የተዳከመው የደቡብ ሱዳን የሰላም ሂደት፤ የዩክሬን ሩስያ ርነት እና አፍሪቃ
ቅዳሜ፣ የካቲት 19 2014
የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርና ና ምክትላቸው ሪየክ ማቻር የአንድነት መንግሥት ከመሰረቱ ባለፈው ማክሰኞ ሁለት ዓመት ሆናቸው።ከዚያ በኋላ ደቡብ ሱዳን ልዩ ልዩ ቀውሶች ውስጥ ናት።የሰላም ሂደቱም ወደፊት መራመድ አቅቶታል።የሩስያና ዩክሬን ጦርነት ከአካባቢው አልፎ በአፍሪቃ ሀገራት ላይ ተጽእኖ እያሳደረ ነው። የአሁኑ ብቻ ሳይሆን የወደፊቱ ደግሞ ይbleጥ አሳሳቢ ሆኗል። የዛሬው ትኩረት በአፍሪቃ በነዚህ ሁለት ጉዳዮች ላይ ያተኩራል።ኂሩት መለሰ አጠናቅራዋለች።
የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኅይላት ደቡብ ሱዳን እንድትረጋጋ ይረዳል የተባለውን የአንድነት መንግሥት ከመሰሩቱ ሁለት ዓመት አለፈ። ይሁንና የዛሬ ዓመት ምርጫ ታካሂዳለች ተብላ የምትጠበቀው ደቡብ ሱዳን አሁንም ሰላም እንደራቃት ነው። በጎርጎሮሳዊው የካቲት 22፣ 2020 ዓም ነበር የደቡብ ሱዳን ተቀናቃን መሪዎች ሳልቫ ኪርና ርየክ ማቻር የአንድነት መንግስት የመሰረቱት። ባለፈው ማክሰኞ ሁለት ዓመቱን የደፈነው ውል በጎርጎሮሳዊው 2018 ሁለቱ ወገኖች በሀገሪቱ ጦርነቱን ለማስቆም የተስማሙበት ውል ላይ ማሻሻያ የታከለበት ሰነድ ነበር ። ስምምነቱን ሲፈራረሙ በ2013 ዓም በተከፈተው የደቡብ ሱዳን ጦርነት በሺህዎች የሚቆጠሩ ተገድለው ሚሊዮኖች ደግሞ ተፈናቅለው ነበር። ያኔ በተመሰረተው የአንድነት መንግሥት ሳልቫ ኪር በፕሬዝዳንት ሲቀጥሉ ማቻር ደግሞ እንደገና የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ተሾሙ።የሁለቱ መሪዎች የስልጣን ዘመንም በ2023 ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ ለሦስት ዓመት የሚቆይ ነው ተብሎ ነበር ። የደቡብ ሱዳንን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለማስቆም የተደረገው የመጀመሪያው የሰላም ጥረት የከሸፈው በ2016 ፕሬዝዳንት ኪር ፣ማቻርን ከሃላፊነታቸው ሲያነሷቸው በኋላ የቀድሞው የአማጽያን መሪ ማቻር ተመልሰው ጫካ ከገቡ በኋላ ከፕሬዝዳንቱ ታማኝ ኃይሎች ጋር ጦርነት ሲከፍቱ ነበር።በጎርጎሮሳዊው 2011 ከሱዳን ተነጥላ ነጻነትዋን ካወጀች ጊዜ ጀምሮ ዘላቂ ሰላም ማግኘት ባቃታት በደቡብ ሱዳን አሁንም መፈታት ያልቻሉ በርካታ ችግሮች ብዙዎችን ያሳስባሉ።
የጸጥታ ስጋት ደቡብ ሱዳናውያንን እጅግ ከሚያስጨንቁ ጉዳዮች አንዱ ነው።ሄነሪ ኤኖካ በዋና ከተማይቱ በጁባ የሚኖር መምህር ነው።የ40 ዓመቱ ኤኖካ ለዶቼቬለ በሰጠው ቃለ ምልልስ እንዳለው ይህ በሚኖርባት ከተማ በነጻነት እንደልቡ መዘዋወር ይፈልጋል።ይሁንና ታጣቂዎች በየመንገዱ መገኘታቸው ፍርሀት ያሳድርብኛል ብሏል።
«አዎ በነጻነት እንንቀሳቀሳለን ግን ከስጋት ጋር፤መኖሪያህ ስለሆነው ትዘዋወራለህ ሆኖም መቶ በመቶ ግን በነጻነት አንትንቀሳቀስም።መዘዋወር ይቻላል ሰዎች አሉ።ሆኖም በርካታ ማንነታቸው የማይታወቅ ታጣቂዎች በየመንገዱ ይገኛሉ።»
ኤኖኮ ከመጀመሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ በነጻነት መዘዋወር ይቻል እንደነበር ያስታውሳል።ይህ ግን አልዘለቀም የሰላም ስምምነቱ እያለ እንደገና በ2016 ግጭቱ ሲቀጥል ሰላሙ ደፈረሰ። የደቡብ ሱዳን የመጨረሻው የሰላም ስምምነት አሁንም በእንጥልጥል ላይ ነው። በኪር ታማኝ ኃይሎችና በማቻር ሰራዊት መካከል አሁንም ግጭቶች መካሄዳቸው አልቀረም። በሁለቱ መሪዎች መካከል ያለው አለመተማመን አልተወገደም።ለምሳሌ በ2020 ቶንጂና ዋራፕ በተባሉት ማዕከላዊ ከተሞች ወታደሮች በአካባቢዎቹ የሚገኙ አርብቶ አደሮችንና ሌሎች ነዋሪዎች ትጥቅ ለማስፈታት ሲሞክሩ ግጭቶች ተቀስቅሰው ነበር። ትጥቅ የማስፈታቱ ሙሉ ዓላማ ታጣቂ ሚሊሽያዎች በኅብረተሰቡ መካከል ግጭቶችን እንዳያስነሱ መከላከል ነበር ተብሏል።
አምስት ምዕራፎች ካሉት የደቡብ ሱዳን የመጨረሻው የሰላም ስምምነት ውስጥ ሶስት ዋና ዋና ነጥቦች እስካሁን አልተተገበሩም።እነርሱም የደቡብ ሱዳን መልሶ ግንባታ፣ የኤኮኖሚ ተኅድሶ እና ፍትህና ተጠያቂነት የሚሉት አንኳር ጉዳዮች ናቸው።እነዚህ አስፈላጊ ጉዳዮች ስራ ላይ አለማዋላቸው ደግሞ እጅግ እየተባባሰ በሄደ የኤኮኖሚ ችግር ውስጥ በህይወት ለመቆየት ጥረት የሚያደርጉ ዜጎች ላይ መከራውን አብዝቷል። የመመህር ኤኖካ ገቢ ቤተሰቡን መደገፍ አልስቻለውም። የወር ደሞዙ 35 ሺህ የደቡብ ሱዳን ፓውንድ ሲመነዘር ደግሞ 80 ዩሮ ነው። በጁባ የኑሮ ውድነት ሰማይ በመድረሱ ከቤተሰቡ መሠረታዊ ፍላጎቶች አንዳንዶቹን ማሟላት አልቻለም
የደቡብ ሱዳን ዓለም አቀፍ አጋሮችና የፖሊሲ ተንታኞች የሰላም ስምምነቱ ትግበራ መዳከም ምክንያቱ የፖለቲካ ፈቃደኝነት አለመኖር ነው ይላሉ። በደቡብ ሱዳን የአውሮጳ ኅብረት አምባሳደር ክርስቲያን ባደር ይህን ከሚሉት አንዱ ናቸው።
«ውሉ ጥሩ ሳይሆን ቀርቶ አይደለም።ሆኖም መልክም ፈቃደኝነቱ አለመኖሩ ነው ምክንያቱ መልካም ፈቃድ ቢኖር ኖሮ ስምምነትም አያስፈልግም ነበር።የሚፈለገው እንዲ ይሳካ ነበር። የሰዉም ትኩረቱ ሌላ ነገር ላይ ይሆን ነበር።»
እርሳቸው እንደሚሉት ዋናው ችግር በፖለቲከኞች መካከል የሰፈነው አለመተማመን ነው።አምባሳደር ባደር ይህን ቢሉም የደቡብ ሱዳን መንግሥት ግን የሰላም ውሉ እንዲተገበር እየጣርኩ ነው ሲል ይከራከራል።የደቡብ ሱዳን የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ማርቲን ኤልያ ሎሙሮ ለዶቼቬለ በሰጡት ማብራሪያ እንደተናገሩት መንግሥት ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ቢሆንም አሁንምተግዳሮች አሉ። ከመካከላቸው ሚኒስትሩ እንዳሉት በፋይናንስና በጦር መሳሪያ ላይ የተጣለው ዓለም አቀፍ ማዕቀብ የስምምነቱን ትግበራ ከሚያደናቅፉት ጉዳዮች መካከል ናቸው።
«ለመረጋጋት እየታገልን ባለንበት ሰዓት የነዳጅ ዘይት ዋጋ በጣም ወረደብን ።ከዚያም ወደ ፓንቱው ግጭት ገባን። እናም ነዳጁን ሙሉ በሙሉ ለመዝጋት ወሰንን ያም ማለት ያለንን ሁሉ መጠቀም ጀመርን። ሌላ የገቢ ምንጭ አልነበረንም።እርግጥ ነው ከዚህ ሳናገግም በ2013 የተቀሰቀሰው ግጭት የነዳጅ ማውጫ ስፍራዎቹን አወደማቸው።»
ፓንቱ የተባለው ጦርነት ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በአንድ የነዳጅ ዘይት ማውጫ ጉድጓድ ይዞታ ላይ በተነሳ ጸብ በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ በ2012 ዓ.ም. የተካሄደ ጦርነት ነው። እስካሁን ባለው መረጃ ፕሬዝዳንት ኪር በሚቀጥለew ዓመት በሚካሄደው ምርጫ አልሳተፍም ብለዋል። ማቻር ደግሞ በፓርቲያቸው የሱዳን ህዝቦች ነጻ አውጭ ንቅናቄ ውስጥ በተፈጠረ ቀውስ ተጠምደዋል። እርሳቸውን የሚቃወሙ የፓርቲው አባላት ከፓርቲውና ከፓርቲው ጦር መሪነት አንስተናቸዋል ይላሉ።ተቃዋሚዎቻቸው ማቻርን ለደቡብ ሱዳን ተሃድሶ ትኩረት ባለመስጠትና አመድ አዝማድን በመጥቀም ይከሷቸዋል።ማቻር ግን ይህን አይቀበሉም። ከዚያ ይልቅ ተቀናቃኞቻቸው የደቡብ ሱዳንን የሰላም ሂደት ለማስቆም እየሞከሩ ነው ይላሉ ማቻር።ምርጫው እየተቃረበ በመጣበት በአሁኑ ጊዜ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና ምክትል ፕሬዝዳንት ሪየክ ማቻር በደቡብ ሱዳን ሰላምና ፀጥታ ማስፈንና ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል።
የዩክሬን ሩስያ ጦርነትና አፍሪቃ
የዩክሬኑ ጦርነት ከአካባቢው ሀገራት አልፎ በመላው ዓለም ተጽእኖ ማድረጉ ቀጥሏል። ሩስያ ዩክሬንን ድንበር ጥሳ ከገባችና ጥቃትም መፈጸም ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ንሯል። ጭማሪው የአፍሪቃ ሀገራትንም ነክቷል። ኬንያዊው ክሊንተን ምዌንዳ ፣ስራው በሞተር ቢስኪሌት ሰዎችን ማጓጓዝ ነው ።ከዚህ ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ የነዳጅ ዋጋ መጨመር አሳስቦታል። «የ28 ዓመቱ ምዌንዳ እንደሚለው አሁን አንድ ሊትር ቤንዚን 160 የኬንያ ሽልንግ ገብቷል።ይህ በጣም ከፍተኛ ዋጋ ነው። የምጣኔ ሀብታ ባለሞያዎች የዩክሬኑ ጦርነት የነዳጅ ዘይት ዋጋን ከአሁኑም በማናር በአፍሪቃ የዋጋ ግሽበት እንዲጨምር ሊያደርግ እንደሚችል ሲያሳስቡ ነበር። ደቡብ አፍሪቃዊ ዶክስ ዲዞል ጆሀንስበርግ ውስጥ ነጋዴና አርቲስት ነው። እርሱ እንደሚለው የዩክሬኑ ጦርነት የአፍሪቃ ሀገራትን ድሀ ህዝብ እስከ ማስራብ ሊያደርስ ይችላል ይላል ነጋዴው ዲዞል።
«እነዚህ ሀገራት ሲዋጉ ሰዎች ይራባሉ። ምክንያት ሀገራቱ ራሳቸውን እንደ ዓለም አቀፍ ኃያላን ለአፍሪቃ ሀገራት ደግሞ እንደ እናት ሀገራት ሆነው ነው የሚቀርቡት። እናም ወላጆች ሲጣሉ ለልጆች ጥሩ አይደለም።ለኛም በምንም ዓይነት መንገድ ጥሩ አይሆንም።እንቸገራለን ብዮ እፈራለሁ። ችግሩ ሲባባስ የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ ይሄዳል።ኤኮኖሚው ቁልቁል ሲሄድ ህዝቡ ተጨማሪ ዋጋ እንዲከፍል ያደርጋል። »
.የድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ዋጋ ከጨመረ የዋጋ ግሽበት በዓለም ዙሪያ ይከሰታል። ይህ ደግሞ በሀገራት ውስጥ ቀውስ ያስከትላል። የሚሉት ደግሞ ናይጀሪያዊ የምጣኔ ሀብት ባለሞያ ናቸው። በበርካታ የአፍሪቃ ሀገራት እጅግ የተኮሰው የሸቀጦች ዋጋ የሚሊዮኖችን ሕይወት እየፈተነ ነው። ብሪክስ በመባል ከሚጠሩትና ፈጣን እድገት በማስመዝገብ ላይ ካሉ ሀገራት አንዷ የሆነችው ደቡብ አፍሪቃ በጎርጎሮሳዊው 2014 ሩስያ ክሪምያን የግዛቷ አካል ስታደርግ ዝምታን ነበር የመረጠችው።አሁን ግን የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት ሁሉም ወገን እንዲታቀብ አሳስቧል።ብሪክስ በሚል ምህጻር በሚጠሩት በብራዚል፣ሩስያ፣ህንድ፣ቻይናና ደቡብ አፍሪቃ ላይ ጥናት የሚያካሂደው ተቋም ሃላፊና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር ሲፋማንድላ ዞንዲ ጦርነቱ የደቡብ አፍሪቃን ኤኮኖሚ መጉዳቱ አይቀርም ይላሉ።
«ደቡብ አፍሪቃ ከዓለም አቀፍ ኤኮኖሚ ጋር የተሳሰረች ሀገር ናት። ስለዚህ ጦርነቱ የነዳጅ ዘይት ዋጋን በማናሩ ዱቡብ አፍሪቃ ላይ ተጽእኖ አሳድሯል።ዓለም ሲያነጥስ ደቡብ አፍሪቃም ጉንፋን ይይዛታል። »ብለዋል።በጦርነቱ ሰበብ አፍሪቃን የሚጎዳው የነዳጅ ዘይት ዋጋ መናር ብቻ አይደለም በአፍሪቃ ሀገራትና በሩስያ እንዲሁም በዩክሬን መካከል የሚደረገው ከእርሻ ጋር የተያያዘ ንግድ ትልቅ ቦታ የሚይዝ ነው።
በ2020 ዓም የአፍሪቃ ሀገራት 4 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ የእርሻ ምርቶችን ከሩስያ ገዝተዋል።ከመካከላቸው ስንዴ 90 በመቶውን ድርሻ ይይዛል። ግብጽ ግንባር ቀደምዋ የሩስያ ስንዴ ደንበኛ ናት።ሱዳን ናይጀሪያ ታንዛንያ አልጀሪያ ኬንያና ደቡብ አፍሪቃ ከሩስያ ስንዴ የሚያስገቡ ተጨማሪ የአፍሪቃ አገራት ናቸው። በተመሳሳይ ሁኔታ ዩክሬን በ2020 2.9 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የእርሻ ምርት ለአፍሪቃ ሸጣለት። ከምርቶቹ ስንዴ 48 በመቶውን በቆሎ 31 በመቶውን ፣ሱፍ ገብስ እና አደንጓሬ ደግሞ ቀሪውን መቶኛ ይሸፍናሉ።የዩክሬኑ ጦርነት የዋጋ ጭማሪ በማስከተል በምርት አቅርቦቱ ሰንሰለት ላይ ተጽእኖ ሊያደርግ ይችላል ተብሎ ይፈራል። ከዚህ ሌላ ዩናይትድ ስቴትስና አጋሮቿ በሩስያ ላይ የጣሉት ማዕቀብ በአፍሪቃና ሩስያ የንግድ ግኙነቶች ላይ የሚኖረው ተጽእኖም ግልጽ አይደለም።
በሌላ በኩል ከፍተኛ ትምህርታቸውን ዩክሬን የሚከታተሉ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በሺህዎች የሚቆጠሩ አፍሪቃውያን ሁኔታም አሳሳቢ ነው። ብዙዎቹ አሁን ከዩክሬን መውጫ አጥተው ጭንቅ ላይ ናቸው። ዩክሬን የሚኖሩና ከዩክሬንና ሩስያውያን ጋር የሚነግዱ አፍሪቃውያንም ሃሳብ ገብቷቸዋል።
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ