1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሕግ እና ፍትሕኢትዮጵያ

«የተዘነጉ ድምፆች» የቅድመ - ክስ እሥር በኢትዮጵያ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 29 2016

የቅድመ ክስ እሥርን ለመቆጣጠር እና ለማስቀረት እንዲሁም የፍትሐዊ እና ሰብአዊ መብት መርኾችን ያካተተ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ለመገንባት፤ የፍትሕ አካላት እና ሌሎች ባለድርሻዎች ግዴታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ ።

ያለፍርድ ሒደት በካቴና የታሰሩ እጆች፦ የፍትሕ እጦት
ያለፍርድ ሒደት በካቴና የታሰሩ እጆች፦ የፍትሕ እጦት ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Kim Ludbrook/dpa/picture alliance

«የተዘነጉ ድምፆች»

This browser does not support the audio element.

የቅድመ ክስ እሥርን ለመቆጣጠር እና ለማስቀረት እንዲሁም የፍትሐዊ እና ሰብአዊ መብት መርኾችን ያካተተ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ለመገንባት፤ የፍትሕ አካላት እና ሌሎች ባለድርሻዎች ግዴታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ ። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን «የተዘነጉ ድምፆች» በሚል አራት ሰዎች በተራዘመ እሥር ምክንያት የደረሰባቸውን እንግልት የሚያሳይ ምስክርነት ያወጣ ሲሆን፤ ታሳሪዎቹ በተራዘመ ቅድመ ክስ እሥር ምክንያት ፍትሕ ማጣታቸውን ተናግረዋል ። ግለሰቦቹ በፀጥታ አካላት የተያዙበትን ሁኔታ፣ ለምን ያህል ጊዜ በእሥር እንደቆዩ በተናገሩበት ቃል የትምህርታቸው ሁኔታ እንደሚያሳስባቸው፣ መሰል ድርጊት ለምን እንደተፈፀመባቸው እና የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ካልተከበረ የማን ይከበራል  በሚል የተሰማቸውን ቁጭት ገልፀዋል። 

«የተዘነጉ ድምፆች»

መብት ገዳቢ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደጋግሞ በተደነገገባት ኢትዮጵያ በተለይ ፖለቲከኞች፣ የማኅበራዊ ንቃት ፈጣሪዎች፣ ጋዜጠኞች እና ያገባናል ባዮች በፀጥታ አካላት ከተያዙ በኋላ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለተራዘመ የቅድመ ክሥ እሥር ሲዳረጉ ተስተውሏል ።

በቀረበው ታሪክ ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎችን መገኛ ቦታ እና ስማቸውን ለደኅንነታቸው ሲል መቀየሩን የገለፀው ብሔራዊው የሰብዓዊ መብት ተቋም - ኢሰመኮ

በየዓመቱ ሚያዚያ 17 ቀን የሚታሰበውን የአፍሪካ ቅድመ-ክስ እሥራት ቀንን ታሳቢ በማድረግ ስለ የቅድመ-ክስ እሥር ግንዛቤ ለመፍጠር በሚል ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ያሰባሰባቸውን አራት ታሪኮች «የተዘነጉ ድምፆች» በሚል አጋርቷል።

የተራዘመ የቅድመ- ክስ እሥራት ለነፃነት መብት ጥሰት ዋነኛ ምክንያት ነው ያለው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በሕይወት የመኖር መብት፣ ከስቃይ እና ከኢ- ሰብዓዊ አያያዝ የመጠበቅ መብት፣ የዋስትና መብት እና የተቀላጠፈ ዳኝነት የማግኘት መብትን የሚቃረን እንደሆነም አመልክቷል።

የፍትሕ ሚዛኑ ከወዴት ነው? በቅድመ - ክስ እሥር ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች ያለፍትሕ እየተንገላቱ ነው ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Arne Dedert/dpa/picture alliance

«የትምህርቴስ ነገር»?

ከታጣቂ ቡድን ጋር ግንኙነት አለህ በሚል መታሠሩን ለመብት ተቋሙ የተናገረው የ 10ኛ ክፍል ተማሪ "አንድም ጊዜ ፍርድ ቤት አልቀረብኩም፣ ክሥም አልተመሠረተብኝም፣ ትምህርቴም ተቋርጧል" ብሏል። "ፍትሕ መቼ እና በማን አግኝቼ እንደምፈታ ጥያቄ ሆኖብኛል" ሲል ጭንቀቱን ለኢሰመኮ ያጋራው ይህ ወጣት በ 2015 ዓ.ም በምሽት ከመኖሪያ ቤቱ ተይዞ ከታሠረ አንድ ዓመት ከሁለት ወር እንደሆነው በቀረበው መግለጫ ተጠቅሷል።

«ለምን እኔ»?

"ለምን እኔ" ስትል የምትጠይቀው ሁለተኛዋ የቅድመ - ክስ እሥር ተጎጂ ግለሰብ፤ ፀጉሯን ለመሠራት ወደ ከተማ እየሄደች እያለ በፖሊሶች መያዟን አብራርታለች። "ወንድምሽ እና የአጎትሽ ልጅ የታጣቂ ቡድን አባል ናቸው። የት እንዳሉ መረጃው አለሽ ብለው ነው የያዙኝ" ስትል ቃሏን የሰጠችው ይህቺ ሴት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ከተወሰደች በኋላ ድብደባ እንደተፈፀመባትም ለኢሰመኮ አመልክታለች። ከተያዘችበት ከ 2015 ዓ.ም ጀምሮ "በወቅታዊ ጉዳይ" በሚል ለአሥራ ስድስት ወራት ፍርድ ቤት ሳትቀርብ፣ ክስም ሳይመሠረትባት በእሥር ላይ መሆኗንም ተናግራለች።

በኢትዮጵያ በተለይ ፖለቲከኞች፣ የማህበራዊ ንቃት ፈጣሪዎች፣ ጋዜጠኞች እና ያገባናል ባዮች በፀጥታ አካላት ከተያዙ በኋላ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለተራዘመ የቅድመ ክሥ እሥር ሲዳረጉ ማየት ተለምዷል።

«በሕግ አምላክ»

«የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ካልተከበረ ለማን አቤት ይባላል...» ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Ute Grabowsky/photothek/picture alliance

የ34 ዓመቱ ባለትዳር እና የልጆች አባት የሆነው ሌላኛው ታሳሪ፣ በሚኖርበት ከተማ ተፈጥሮ ከነበረ ግጭት ጋር ተያይዞ 2014 ዓ. ም ላይ "በከባድ ውንብድና ወንጀል" የተያዘ ነው። ይሄው ተጎጂ በወቅቱ ፍርድ ቤት ቀርቦ እንደነበር የተገለፀ ሲሆን ክስ ሳይመሠረትበት በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ለሰባት ወራት በማረሚያ ቤት ለተራዘመ እሥር ተዳርጎ መቆየቱ ተገልጿል።

"የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ካልተከበረ ለማን አቤት ይባላል...."

ወቅታዊ ጉዳይ በሚል ተይዞ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ አምስት ወር ከቆየ በኋላ ቤተሰቦቹ የዋስ መብቱ እንዲጠበቅ ወረዳ ፍርድ ቤት ጥያቄ አቅርበው ተፈቅዶ ፣ ገንዘብም ተከፍሎ እንደነበር ለኢሰመኮ ያስረዳው ግለሰብ ሆኖም ፖሊስ "በፀጥታ ምክር ቤት ስለተያዝክ በፍርድ ቤት አትፈታም" በሚል ለአራት ወር በእሥር ላይ መሆኑን ገልጿል።

"የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ካልተከበረ ለማን አቤት እንደሚባል አላውቅም" ያለው ይህ የ 35 ዓመት አርሶ አደር እና የቤተሰቡ ብቸኛ አስተዳዳሪ ግለሰብ ራሱም የዋስትና ገንዘቡም ታሥረው ቤተሰቡ መራቡን አስታውቋል ።

ለረጅም ጊዜ ያለ ክስ ለተራዘመ ቅድመ-ክስ እሥር የተዳረጉ ሰዎችን ቀደም ሲል እንዲፈቱ ማድረጉን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገልጿልምስል Solomon Muche/DW

የቅድመ ክሥ እሥር የሚፈቀድበት አሠራር

በተለያዩ ጊዜያት መሰል ጉዳዮችን በማጣራት በሰጣቸው ምክረ ሀሳቦች ለረጅም ጊዜ ያለ ክስ ለተራዘመ ቅድመ-ክስ እሥር የተዳረጉ ሰዎች እንዲፈቱ ማድረጉን የገለፀው ኢሰመኮ፤ የቅድመ ክስ እሥራት "ተጨማሪ የወንጀል ተግባርን ለመከላከል፣ የተጠርጣሪውን ማምለጥ ለመከላከል ወይም በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ውስጥ የተጠርጣሩዎችን ተገቢ ያልሆነ ጣልቃ ገብነት ለመከላከል በአሳማኝ ምክንያታዊ ሁኔታ ብቻ የሚፈቀድ" በመሆኑ ይህንን ለማስቀረት የፍትሕ አካላት እና ሌሎችም የድርሻቸውን እንዱወጡ ብሔራዊው የመብት ተቋም ጠይቋል ።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW