«የምግብ እርዳታ ከተሰጠን 2 ወራት አለፉ» ተፈናቃዮች
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 6 2018
በአማራ ክልል ሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች ያሉ ተፈናቃዮች፣ በነዳጅ እጥረት ምክንያት ወርሃዊ የምግብ እርዳታ መቋረጡን ገልጸዋል። በሁለቱም ዞኖች ከ60 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች የሚገኙ ሲሆን፣ ባለፉት ሁለት ወራት ቀለብ እንዳልተሰፈረላቸው ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የዞንኖቹ የሥራ ኃላፊዎች ቅሬታውን አስተባብለዋል። በነዳጅ እጥረት ምክንያት የተወሰነ መዘግየት ቢኖርም፣ እርዳታው እየደረሰ መሆኑን ግን የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ስራአመራር ኮሚሽን አስታዉቋል።
በአማራ ክልል ሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በነዳጅ እጥረት ምክንያት ወርሃዊ የምግብ እርዳታ ካቆመ ሁለት ወራት መቆጠሩን በመግለጽ ቅሬታቸውን ገለጹ። በሁለቱም ዞኖች ከኦሮሚያ ክልልና ከሌሎች አካባቢዎች ተፈናቅለው ስድስት ዓመታትን በመጠለያ ጣቢያና ከማህበረሰቡ ጋር የሚኖሩ ቁጥራቸውከ60 ሺህ የሚበልጥ ተፈናቃዮች አሉ። በደቡብ ወሎ ዞን ጃሪ፣ መካነ ኢየሱስ እና ቱርክ ካምፕ መጠለያ ጣቢያዎች የሚኖሩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ባለፉት ሁለት ወራት በየወሩ የሚሰፈርላቸው ቀለብ እንደተቋረጠ ይናገራሉ።
"ነዳጅ የለም፣ በነዳጅ ተመሃኝን እንጂ በሶስት ወር አራት ወር ነው እርዳታው የሚመጣው። አሁን ግን ነዳጅ ጠፋ አለን በቃ። አሁንም እንግዲህ ተስፋችንን አስቆርጠው አስቀመጡን። ረሃብ አለቀን ምግብ ስጡን። ረሃብ አለቀ። ህፃናቱ፣ ሽማግሌው እንዳለ ረሃብ አለቀ።"
"የናፍጣ መጥፋቱ ያው ደግሞ አስበው እንግዲህ እዛ ላይ አቅርቦት ከሌለ እዛ ካምፕ ውስጥ ተንቀሳቅሶ ወይም ሰው ቀን ስራ አይሰራ፣ ስራ የለም፣ እንደ ልብ አይሄድና በጣም አስቸጋሪ ነው።"
በሰሜን ወሎ ዞን ትልቁ የሀገር ውስጥ ስደተኞች መጠለያ የሆነው የጃራ መጠለያ ጣቢያ ነዋሪዎችም ምክንያቱ የነዳጅ እጥረት ማጋጠሙ ነው ተብለን የምግብ ድጋፍ ከተቋረጠ ሁለት ወር እንዳለፈባቸው አቶ አህመድ አሊ ገልጸዋል።
"አሁን ማህበረሰቡ በጣም ለትልቅ ችግር ተጋልጦ ነው ያለው። በነዳጅ እጥረት ምክንያት ነው አሉ። ጠይቄ ነበር ዛሬም ጠዋት ጠይቄ ነበር። በነዳጅ እጥረት ምክንያት ነው መኪና ልናገኝ አልቻልንም አሉ። ያው ወርሃዊ ሬሽን መጋቢት አልፎ ሚያዝያም እንግዲህ ዛሬ ስድስት ቀን ነው። በወር በወር የሆነች ነገር ጣል እየተደረገለት ነበር ህይወቱን እያቆየ ያለው። እያችም ስትቋረጥ ደግሞ እንግዲህ አስበው በጣም ከፍተኛ አደጋ ላይ ነው ያለው ሰው።"
የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር አደጋ መከላከልና ስራ አመራር ኮሚሽን ተጠሪ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጀማል ይመር ተፈናቃዮቹ ያቀረቡት ቅሬታ ተቀባይነት የሌለው ነው፤ የምግብ ድጋፉን በየወሩ አድርሰናል ይላሉ።
"ሁለት ወር አልሆናቸዉም፣ አሁን ገና መቶላቸው ገና መሸፈናቸው ነው። እርዳታው እንደ ልብ እጥረት እንዳይኖር አለ ሁለት ወር አልሆነም። ሁለተኛ ያው ቀጥታ ፌደራልም ስለሆነ በየተቋሙ ተለይቶ ነዳጅ ስለሚያስፈልጋቸው አሁን ቅድሚያ የሚሰጥ ቅድሚያ ተሰጥቶ ነው እንጂ በነዳጅ ምክንያት የተስተጓጎለ የለም። ግን አሁን ገና አንድ ወር ሊሆናቸው ነው።"
ተፈናቃዮቹ በበኩላቸው በየወሩ ተከታታይ የሆነ የምግብ ድጋፍ ደርሶን አያውቅም ሲሉ ነው የሚገልጹት።
"ለማን ነው የሚሰጡት? እኛ አልደረሰንም። ምንም ነገር! አሁን የዉጭ ድርጅት የለም፣ ብር የሚሰጥ አካል የለም። እህሉ በወር መጥቶ አይሰጠንም። እንደው በችኮላ መጣ ከተባለ በሁለት ወር፣ ከዛ በቃ ያው ሶስት ወር አራት ወር ነው የሚመጣው። መቼ በወር በወር እዚህ አግኝተንም እናውቅ እንደሆነ ማህበረሰቡን መጥታችሁ አትጠይቁም?"
የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ስራ አመራር ኮሚሽን ተጠሪ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አለሙ ይመር በበኩላቸው የምግብ ድጋፉ ምንም አይነት መዘግየት ሳይኖርበት ለተፈናቃዮቹ እየደረሰ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
"አይ እኛ እስካሁን በነዳጅ እጥረት የቆመብን የእርዳታ የለም። አሁን ነዳጅእንደ ሀገር እጥረት አለ አዎ ይታወቃል። ግን እንደ እኛ ደግሞ የለም። እንደኛ ሃብት ለማምጣት፣ ለማምጣት የገጠመ ችግር የለም። ደርሷል፣ ከአቅም በላይ ነው አለ በቂ። ተየተቋረጠ የለም ምንም ተቋርጦ አያዉቅም በየወሩ ።"
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ስራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር የሆኑት ወይዘሮ ሰርካዲስ አታሌ በበኩላቸው አለም አቀፍ የነዳጅ አቅርቦት እጥረት በረድኤት ስራ እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ ቢኖረውም ከተወሰነ መዘግየት ውጭ ግን በአማራ ክልል ምንም የፈጠረው መስተጓጎል የለም ብለዋል።
"በማናቸውም እንቅስቃሴ ላይ ወይም መጓጓዝ ላይ እንደተፈጠረው ተጽዕኖ በሰብአዊ ድጋፍ ላይም ተጽዕኖ አለው። እንደ ሌላው ሁሉ የተንዛዛ ሁኔታ አለ። በተለየ መንገድ የጎዳው ግን አይደለም። እንደማንኛውም አካል ማለት ነው። አሁን በልዩ ሁኔታ ይህ ጉዳት ቢኖርም ደግሞ የክልሉ መንግስት በልዩ ሁኔታ ለሰብአዊ ድጋፍ ቅድሚያ እንዲሰጥ በተገኘው እድል ነዳጅ በመጣ ጊዜ ከሌሎች በቅድሚያ ነዳጅና ማዳበሪያ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው የሚገኘውን ማለት ነው። በዚህ አግባብ እየደረሰ ነው፤ ቢዘገይም ግን ይደርሳል።"
ኢሳያስ ገላው
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ታምራት ዲንሳ