssonnier/REUTERS

ማክሮ ከሦስት ዓመት በፊት ዳግም ከተመረጡ ወዲህ የፈረንሳይ ፖለቲካ ሊረጋጋ አልቻለም። ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ እንደሚሉት ማክሮ ባለፈው ዓመት ወቅቱን ያልጠበቀ ምርጫ እንዲጠራ መወሰናቸው ምክር ቤቱን ይበልጥ በመከፋፈል ቀውሱን አባብሶታል። የዛሬ ሁለት ዓመት በግንቦት ወር ስልጣናቸው የሚያበቃው ማክሮን አሁን አዲስ ወቅቱን ያልጠበቀ ምርጫ ሊጠሩ ፣ ከስልጣናቸው ሊወርዱ አለያም ሌላ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሾሙ ይችሉ ይሆናል የሚሉ ግምቶች አሉ እርሳቸው ግን ምርጫ መጥራትንም ሆነ ስልጣን መልቀቅን ባለፉት ወራት በተደጋጋሚ ውድቅ አድርገዋል። የፖለቲካ ቀውሱን የከፋ ሲሉ የገለጹት አቶ ፉአድ እስማኤል  ያስከተላቸው መዘዞች እንዲህ ቀላል እንዳይደሉ ነው የገለጹት ።

ዛሬ ደግሞ ለሀገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ መፍትሔ እንዲያፈላልጉ  ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮ ለኮርንዩ ሃላፊነት ሰጥተዋቸዋል፤ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት ጋር እስከ ረቡዕ ምሽት ድረስ በጉዳዩ ላይ ውይይት እንዲያካሂዱ የቤት ስራ ሰጥተዋቸዋል። ሆኖም ይህ የፕሬዝዳንቱ እርምጃ ፖለቲከኞችን ማደናገሩ አልቀረም። ከመካከላቸው ፣አዲሱ ተልዕኮ ለማክሮ ጊዜ መግዣ ነው ሲሉ ጥርጣሪያቸውን የሰነዘሩም አሉ። 

ኂሩት መለሰ

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW