1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተፈናቃዮች እሮሮ እና የሰላም ጥሪ

ሰኞ፣ ጥር 22 2015

የየአከባቢዎቹን ሰላም በማስፈን ወደ ቀያያችሁ እንመልሳችኋለን የሚል ቃል ቢገባልንም ሲፈጸም አናይም ይላሉ ተፈናቃዮቹ። ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሁን አንጻራዊ ሰላም መኖሩን ያስረዱት የክልሉ ባለስልጣን ግን ወደ ሌላ ክልል ከተፈናቀሉት ይልቅ ከኦሮሚያ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ተፈናቅለው ያልተመለሱት ዜጎች ጉዳይ ነው የሚያሳስበን ይላሉ፡፡

Äthiopien Vertriebene Menschen in Mendi
ምስል DW/N. Dessalegn

የተፈናቃዮች እሮሮ እና የሰላም ጥሪ

This browser does not support the audio element.

በ2011 እና በ2013 ዓ.ም. ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከተለያዩ ወረዳዎች ተፈናቅለው ምእራብ ወለጋ ማናሲቡ መንዲ የሚገኙ ተፋናቃዮች መንግስት የሰላም አስተማማኝነትን አረጋግጦ ወደ ቀዬያቸው እንዲመልሳቸው ጠየቁ፡፡ የሰላም እጦት አፈናቅሎን ኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ውስጥ ድጋፍ እንኳ በበቂ ሁኔታ በማይቀርብበት ሁኔታ ለዓመታት የመከራ ህይወትን እየመራን ነው ያሉት ተፈናቃዮቹ፤ ተፈናቅለው የተጠለሉበት አከባቢም የፀጥታ ችግሩ ተመሳሳይ በመሆኑ ተንቀሳቅሶ መስራትም ፈተና ሆኖብናል እያሉ ነው፡፡ የሁለቱ ክልሎች ባለስልጣናት በበኩላቸው በአከባቢዎቹ አሁን የተሻሻለ የፀጥታ ሁኔታ በመኖሩ ተፈናቃዮቹን የመመለስ ስራ ቅድሚያ ትኩረት ያገኘ ጉዳይ ሆኖ ወደ ተግባር ተገብቷል እያሉ ነው፡፡ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን ሴዳን ወረዳ ቆሮንጮ አከባቢ ሚያዚያ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. በጉሙዝ ታጣቂዎች በተነጣጠረ ጥቃት ከ20 በላይ ሰላማዊ ዜጎች በአንድ ቀን መገደላቸውን ተከትሎ ወደ መንዲ የተፈናቀሉት ከ500 በላይ አባወራዎች አሁንም የከፋ ህይወትን ነው የሚመሩት ያሉን አንደኛው ተፈናቃይ፤ በተለያዩ ጊዜያት የምናቀርባቸው ጥሪዎች ምላሽ አላገኘም ብለዋል፡፡ ከ5 ቤተሰቦቻቸው ጋር ተወልደው ካደጉበት ሴዳን ወረዳ ተፈናቅለው ለአንድ ዓመት ከ8 ወር ገደማ ይህን የተፈናቃይነት ህይወት እየመሩ መሆኑን የገለጹት እኚህ ተፈናቃይ፤ እርዳታ ከደረሳቸው አንድ ኣመት ማለፉንና እንጨት ሰብረው ሴቶችም ሰው ቤት ውስጥ የተገኘውን እየሰሩ ህይወት እንደሚገፉ አስረድተዋል፡፡  የተፈናቃዮች አቤቱታ በአማራ ክልል
“መንግስት በሚዲያ ከዚያ የሚለቃቸው መረጃዎች እና እኛ ጋር ያለው የሚመሳሰል ነገር የለም፡፡ በወቅቱ ሽፍቶች በተባሉ ታጣቂዎች ጥቃት ነበር የተፈናቀልነው፡፡ እስካሁን በዚያ አከባቢ የፀጥታ ሁኔታ አስተማማን አይደለም፡፡ አሁን ያለንበትም አስተማማን ሰላም ያለበት ባለመሆኑ ተንቀሳቅሰን መስራት አዳጋች ነው፡፡ በቂ ድጋፍም የለም ማህበረሰቡ ችግር ላይ ወድቋል፡፡”
ከአሶሳ ዞን ብልድግሉ ወረዳ በ2011 ዓ.ም. በተከሰተው የብሔር ግጭት ተፈናቅለው ላለፉት አራት ዓመታት ገደማ በዚሁ መንዲና አከባቢው በተፈናቃይነት ፈተናን እየተጋፈጥን ነው የሚሉት ሌላው ተፈናቃይ በበኩላቸው፤ ተስፋ አስቆራጭ ካሉት ፈተና እንዲወጡ ይጠይቃሉ፡፡ ከዚህ ወረዳ ከተለያዩ ቀበሌያት የተፈናቀሉት ከ2 ሺህ በላይ እንደሚገመቱም በማስረዳት አሁንም ድረስ አስተማማኝ ፀጥታ አይስተዋልበትም ወዳሉት ቀዬያቸው ስለመመለስ እንደሚናፍቁም አመልክተዋል፡፡ “ችግሩ ይህ ነው የሚባልና ቀላል አይደለም፡፡ በዴሳ እና ዳላቲ የሚባሉ የተፈናቀልንባቸው ቀበሌያት አሁንም በቅርቡ ከ20 ቀናት በፊት እንኳ ለጥቃት የተዳረጉ ነዋሪዎች መኖራቸውን ተከትሎ ወደአከባቢው የመመለሱን አማራጭ በጥርጣሬ እንድንመለከት አድርጎናል፡፡ እዚህ የኑሮ ሁኔታ ከብዶናል፡፡ እርዳታ ሚደርሰን እጅግ አልፎ አልፎና በቂ ባልሆነ መንገድ ነው፡፡ ወደ ቀዬያችን መመለስ እንፈልጋለን፡፡ እዚህ ያለንበትም ፀጥታው አስተማማኝ ባለመሆኑ ወደ ጫካ ወጥቶ እንጨት ሰብሮ መመለስ እንኳ አስፈሪ ነው፡፡ እናም ተፋናቃዮች ችግር ውስጥ ነው ያሉት፡፡”
በሁለቱ ክልሎች መንግስታት በኩል የየአከባቢዎቹን ሰላም በማስፈን ወደ ቀያያችሁ እንመልሳችኋለን የሚል ቃል በተደጋጋሚ ብገባልንም በተግባር ግን ሙሉ በሙሉ ሲፈጸም አናይም ሲሉም ተፈናቃዩ ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ አሁን የተሻለ አንጻራዊ ሰላም መኖሩን ያስረዱት የክልሉ ባለስልጣን ግን ወደ ሌላ ክልል ከተፈናቀሉት ይልቅ አሁን ይበልጥ የሚያሳስበን ከኦሮሚያ ክልል ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅለው ያልተመለሱት ዜጎች ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡ የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ቢሮ ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ታሲሳ ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት፤ “ክልሉ ውስጥ አሁን የተሻለ ሰላም ስለተረጋገጠ ከጫፍ እስካ ጫፍ ሰው መመላለስ ይችላል፡፡ መንግስት ጥርጣሬ አለኝ እዚህ ውስጥ አትግቡ ብሎ የያዛቸውም ቦታዎች እጅግ ውስን ነው፡፡ ይልቅ ከመናሲሙ፣ ከመንዲ፣ ከባቦ እና ጉሊሶ ከተባሉ የኦሮሚያ ክልል አወሳን ወረዳዎች ወደ አሶሳ የተፈናቀሉ ነው እንጂ ከክልላችን ተፈናቅለው እስካሁንም መንዲና አከባቢው ላይ ስላሉ ተፈናቃዮች መረጃ የለንም፡፡ በርካቶችን መልሰን እያቋቋምን ነው፡፡ ከሴዳልም የተፈናቀሉት በብዛት በዚሁ ክልል ባንባሲ አከባቢ ነው ያሉት፡፡ ከነሃሴ ጀምሮ በተሰራ ስራ ከተወሰኑት ውጪ ሰውን መልሰን እያቋቋምን ነው” ብለዋል፡፡ የተፈናቃዮች ሮሮ በካማሺ ዞን
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ከአማጺያን ጋር የተደረሰው የሰላም ስምምነት በክልሉ ውስጥ መረጋጋትን ለማስፈን አይነተኛ ሚና ነበረው ያሉት ባለስልጣኑ፤ ከኦሮሚያ ተፈናቅለው ክልላቸው ውስጥ የሚገኙትን ተፈናቃዮችም ጭምር ወደ ቀዬያቸው የመመለሱ ስራ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡ ለአብነትም ከመነሲቡ ከተፈናቀሉ 22 ሺህ ዜጎች አራት ሺህ ገደማውን በመመለስ ከቆንዳላ፣ ባቦ እና ጉሊሶ ከሚባሉ የምእራብ ኦሮሚያ አከባቢዎች የተፈናቀሉ 8 ሺህ ዜጎችንም በቀጣይ ሁለት ወራት ለመመለስ ወጥነን እየሰራን ነው ብለዋልም፡፡
ዶቼ ቬለ ስለተፈናቃዮቹ አስተያየት እንዲሰጡ ጥያቄ ያቀረበላቸው የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽብ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ በክልሉ የሰላም ማስፈን ስራ ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑ አንጻራዊ ሰላም በክልሉ እንዲመጣ ማስቻሉን ገልጸው፤ በቀጣይ ግጭት ያፈናቀላቸው ነዋሪዎችን ወደ ቀደመ ህይወታቸው የመመለስ ስራ ቀዳሚ ትኩረት ያገኛል ብለዋል፡፡ ሃላፊው አክለውም ተፈናቃዮችን መልሶ የማቋቋም ስራ መጀመሩንና መንግስት ባለው አቅም እየረዳቸውም እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ 
ምዕራብ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት አራት ዓመታት በብሔር ግጭትና በተለያየ መልኩ በተስተዋለው አለመረጋጋት በርካቶች ህይወታቸውን ሲያጡ በሚሊየን የሚቆጠሩ ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት ከሃብት ቀዬያቸው መፈናቀላቸው ይታመናል፡፡ 

ከቤንሻንጉል ጉሙዝ በ2011 ዓ.ም. ተፈናቅለው መንዲ ምዕራብ ወለጋ የተጠለሉ ሰዎች ምስል DW/N. Dessalegn


ስዩም ጌቱ


ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW