የተፈናቃዮች ሁኔታ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል
ዓርብ፣ ሰኔ 30 2015
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ተፈናቅለው ከነበሩት 475ሺህ ዜጎች ወደ ቀአቸው መመለሳቸውን የክልሉ መንግስት ገልጸዋል፡፡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ታሲሳ ከዚህ ቀደም በሰጡን ማብራሪያ ከተለያዩ የምዕራብ ወለጋ ዞን ወረዳዎች የተፈናቀሉ ዜጎች በባምባሲ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። የተፈናቀሉ ዜጎች ለመመስ ስጋት ስነበራቸው በመጠለያ ጣቢያ እንዲቆዩ መደረጉንም ገልጸዋል። 22ሺህ የሚደርሱ ዜጎች ከምዕራብ ወለጋ ተፈናቅለው በክልሉ ባምባሲ ይገኛሉ። ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አህመድ በህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ በሰጡት ማብራሪያ በሚሊዩን የሚቆጠሩ ዜጎች አሁንም ተፈናቅለው እንደሚገኙ ተናግረዋል። የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባትና ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ማቋቋም እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደየቀአቸው ተመልሰው ተደራጅተው መኖር አለባቸው ብለዋል። ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጉልሶ እና ባቦ ጋምቤል የተባሉ ወረዳዎች የተፈናቀሉ ወደ 22ሺህ የሚደርሱት ዜጎች ዛሬም በአሶሳ ዞን ባምባሲ ወረዳ በተዘጋጀው መጠለያ ጣቢያ ይገኛሉ። ከጥቅምት 2013 ጀምሮ ከባቦ ጋምቤል የተፈናቀሉና በባምባሲ የሚገኙ አቶ ሰይድ የተባሉ ነዋሪ የተፈናቀሉበት አካባቢ ዘላቂ ሰላም ሰፍኖ ዕርቅ ከወረደ ወደቀያቸው እንደሚመለሱ ተናግረዋል። ሆኖም በሚገኙበት መጠለያ ጣቢያ በትናትናው ዕለት ሰብአዊ ድጋፍ እንደተሰጣቸውም ጠቁመዋል።
ለሁለት ዓመት ያህል በመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ አቶ ማዕረጉ የተባሉ ነዋሪም በሰጡን አስተያየት ከዚህ ቀደም መኖሪያ ቤታቸውን ጨምሮ ንብረታቸው በሙሉ በመውደሙ እንዲሁም አስተማማኝ የጸጥታ ሁኔታ ባለመኖሩ መመለስ እንደማይፈልጉ ነው የተናገሩት። ንብረት ያቃጠሉ፣ በሰው ላይም ጉዳት ያደረሱ አካላት ለሕግ ባለማቅረባቸው ወደ ቀድሞ ቀያቸው ለመመለስ ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል። የነበሩበት ወረዳ የሚገኘው አብዛኛው የነዋሪው ንብረት መቃጠሉንና አርሶ አደሩ በመሸሹ በአካባቢው የግብርና ሥራ ለሁለተኛ ዓመት አለመሠራቱንም ገልጸዋል።
የምዕራብ ወለጋ ዞን የአደጋ ስጋት ጽ/ቤት/ ቡሳ ጎኖፋ ኃላፊ ወ/ሮ ነጻነት አለማየሁ ከዞናቸው በርካታ ቁጥር ያለው ነዋሪ ተፈናቅሎ እንደነበር ገልጸዋል። ከባቦ ጋምቤል፣ ቤጊና ቆንዳላ የተባሉ ወረዳዎች ሰዎች ተፈናቅለው እንደነበር በማመልከትም ሰላም በሰፈነባቸው ስፍራዎች ወደ 14 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ከዚህ በፊት ወደ ቆንዳላና ቤጊ ወረዳዎች መመለሳቸውን ተናግረዋል። በባቦ ጋምቤልና ጉልሶ የተፈናቀሉ ዜጎችን ከወረዳና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር በመነጋገር የጸጥታ ችግሮች ሲፈቱ ይመለሳሉም ብለዋል። በምዕራብ ወለጋ እና የተለያዩ የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች በነበረው የጸጥታ ችግሮች ወደ 700 ሺህ የሚደርሱት ተፈናቅለው እንደነበር ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል።
ነጋሳ ደሳለኝ
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ