1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተጠናከረዉ ግፊትና ኢትዮ-ኤርትራ

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ግንቦት 23 2013

ጅቡቲ ዛሬ አዲስ አበባ-አስመሮችን  ገሸሽ፣ ገለል፤ ካይሮ-ካርቱሞችን ቀረብ-ደብለቅ የማለቷ ምክንያት ኢትዮጵያ በተለይ ጠቅላይ ሚንስትሯ ከረጅም ጊዜ የጅቡቲ ባላንጣ ከኤርትራ በጣሙን ከኤርትራ ፕሬዝደንት ጋር በመወዳጀታቸዉ ነዉ ባዮች አሉ።ኢትዮጵያ በመዳከሟ ነዉ የሚሉም ብዙ ናቸዉ።አቶ የሱፍ ግን ይሕ ብቻ አይደለም ባይ ናቸዉ።

Infografik Karte Dschibuti Militärbasen Bab el-Mandeb Meerenge EN

በኢትዮ-ኤርትራ ላይ ያየለዉ ግፍትና ጫና

This browser does not support the audio element.

 

ዩናይትድ ስቴትስ በማዕቀብ፣የአዉሮጳ ሕብረት በማስጠንቀቂያ፣ ሱዳን በጦር ኃይል፣ ግብፅ በዲፕሎማሲ ዘመቻና በጦር ኃይል ዝግጅትም በኢትዮጵያና ኤርትራ ላይ የሚያደርጉትን ጫና አያጠናከሩ ነዉ።የኬንያ፣ የዩጋንዳ፣ የብሩንዲ መንግስታት ኢትዮጵያን ገሸሽ፣ሱዳን-ግብፅን ጠጋ እያሉ ነዉ።ከአወዳይ ጫት እስከ መርቲ ብርቱካን-ቲማቲም፣ ከድሬዳዋዉ ሸቀጥ እስከ ወደብ ኪራይ ከኢትዮጵያ የሚላክ-የሚከፈላት ጅቡቲም ባለፈዉ ሳምንት የነግብፅን ጎራ ተቀየጠች።የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግስታት ማዕቀብ ጫናዉን አዉግዘዋል።የአዲስ አበባ ሕዝብም አሜሪካኖችን ባደባባይ ሰልፍ ተቃዉሟል። ከዚያስ?

ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያና በኤርትራ መንግስታትና በየባለስልጣናቸዉ ላይ የምጣኔ ሐብትና አሜሪካ የመግቢያ ፈቃድ (ቪዛ) ማዕቀብ ለመጣልዋ ምክንያት ካደረገችዉ ዋናዎቹ ሶስት ናቸዉ።የትግራይ ክልልን የሚያወድመዉ ጦርነት፣ በጦርነቱ አሜሪካኖች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ይፈፃማል ያሉት ግፍ፣ የኤርትራ ጦርና «መደኛ ያልሆነ» ያሉት የአማራ ክልል ሚሊሺያ በጦርነቱና በሚፈፀመዉ ግፍ መካፈላቸዉ ነዉ።

ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎችን የሚያዉከዉ ግጭት፣ግድያ፣ መፈናቀለም እንዳሳሰባቸዉ የአሜሪካ ባለስልጣናት አስታዉቀዋል።የኢትዮጵያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር በይፋ በሰጠዉ መልስ ማዕቀቡን አሳዛኝ፣ተገቢ ያልሆነና ረጅም ዓመታት ያስቆጠረዉን የኢትዮጵያና የዩናይትድ ስቴትስን ግንኙነት የሚጎዳ በማለት ተቃዉሞታል።

የማዕቀቡ-ምክንያት፣የአፀፋዉ ተመጣጣኝነት በሚዘገብ-በሚተነተንበት መሐል ባለፈዉ ሳምንት የአስመራና የአዲስ አበባ ባለስልጣናትና ደጋፊዎቻቸዉ በሁለቱ ሐገራት ላይ «ጠላት በዛ» እያሉ ነዉ።ኢትዮጵያ ከራስ ካሰር እስከ ራስ ዱሜራ የተዘረጋዉ የቀይ ባሕር ሙሉ ባለቤት የነበረችበት ዘመን በ1983 ሲዘጋ አብሮ የተዘነጋዉ የቀይ ባሕር ፖለቲካም እንዳዲስ አጎንቁሎ «ጠላት ለመብዛቱ» እንደምክንያት እየተጠቀሰ ነዉ።ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያ የተጠናቀቀዉ የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ የብልፅግና ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ ባወጣዉ መግለጫም ለጫና፣ግፊት፣ ቅጣት፣ መገለሉ ምክንያት የጠቀሰዉ የቀይ ባሕር ፖለቲካን ነዉ።

ምስል Egyptian President Office/Zuma/picture alliance

 የካፒታሊስቱን ርዕዮተ ዓለም በግልፅ አዉግዞ ሶሻሊስታዊዉን መስመር የተቀየጠዉ የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ወይም የደርግ መንግስት ኢትዮጵያ በጠላቶች መከበቧን በተደጋጋሚ ሲያስታዉቅ፣ ሲያስረዳም ነበር።

የከበባዉ ሰበብ ምክንያት ከቀዝቃዛዉ ጦርነት እስከ ርዕዮተ-ዓለም ተቃርኖ፣ ከምጣኔ ሐብት ሽሚያ እስከ ቀይ ባሕር ባለቤትነት እንደሚደርስ ምክንያት ከምሳሌ እየጠቀሰ ያስተነትንም ነበር።በሻዕብያ-ወያኔ ጥብቅ ወዳጅነት ዘመን የተዘነጋዉ፣ በሻብዕያ-ወያኔ ጠላትነት ዘመን ደግሞ ለ23 ዓመት «የግመል ዉሐ መጠጫ» ይሆናል ሲባል የነበረዉ ቀይ ባሕር ዳግም እንደ ድሮዉ ዋና ምክንያት መሆኑ ለታዛቢ በርግጥ የሚያስተዛዝብ ነዉ።

የቀይ ባሕር ዳርቻን ተወልደዉ አድገዉበት፣ የቀይ ባሕር ፖለቲካን ኖረዉ-ተንትነዉ የሚያዉቁት የፖለቲካ ተንታኝና ደራሲ የሱፍ ያሲን የቀይ ባሕር «ጣጣ» ዛሬም ባንድ ወይም በሌላ መልኩ ኢትዮጵያን መንካቱን «እዉነት» ይሉታል።ለአሜሪካኖች ማዕቀብና ለሌች ጫና ቀይ ባሕር እንደምክንያት መጠቀሱትን ግን «ሊሆን የማይችል።»

                                         

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ «ሕዳሴ» ያለችዉን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ መገንባትዋን ግብፅና ሱዳን ይቃወሙታል።የተቃዉሟቸዉ ምክንያት ግልፅ ነዉ። ግድቡ ወደ ሁለቱ ሐገራት የሚፈሰዉን የዉሐ መጠን ይቀንሳል የሚል።ሶስቱ ሐገራት ዉዝግቡን ለመፍታት ላለፉት 11 ዓመታት ያደረጉት ድርድር ያመጣዉ ዉጤት የለም።

ግብፅና ሱዳን  ባንድ ወገን ድርድር እያሉ በሌላ በኩል ደግሞ ለተቃዉሟቸዉ ድጋፍ ለማሰባሰብ ከስለላ-ዲፕሎማሲዉ ዘመቻዉ አልፈዉ የጦር ኃይል ቁርቁስ-ዛቻም ከፍተዋል።በተለይ ሱዳን በመቶ ኪሎ ሜትር የሚቆጠር የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያን ግዛትን መያዝዋን የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ አስታዉቋል፤ አዉግዟልም።

ግብፅ በበኩሏ ለወትሮዉ ከኢትዮጵያ ጎን የሚቆሙ የሚባሉ የአፍሪቃ ሐገራትን ቀስ በቀስ ከእቅፏ እያስገባች ነዉ።ግብፅ ባለፈዉ መጋቢት ከብሩንዲ፣ሚዚያ ላይ ከዩጋንዳ፣ ግንቦት ደግሞ ከኬንያ ጋር የወታደራዊ፣ የስለላና የጋራ ወዳጅነት የተባሉ ዉሎችን ተፈራርማለች።ኬንያና ዩጋንዳ ከግብፅ ጋር መዋዋላቸዉ በርግጥ ብዙ ታዛቢዎችን ማነጋገሩ አልቀረም።ባለፈዉ ሐሙስ ጅቡቲም የካይሮ-ካርቱሞችን «ክለብ» መቀየጧ ደግሞ ከማነጋገርም በላይ አስገራሚ ነዉ።

ትንሺቱ የደቡብ ቀይ ባሕርና የአደን ባሕረ ሰላጤ መጋጠሚያቱ ሐገር ጅቡቲ ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያና የሶማሊያ፣ የኢትዮጵያና የግብፅ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ ዉጊያ፣ ፍትጊያ ሽኩቻ ተለይቷት አያዉቅም።አቶ ዩሱፍ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር በ1977 ጅቡቲ ነፃ ስትወጣ በኢትዮጵያና ሱማሌያ፣ በኢትዮጵያና ግብፅ መካከል የነበረዉን የጦር-ዲፕሎማሲ፣ የስለላ-ምጣኔ ሐብት ሽኩቻን ያስታዉሳሉ።

                                    

ነበር።በዚሕም ምክንያት ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር ትሻኮት፣ከሱዳን ጋር ትፋጠጥ፣ ከሶማሊያ ጋር ትወጋ ከኤርትራ ጋር ጅቡቲ የአረብ ሊግ አባል ሆናም አንድም ጊዜ ኢትዮጵያን በግልፅ ተቃርና ወይም ተጋፍታ አታዉቅም።አትችልልምም ነበር።

ጅቡቲ ዛሬ አዲስ አበባ-አስመሮችን  ገሸሽ፣ ገለል፤ ካይሮ-ካርቱሞችን ቀረብ-ደብለቅ የማለቷ ምክንያት ኢትዮጵያ በተለይ ጠቅላይ ሚንስትሯ ከረጅም ጊዜ የጅቡቲ ባላንጣ ከኤርትራ በጣሙን ከኤርትራ ፕሬዝደንት ጋር በመወዳጀታቸዉ ነዉ ባዮች አሉ።ኢትዮጵያ በመዳከሟ ነዉ የሚሉም ብዙ ናቸዉ።አቶ የሱፍ ግን ይሕ ብቻ አይደለም ባይ ናቸዉ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐባይ አሕመድ ድሬዳዋ ካደጉ፤ከተማሩ፣ አማርኛን አቀላጥፈዉ ከሚናገሩት ከጅቡቲዉ ፕሬዝደንት ኢስማኤል ዑመር ጌሌ ጋር ያደረጉት ዉይይት የኢትዮጵያ የኢሳ ሶማሌዎች የራሳቸዉ ክልል እንዲኖራቸዉ የጅቡቲዉ መሪ ላነሱት ጥያቄ የተሰጣቸዉን መልስ ያስታዉሳሉም።

                               

የጅቡቲ ፖለቲከኞችን  ሥራና ሴራ በቅርብ የሚዉቁ እንደዘገቡት ፕሬዝደንት ጌሌ ዘመነ ስልጣናቸዉን በምርጫ እስኪያራዝሙ ድረስ በይደር የያዙትን ዶሴ ማገላበጥ የጀመሩት በምርጫዉ 97 ከመቶ በላይ ድምፅ ባገኙ ማግስት ነዉ። ሚያዚያ።ሚያዚያ 28፣ 2021 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) በፕሬዝደንቱ ግብዣ መሠረት የግብፁ መከላከያ ሚንስትር ጄኔራል መሐመድ ዘኪ፣ የጦር ኃይል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹምና ሁለት የሱዳን የጦር መኮንኖች አስከትለዉ ጅቡቲ ገቡ።

የግብፅ መከላከያ ሚንስትር የመሩት የመልዕክተኞች ጓድ ከጅቡቲዉ ፕሬዝደንት፣ ከጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ከዘካሪያ ሼኽ ኢብራሒም፣ ከጅቡቲ የስለላ መስሪያ ቤት ኃላፊ ከሐሰን ሰይድ ኸይሬ ጋር ያደረጉት ዉይይት እየዳበረ፣ እየሰፋ፣ እየበሰለ መጥቶ የግብፅ ፕሬዝደንት የማርሻል አብዱል ፈታሕ አል ሲሲን ጉብኝትን አፈራ።

ምስል Getty Images/AFP/E. Soteras

ጅቡቲን አንድም የግብፅ መሪ ረግጧት አያዉቅም ነበር።አል ሲሲ ባለፈዉ ሳምንት አደረጉት።ከርዕሠ-ከተማ ጅቡቲ 7 ኪሎ ሜትር በሚርቀዉ ዳመርጆግ ላይም የግብፅ የጦር ሠፈር እንዲከፈት ከፕሬዝደንት ኢስማኤል ዑመር ጌሌ ጋር ተስማሙ።ሐሙስ።

አል ሲሲ ጅቡቲ ላይ ጦር ሠፈር ሲከፍቱ፣ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የኢትዮጵያና የጅቡቲን ግንኑነት «ያሻሽላል» የተባለዉን የአዳማ-አዋሽን ፈጣን መኪና መንገድ ሥራን አስጀመሩ።ትናንት።ጠቅላይ ሚንስትሩ የሶማሌዎች ተረትን ጠቅሰዉ ከማዕቀብ እስከ ጦር ሠፈር ምስረታ የደረሰዉን ጫናና ግፊት  «ጩኸት» አሉት።ከአሜሪካኖች ማዕቀብ እስከ ግብፅ-ሱዳኖች የጦር ኃይል ግፊት የደረሰዉን ተፅዕኖ የአዲስ አበባ ሕዝብ ትናንት ባደባባይ ሰልፍ አዉግዟልም።

 በ1970ዎቹ የያኔዉ የኢትዮጵያ መንግስት ሕዝቡን በየአደባባዩ እያሰለፈ «ኢምፔሪያሊዝም» እና «ፔትሮ ዶላር ያሰከራቸዉ» የሚላቸዉን የዓረብ መንግስታትን ያስወግዝ፣ያስረግም ነበር።ዉግዘት ርግማኑን የሚከታተሉ የግብፅ ጋዜጠኞች የሐገራቸዉን ፕሬዝደንት አንዋር አሳዳትን ጠየቋቸዉ አሉ።የኢትዮጵያ ዛቻ ግብፅን ያሰጋት ይሆን» የሚል ዓይነት ጥያቄ።ሳዳት መለሱ «ኢትዮጵያ ጠቧ ከኛ ጋር አይደለም ከአሜሪካ ጋር እንጂ።«የምሰጋዉ የኢትዮጵያ ጦር አሜሪካን ለመዉጋት በኛ በኩል ከዘመተ እንዳይረግጠን ነዉ---ብለዉ።

ምስል Reuters

ግብፆች እንደ ፖለቲካ ዲፕሎማሲያቸዉ ሴራ ሁሉ ፌዘኞች ናቸዉም ይባላል።የትናንቱን የአዲስ አበባዉን ሠልፍ-ዉግዘት ምን እንዳሉት ገና አልሰማንም።ግብፅና ሱዳን የጋራ የጦር ልምምድ መጀመራቸዉ ግን ተዘግቧል

ኢትዮጵያ መንግሥት መግለጫ፣ የከያኒዎች መፈክር፣ የአዲስ አበቦች ሰልፍ፣ዉግዘት ለማዕቀብ፣ ዲፕሎማሲ ዘመቻ፣ ለጦር ትንኮሳ፣ ልምምዱ በቂ አፀፋ ይሆን?

የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ የብልፅግና ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በሰሙኑ ስብሰባዉ ፓርቲዉ የኢትዮጵያን «ሰላምና ብልፅግና ለማረጋገጥ» ባለዉ መርኹ እንደሚቀጥል አስታዉቋል።እስካሁን የነበረዉ መርሕ እስካሁን የነበረዉን ጦርነት፣ ግጭት፤ ሁከት፣ ክፍፍል፣ ከዉጪ የሚደረገዉን መገለል፣ ማዕቀብ ዛቻና ጫና አለማስቀረቱ እየታወቀ እንዲቀጥል መወሰኑ በርግጥ አሳሳቢ ነዉ።

                                           

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW