1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተፈናቃይ ተመላሾች ሮሮ

ዓርብ፣ ግንቦት 9 2016

ከኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞኖች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ከነበሩና ወደቀያቸው የተመለሱ ዜጎች አስፈላጊው የግብርና ግብዓት ባለመሟላቱ ወደ ስራ መግባት አልቻልንም አሉ፣ የመኖሪያ ቤቶቻቸውም ባግባቡ እንዳልተገነባ ናግረዋል። የኦሮሚያ ክልል “ቡሳ ጎኖፋ” በበኩሉ ለተመላሾች የግብርና ግብዓት እንዲቀርብና የተጎዱ ቤቶች እንዲጠገኑ እተደረገ ነው ብሏል።

ፎቶ ማህደር፤ ከወለጋ ዞኖች የተፈናቀሉ ዜጎች
ፎቶ ማህደር፤ ከወለጋ ዞኖች የተፈናቀሉ ዜጎች ምስል Negassa Desalegn/DW

ከአማራ ክልል ወደ ኦሮምያ ክልል የተመለሱ ተፈናቃዮች ሮሮ

This browser does not support the audio element.

የተፈናቃይ ተመላሾች ሮሮ

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞኖች በነበሩ ግጭቶች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ከነበሩና አሁን እንደገና ወደ ቀድሞ ቀያቸው የተመለሱ ተፈናቃች አስፈላጊው የግብርና ግብዓት ባለመሟላቱ ወደ ስራ መግባት አልቻልንም አሉ፣ የመኖሪያ ቤቶቻቸውም ባግባቡ እንዳልተገነቡ ነው የገለፁት፣ የኦሮሚያ ክልል “ቡሳ ጎኖፋ” በበኩሉ ለተመላሾች የግብርና ግብዓት እንዲቀርብና የተጎዱ ቤቶች እንዲጠገኑ እተደረገ ነው ብሏል፣ አንዳንድ ተፈናቃዮች ደግሞ ወደ ቦታቸው ለመመለስ ቢፈልጉም “እንድንመለስ የሚጠይቀን የለም” ይላሉ፡፡

ከኦሮሚያ ክልል በፀጥታ ችግር ምክንያት ተፈናቅለው በአማራ ክልል ከቆዩ ተፈናቃዮች መካከል የተወሰኑት የሁለቱ ክልል መንግስታት በደረሱበት የጋራ ስምምንት መሰረት ወደ ቀድሞ ቀያቸው መመለስ ጀምረዋል፡፡ አንዳንዶቹ ወደ ቦታቸው ከተመለሱ በኋላ አንዳንድ ሁኔታዎች እንዳልተመቻቹላቸው ለዶይቼ ቬሌ አመልክተዋል፣ በተለይ የመኖሪያ ቤት ችግሮችና የግብርና ግብዓት አልተሟላም ይላሉ፡፡ አስተያየታቸውን ከሰጡን መካከል አንዱ፣

“... መሬታችንም፣ ንብረታችንም እያገኘን አይደለም፣ ከመጣን ወደ ሶስት ወራት እያስቆጠርን ነው፣ መጠለያ ውስጥ ነው ያለነው፣ የግብርና መሳሪያ ከመቆፈሪያ ጀምሮ አልተሰጠንም፣ የግብርና ግብዓትም አልቀረበልንም ዘርም፣ ምንም አቅርቦት የለም፣ በምዕራብ ወለጋ ቶሌ ነው የምንነኖረው፡፡፣ ”

ሌላ በዚሁ በምዕራብ ወለጋ ዞን ቶሌ በተባለ አካባቢ በመጠለያ ጣቢያ እንደሚኖሩ የገለፁልን ሌላ ተመላሽም በተመሳሳይ የግብርና ግብዓትም ሆነ የመኖሪ ቤት ችግር እንዳለባቸውገልጠዋል፡፡ በደብረብርሐን መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃ ደግሞ ወደነበሩበት ቦታ ለመመለስ ምዝገባ እንዳደረጉና ፈቃደኛ ያልሆነ ተፈናቃይ ደግሞ እርዳታ እንደሚቋረትበት ተነግሮታል ብለዋል፣ ከዚህ በፊት እንዲሄዱ ተመዝግበው ያልሄዱ ተፈናቃዮች እርዳታ ተቋርጦባቸዋልም ብለዋል፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን ጃሪ ቁጥር 1 የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃይ ደግሞ ወደ መጡበት ለመመለስና የግብርና ስራ ለመጀመር ቢፈልጉም “የሚሰማን አጣን” ይላሉ፡፡ በያዝነው የክረምት ወቅት አምርተን በቀጣዩ ዓመት ራሳችን ለመቻል ፍላጎት ቢኖረንም ወደ ቦታችን የሚመልሰን አካል አልተገኘም ሲሉ ነው ቅሬታቸውን ያቀረቡት፡፡ በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ወለጋ ዞን ቡሳ ጎኖፋ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ነፀነት ዓለማየሁ የግብርና ግብዓት እንዲመጣ ጥያቄ ለክልል ቢያቀርቡም እስካሁን ምላሽ እንዳላገኙ ገልጠዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ቡሳ ጎኖፋ ኃላፊ አቶ ሞገስ እዳዬ የመኖሪያ ቤትን እስመልክተው ለዶይቼ ቬሌ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

“... ቤት ያላቸው ገብተዋል፣ አንዳንድ ጉዳት የደረሰባቸው ቤቶች ደግሞ ህዝቡ በአቅሙ እየሰራው ነው፣ አንዳንድ አካባቢ፣ በብዛት አማራ የተፈናቀለበት አካባቢ ያሉት የኦሮሞዎች ቁጥር አነስተኛ የሆነበት ሁሉንም ቤቶች ለመስራት ለመስራት ከአቅማቸው በላይ የሆነባቸው አሉ፣ ያም ሆኖ አልተቋረጠም፣ እየሰሩላቸው ነው፣ እኛም ክረምት ስለሚገባ በመጠለያ ያሉ ከመጠለያ ይውጡ ብለን አቅታጫ አስቀምጠናል፡፡” ነው ያሉት፡፡ እንደ አቶ ሞገስ የግብርና ግብዓቶችንና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ተመላሾች በልዩ ሁኔታ ብድር የሚገኙበት ሁኔታ እንደሚመቻችላቸው አቶ ሞገስ አመልክተዋል፡፡

ፎቶ ማህደር፤ በጃራ ካምፕ የሚገኙ ተፈናቃዮች አማራ ክልል ምስል Alemenw Mekonnen/DW

“... ግብርና ላ ያስቀመጥነው አቅታጫ የአካባቢው ህዝብ በማረስ እንዲተባበራቸው፣ እያደረግን ነው፣ ቀደም ሲል ያውቋቸው ከነበሩ ሰዎች ጋርም እየተጋገዙ ተመላሾች ስራ ጀምረዋል፣ የግብዓት ችግር ግን አጋጥሞናል፣ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ከፌደራሉ ግብርና ሚኒስቴር ድጋፍ ጠይቀን ምላሽ አላገኘንም፣ ምላሽ እየጠበቅን ነበር ያ አልተሳካም፣ የመጨረሻ አማራጭ ግን ጥያቄውን ለኦሮሚያ ክልል መንግስት አቅርበን  ግብዓት በብድር እንዲሰጣቸው ማድረግ ነው፣ በተለይ  ቶሌ አካባቢ ያሉ ተመላሽ አርሶ አደሮች ግብዓት በሰፊው ይፈልጋሉ፣ ክልሉ በግብዓት ብድር ላይ ቀጥታ ግዥ እንጂ ብድር አይፈቅድም ፣ ለተመላሾች ግን በልዩ ሁኔታ ብድር እንዲመቻች እየሰራን ነው፡፡”   በማለት ነው አቶ ሞገስ ያስረዱት፡፡

እንደ አቶ ሞገስ በሁለት ዙር በመንግስት ደረጃ እስካሁን ወደ 3 ሺህ ተፈናቃች ወደ ኦሮሚያ ክልል ተመልሰዋል፣ በግላቸው ደግሞ ከዚህ ቁጥር የማያንሱት መመለሳቸውንም አብራርተዋል፡፡ ቀሪ ተፈናቃዮችን ለመቀበልም የኦሮሚያ ክልል ዝግጁ ሆኖ እየጠበቀ እንደሆነ ኃላፊው ጠቁመው 3ኛው ዙር ተፈናቃዮችን የመመለስስራ በቅርቡ እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡ የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል በቅርቡ በሰጡት መግለጫ ተፈናቃዮቹን ወደ ኦሮሚያ ክልል  የመመለስ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ከኦሮሚያና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የተፈናቀሉ ወደ 622 ሺህ ያክል ተፈናቃዮች በአማራ ክልል ይገኛሉ፡፡

ዓለምነው መኮንን

አዜብ ታደሰ 

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW