1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተዘነጋው የሕዝብ ቆጠራ

ዓርብ፣ ሐምሌ 5 2016

የኢትዮጵያ ፌደራል ሕገመንግስት አንቀጽ 103 ንኡስ አንቀጽ 5 “የሕዝብ ቆጠራ በየ 10 ዓመቱ ይካሄዳል። በውጤቱም የምርጫ ክልሎችን አከላለል የምርጫ ቦርድ በሚያቀርበው ረቂቅ መሰረት የፌደረሽን ምክርቤት ይወስናል“ ሲል ይደነግጋል።

"ለመጨረሻ ጊዜ ቆጠራ ከተካሄደ እስከ አሁን ባለው ጊዜ የሕዝብ ቁጥር በ40 ሚልዮን ጨምሯል።" የምጣኔ ሐብት ባለሙያ
"ለመጨረሻ ጊዜ ቆጠራ ከተካሄደ እስከ አሁን ባለው ጊዜ የሕዝብ ቁጥር በ40 ሚልዮን ጨምሯል።" የምጣኔ ሐብት ባለሙያ ምስል Anantha Krishnan/Pacific Press/picture alliance

የተዘነጋው የሕዝብ ቆጠራ

This browser does not support the audio element.

ዛሬ ዓለም አቀፍ የሕዝ ብዛት ቀን ነው። በያዝነው የጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር የዓለም ሕዝብ ብዛት ከ8 ነጥብ 1 ቢልዮን በላይ መድረሱን ዕለቱን በማስመልከት የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በኢትዮጵያ የሕዝብ ቆጠራ መካሄድ ካለበት ድፍን 7 ዓመታት አልፎታል። ይህ በሕዝብ የፖለቲካ ውክልናና በዋናነት የሕዝብ ቁጥርን መሰረት ላደረገው የፌደራል መንግስት ለክልሎች የሚሰጠው የበጀት ድጎማ ላይ አሉታዊ ጥላውን እንዳጠላ የተወካዮች ምክርቤት አባላትና ፖለቲከኞች እየወተወቱ ነው።

ስለቆጠራው ሕገመንግስቱ ምን ይላል?

የኢትዮጵያ ፌደራል ሕገመንግስት አንቀጽ 103 ንኡስ አንቀጽ 5 “የሕዝብ ቆጠራ በየ 10 ዓመቱ ይካሄዳል። በውጤቱም የምርጫ ክልሎችን አከላለል የምርጫ ቦርድ በሚያቀርበው ረቂቅ መሰረት የፌደረሽን ምክርቤት ይወስናል“ ሲል ይደነግጋል። በዚሁም መሰረት እስከ አሁን ለሦስተኛ ጊዜ ቆጠራ የተካሄደ ሲሆን አራተኛው ዙር ቆጠራ ግን መካሄድ ከነበረበት ድፍን 7 ዓመታት አልፎታል።

ኢኮኖሚያዊ አንደምታው
ቆጠራው በወቅቱ ባለመካሄዱ በተለይ በዋናነትየሕዝብ ቁጥርን እንደመስፈርት ባደረገው የፌደራል መንግስት ለክልሎች የሚሰጠውን የበጀት ድጎማ ድልድል ላይና የሕዝብ ውክልና ላይ አሉታዊ ጥላውን  እንዳጠላ እየተነገረ ነው። የሕግና ሕገመንግስት ሙሁርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ተሰማ ኤልያስ፤
"የቆጠራው አለመካሄድ ካስከተላቸው የበጀት ድልድል ችግሮች እንደ አንድ ማሳያ የሚወሰደውና በፌደሬሽን ምክርቤትም አከራካሪ ሆኖ የቀጠለው፤  አሁን ወደ 4 ክልሎች የተከፈለው የቀድሞው የደቡብ ክልል ከዚህ ቀደም በተካሄደው የሕዝብ ቆጠራን መሰረት በማድረግ ነው የፌደራል መንግስት የበጀት ድጎማ የሚያገኘው። ይህ በክልሉ ከሚታዩ የሙስናና የበጀት አጠቃቀም ችግሮች ጋር ተዳምሮ ለበጀት እጥረት እንደዳረገው ይታወቃል።"
የሕዝብ ቆጠራ አለመካሄድ በኢኮኖሚ ላይ የሚኖሮው አሉታዊ ተጽዕኖ በተመለከተ ጀርመን አገር በዶይች ባንክ የሚሰሩት  የምጣኔ ሐብት ባለሙያው ዶክተር ተኽለወይኒ ገብረመድህን ተከታዩን አክለዋል።

" ያገኘሁት ቁጥር እንደሚያመለክተው ለመጨረሻ ጊዜ ቆጠራ ከተካሄደ እስከ አሁን ባለው ጊዜ የሕዝብ ቁጥር በ40 ሚልዮን ጨምሯል። ይህ ከጎረቤት አገር ሱዳን አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር ተቀራራቢ የሆነ ነው።  እና ይህን 40 ሚልዮን ሕዝብ የማያካትት የበጀት ድልድል ነው ተግባር ላይ እየዋለ ያለው ማለት ነው። ይህን ትተህ ቀደም ሲል በነበረው የሕዝብ ቁጥር መሰረት አድርገህ ፍትሐዊ የሐብት ክፍፍል ማድረግ አትችልም።"

አዲስ አበባ ከተማ በከፊልምስል Goethe Institut/Maheder Haileselassie

ፖለቲካዊ አንደምታው
የሕዝብ ቆጠራን በተመለከተ በሕገመንግስቱ መሰረት አለመከናወኑ የሕዝቡ ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንደሚያጠብ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባል የሆኑት አቶ አብረሃም በርታ ያስረዳሉ። 

"የሕዝብ ውክልና ሲባል በሕዝብ ቁጥር ነው አንድ ተመራጭ ወደ ምክርቤት የሚመጣው። እውነተኛ በሆነ መልሁ አንድ ተወካይ ወደ ምክርቤት የሚመጣው በሕዝብ ቁጥር ነው። ስለዚህ አስራምናምን ዓመት የሕዝብ ቁጥር ሳታውቅ 100ሺህ ሕዝብ የሚወክል ተመጭን ይወክላል ብሎ ወደ ምክርቤት ማምጣት ፍትሃዊ ላይሆን ይችላል።"

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድምስል Ethiopian National Election Board

በተለያዩ ምክንያቶች ለ3ኛ ጊዜ የተራዘመውና አሁን አሁን ጨርሶ የተረሳ የሚመስለው የሕዝብ ቆጠራ ጉዳይ በቅርቡ ከመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች ውጭ ዶይቼቨለን ጨምሮ ሌሎች ጋዜጠኞች እንዳይገቡ ተደርጎ በተካሄደ ስብሰባም ጉዳዩ ተነስቶ የገንዘብ ሚኒስትሩ “ቆጠራው የሚካሄድ ከሆነ ተጠባባቂ በጀት ስላለን ሊካሄድ ይችላል“ የሚል ግልጽ ያልሆነ ምላሽ እንደተሰጠ አቶ አብርሃም ነግረውናል።
ይህ የሕዝብ ቆጠራ አለመካሄዱን በተመለከተ ዕለታዊ ነጥብ ከማስቆጠር በዘለለ አማራጭ ሐሳቦችን በማቅረብ አይሞጉቱም እየተባሉ የሚወቀሱት የሐገሪቱ ፖለቲከኞችና ሙሁራን በዚህ ወሳኝ ነጥብ ላይ ድምጻቸውን አለማሰማታቸውን ብዙዎች ይወቅሳሉ። ረዳት ፕሮፌሰር ተሰማ ግን ይህ አገሪቱ ከገባችበት አጠቃላይ ፖለቲካዊ ውድቀት አንጻር ቅንጦት ነው ይላሉ። የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብና ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት አለመኖር በምክንያትነት በመጥቀስ።


ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ፀሐይ ጫኔ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW