የተከፋፈሉትን የሕወሓት ፖለቲከኞች ለማስታረቅ የተደረገዉ ጥረት አልተሳካም
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 5 2017በህወሓት ሁለት ቡድኖች መካከል የተፈጠረው ልዩነት ለመፍታት በትግራይ በሚንቀሳቀሱ ሲቪክ ማሕበራት እና ሌሎች የተጀመረ ጥረት እስካሁን ውጤት አለማስገኘቱ ተገለፀ። በሌላ በኩል የህወሓት ከፍተኛ አመራር የሆኑት ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር፥ ፓርቲያቸው በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ያለው ውክልና ለመቀየር የጀመረው ጥረት እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የህወሓት ሁለት ቡድኖች ፍጥጫ ባየለበት በዚህ ወቅት፥ ይህ ልዩነት ለመፍታት ያለመ የተባለ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሲቪክ ተቋማት እና ሌሎች አደረጃጀቶች እንቅስቃሴ ማድረግ ላይ መሆናቸው ተገልጿል። በዶክተር ደብረፅዮን እና በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመሩት ሁለቱ የህወሓት ቡድኖች ለማነጋገር እንዲሁም ልዩነቶቻቸው ለመፍታት ከተጀመረው እንቅስቃሴ ውጭ እስካሁን በተጨባጭ የተደረገ ግንኙነት ይሁን የተገኘ ውጤት የለም ሲሉ ስማቸው ሊጠቀስ ያልፈለጉ፣ አንድ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ግለሰብ ነግረውናል። በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሲቪክ ማሕበራት ጨምሮ ሌሎች ከዚህ በፊት አውጥተውት በነበረ መግለጫ የህወሓት መሪዎች መካከል የተፈጠረው ግጭት ለመፈታት የተደረገ ጥረት አለመሳካቱ ገልፀው እንደነበረ ይታወሳል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ሳምንት አቶ ጌታቸው ረዳ ጨምሮ 13 የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የስራ ሐላፊዎች ከስልጣናቸው አንስቼአለሁ ያለው በደብረፅዮን የሚመራው ህወሓት፥ በዚህ ውሳኔው ዙርያ ከፌደራል መንግስቱ ጋር መነጋገሩ አስታውቋል።
ዶክተር ደብረፅዮን ወደ አዲስአበባ ተጉዘው ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጋር ስለመነጋገራቸው ዘግይቶ ያስታወቀው የህወሓት ይፋዊ ገፅ፥ የህወሓቱ መሪ በጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጋባዥነት ወደ አዲስአበባ ተጉዘው በፕሪቶሪያ ውል የእስካሁን አፈፃፀም፣ በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የአመራሮች ለውጥ ላይ እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች መምከራቸው ገልጿል። በውይይቱም ቀጣይ በሚደረግ ግንኙነት ውሳኔ የሚሰጥባቸው አጀንዳዎች ተለይተዋል ሲል ህወሓት ያስታወቀ ሲሆን፥ ከዚህ ውጭ የሚናፈሰው ወሬ ውሸት ነው፣ ህወሓት እጩ ፕሬዝደንት አላቀረበም ሲሉም ጠቁሟል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሳምንቱ መጨረሻ በመቐለ የህወሓት ነባር አቅም ከተባሉ አካላት ጋር በተደረገ መድረክ የተናገሩት የህወሓት ከፍተኛ አመራር ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር፥ ህወሓት በግዚያዊ አስተዳደሩ ያለው ውክልና ለማስተካከል ጥረቱ ይቀጥላል ብለዋል።
ወይዘሮ ፈትለወርቅ "የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ላይ የሰዎች ለውጥ ስላደረግን፥ አስተዳደሩን አፈረሱት እየተባለ በተደጋጋሚ ይነገራል። ይህ ስህተት ነው። በመጀመርያ ደረጃ ከ27 የካቢኔ ወንበሮች ህወሓት የሚመለከተው 14 ነው። 13ቱ አልተነካም በቦታው ነው ያለው። ከ14 የህወሓት ድርሻም ቢሆን 6ቱ አልተቀየረም የነበረ ነው" ብለዋል።
የህወሓት ስራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት ወይዘሮ ፈትለወርቅ ጨምረውም በትግራይ ከህወሓት እጅ ወጥቶ ያለው ስልጣን እንመልሳለን፣ ይህ ለማድረግም ጫናዎች እንፈጥራለን ሲሉ ተደምጠዋል።
ፈትለወርቅ "ከህወሓት እጅ ወጥቶ ያለው ስልጣን ወደ ህወሓት እጅ መመለስ አለበት። ይህ እንዲሆን ህዝባችን እናስረዳለን፣ የማነሳሳት ስራዎች እንሰራለን፣ በየደረጃው እየከረረ የሚሄድ ትግል እናደርጋለን። የማይቀየር ከሆነ ይበልጥ ዙር እያከረርን እንሄዳለን። በህዝብ ጫና ውረድ ወደምንልበት ልንሄድ እንችላለን። ከፌደራል መንግስት ጋር ያለው ግንኙነት በሚመለከት፥ በእኛ በኩል ፕሬዝደንት የሚሆነው የሁለትዮሽ መግባባት ሲኖር ብለን ስለምናምን፣ በአንዱ ወገን እምነት ካጣ ለማውረድ ምንም ችግር የለውም እንላለን። ሁለታችን ካመንንበት ነው የሚሆነው፥ አንዳችን ካላመንንበት አለቀ። ማን ይተካ በሚለው ግን መወያየት አለብን" ብለዋል።
የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የጥፋት ቡድን ብሎ የጠራው የህወሓት ቡድን ግዚያዊ አስተዳደሩ ለማፍረስ እየሰራ ነው ሲል የሚከስ ሲሆን በዚህ ላይም እርምጃ እወስዳለሁ ይላል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሰ