1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተገደሉ የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች

ማክሰኞ፣ መጋቢት 10 2016

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ከሚገኘው የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ታግተው ቆይተው የተገደሉ ሠራተኞች አስክሬን መቀበሩን የሟች ቤተሰብ ለዶቼ ቬለ ተናገሩ ። በአካባቢው በሚንቀሳቀስ ታጣቂዎች ታግተው ከቆዩ 6 የፋብሪካው ሠራተኞች መካከል ለማስለቀቂያ ለእያንዳንዳቸው ተጠይቆ የነበረው ሦስት መቶ ሺህ ብር ከመሰጠቱ በፊት አምስቱ መገደላቸው ተገልጿል ።

Symbolbild Kerze Flamme
ምስል Colourbox

እገታ እና የማስለቀቂያ ቤዛ ጥያቄ ፤ ግድያ

This browser does not support the audio element.

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ከሚገኘው የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ታግተው ቆይተው የተገደሉ ሠራተኞች አስክሬን መቀበሩን የሟች ቤተሰብ ለዶቼ ቬለ ተናገሩ ። በሥራ ላይ እያሉ በአካባቢው በሚንቀሳቀስ ታጣቂዎች ታግተው ከቆዩ ስድስት የፋብሪካው ሠራተኞች መካከል ለማስለቀቂያ ለእያንዳንዳቸው ተጠይቆ የነበረው ሦስት መቶ ሺህ ብር ከመሰጠቱ በፊት አምስቱ መገደላቸው ተገልጿል ። በ1954 ዓ.ም ምርት የጀመረው ይህ ፋብሪካ ከአዲስ አበባ በ110 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው ። 

እገታ እና የማስለቀቂያ ቤዛ ጥያቄ ፤ ግድያ

ከዚህ በፊት በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም አራት መነኮሳት የተገደሉበት፣ በተመሳሳይ ከዚያ ቀደም ብሎ በመተሃራ ስድስት ሰዎች በታጣቂዎች የተገደሉበት የኦሮሚያ ክልሉ ምስራቅ ሸዋ ዞን ባለፈው ሳምንት ደግሞ ከአዲስ አበባ በ110 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውና በኢትዮጵያ የስኳር ኢንዱስትሪ ታሪክ ውስጥ አንጋፋ እና ፈር ቀዳጅ የሆነው የወንጂ ስኳር ፋብሪካ አምስት ሠራተኞች በታጣቂዎች ከታገቱ በኋላ ተገድለውበታል።

ለሀዘን ከተቀመጡበት ተነስተው ያነጋገሩን ከሟቾች መካከል የአንደኛው ቤተሰብ የሆኑ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ግለሰብ የካቲት 29 ቀን 2016 ዓ.ም በተሽከርካሪ ወደ ፋብሪካው የሸንኮራ አገዳ ማሳ በመጓዝ ላይ ሳሉ የተሻለ ገቢ አላቸው ተብለው የተገመቱ ስድስት ሰዎች ታግተው ሌሎች መለቀቃቸውን እንደሚያውቁ እና ስድስቱ ግለሰቦች ታግተው ከተወሰዱ በኋላ ለእያንዳንዳቸው ማስለቀቂያ ቤዛ 600 ሺህ ብር ተጠይቆባቸው እንደነበር ፤ በድርድር 300 ሺህ ብር ለመክፈል ስምምነት ላይ ተደርሶ እንደነበር ገልፀዋል።

"እዚያ አካባቢ ላይ አልፎ አልፎ እንደዚህ አይነት ነገሮች ይከሰቱ ነበር ፤ ሰው የማገት ፣ ገንዘብ የመቀበል ሁኔታዎች ነበሩ። የእኛ ቤተሰቦች ላይ የከፋ መሆኑ ነው ነገሩን በጣም ያከበደው።"

ሠራተኞቹ ለምን ተገደሉ?

ፋብሪካው ለሠራተኞቹ ማስለቀቂያ ገንዘብ እንዲከፍል ተጠይቆ እንደነበር የገለፁት እኒህ የሟች ቤተሰብ ፋብሪካው ያንን ማድረግ እንደማይችል እንደገለፀላቸው ጠቅሰዋል።

ይህንን ተከትሎ የወንጂ ነዋሪዎች ባደረጉት ርብርብ ገንዘብ ተሰባስቦ ሊከፍሉ በተዘጋጁበት ወቅት ፖሊስ እንዳስቆማቸው እና ታጋቾችን ለማስለቀቅ ፋብሪካው የፌዴራል ፖሊስ እና መከላከያን በመጥራቱ ታጋቾች በአገቷቸው ታጣቂዎች መገደላቸውን ገልፀዋል።

እገታ እና ግድያ በኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ ሲፈጸም ይስተዋላልምስል G. Fischer/blickwinkel/picture alliance

"ማስለቀቅ የሚቻልበት ሁኔታዎች ነበሩ። ከተያዙ በኋላ ከባለቤቶቻቸው እና ከእህቶቻቸው ጋር እንዲሁም ፣ ከወንድሞቻቸውና ከሚመለከታቸው ጋር ተገናኝተው የጠየቁት ብር ነበር"

ጉዳዩን በተመለከተ የፋብሪካውን የሥራ ኃላፊዎች ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልሰመረም። የምስራቅ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪን ለማግኘትም ጥረት አድርገን ነበር።

አንድም ሠራተኛ እና የሠራተኛ ቤተሰብ በሥጋት ውስጥ እንዳይወድቅ ሊደረግ ይገባል ያሉት እኒህ የሟች ቤተሰብ ከስድስቱ ታጋቾች የአምስቱ አስክሬን ተገኝቶ ሥርዓተ ቀብር መፈፀሙንም፣ በአሰቃቂ ሁናቴ መገደላቸውንም አረጋግጠዋል።

በምስራቅ ወለጋ 16 ሰዎች ተገደሉ

የወንጂ ስኳር ፋብሪካ አካባቢ አሁን የደኅንነት ሥጋት ውስጥ መሆኑን ግለሰቡ አስታውቀዋል። በተያያዘ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ ዓርብ መጋቢት 6 "ያልታወቁ ሰዎች በመከላከያ ሠራዊት አባል ላይ የፈጸሙትን ግድያተከትሎ የመንግሥት ወታደሮች የበቀል እርምጃ በሚመስል መልኩ በቀበሌው አርሶ አደሮች ላይ በቀበሌው ነዋሪዎች ላይ በከፈተው ጥቃት ከአስራ ስድስት በላይ ንጹሃን ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸውልናል" ሲል እናት ፓርቲ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW