የተፎካካሪ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ በአማራ ክልል
ማክሰኞ፣ ግንቦት 18 2018
የሰባተኛው ሀገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ አንድ ሳምንት ብቻ በቀረበት በዚህ ወቅት፣ በአማራ ክልል በተፋዘዘ ሁኔታ ላይ የነበረው የተፎካካሪ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ ከባለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ እንደገና መነቃቃት ማሳየቱ ተገለፀ ፣ ፓርቲዎቹ በክልሉ ያለዉ የሰላም ሁኔታና የነዳጅ እጥረት ለምርጫ ቅስቀሳዉ መዝግየት ምክንያት ነበር ብለዋል። ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው የደሴ፣ የኮምቦልቻ እና የሰንበቴ ከተማ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲከኞች ምልክቶቻቸውን እና አማራጭ የፖሊሲ ሐሳቦቻቸውን ዕያስተዋወቁ ይገኛሉ ።
የሰባተኛው ሀገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ አንድ ሳምንት ብቻ በቀረበት በዚህ ወቅት በአማራ ክልል በተፋዘዘ ሁኔታ ላይ የነበረው የተፎካካሪ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ ከባለፈው ሳምንት መጨረሻ ቀናት ጀምሮ ተጠናክሮ ቀጥሏል። ፓርቲዎቹምልክቶቻቸውን እና አማራጭ የፖሊሲ ሀሳቦቻቸውን እያስተዋወቁ ይገኛሉ የሚሉት የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪው አቶ አሊ ሰይድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአደባባይ በመውጣት ጭምር የተጠናከረ ቅስቀሳ ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ። «አሁን ትላንትናም ከትላንት ወዲያም እያየሁ ነው እዚህ በከተማው ጎዳናዎች ላይ የጎዳና ቅስቀሳ የባነር እና የታፔላ መለጠፍ ስራ እየሰሩ እያየሁ ነው እና ጥሩ እንቅስቃሴ ነው ይሄ አሁን አንደኛ የፖለቲካ ምህዳሩን ራሱ ያሟሙቀዋል።»
በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ሰንበቴ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ኡመር አብደላም በአካባቢው ያለው የሰላም ሁኔታ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን በነፃነት ለመግለጽ የሚያስቸግራቸው ባይሆንም አሁን ላይ ግን ዘግይተውም በአደባባይ በመውጣት ጭምር በንቃት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አስረድተዋል። «ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጅምሩ ላይ ብዙም ሲሳተፉ አይታዩም ነበር አሁን በመጨረሻው አካባቢ ግን እየተንቀሳቀሉ ነው ሀሳቦቻቸውን ፖሊሲዎቻቸውን እያንጸባረቁ እያስተገቡ ነው ያሉት ጅምሩ መልካም ይመስላል የፀጥታ ሁኔታ ከ ከሌሎች አካባቢዎች በተሻለ ሁኔታ የተረጋጋ ነው ይህንን ያህልም ለተፎካካሪ ፓርቲዎች አስቸጋሪ ሁኔታም አልነበረም።»
በሰባተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫበአማራ ክልል የሚሳተፉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለቅስቀሳ መዘግየታቸውን አምነው ባሉት ጥቂት ቀናት ግን ለህዝቡ አማራጭ ፓርቲ መኖሩን ያሳየንበትን የምርጫ ቅስቀሳ እያካሄድን እንገኛለን ሲሉ ሻምበል ደምሌ ተረፈ የኢዜማ የደሴ ከተማ የክልል ምክር ቤት ተወካይ ይናገራሉ። «ቅስቀሳችን በጣም የተሳካና አርኪ የሆነ ነበረ ህዝቡ አማራጭ ፓርቲ እንዳለ ተረድቶ በደስታ ነው ምልክት ያሳየንና ሲገልጽልን የነበረው ይህም የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ቅስቀሳችን በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል ሕዝቡ እንዲያሰላስል ያለችንን አራት ቀን በደንብ ጥሞና ወስዶ እንዲያስብና ትክክለኛውን ፓርቲ እንዲመርጥ እያደረግንበት የመጨረሻዋ ሰአት ናት።»
የወሎ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ደሴ ከተማ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ዳውድ ማህመድ በበኩላቸው በአካባቢው ያለው የነዳጅ እጥረት ትልቅ ፈተና ቢሆንም የተጠናከረ የምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ መሆናቸውን ግን ይገልጻሉ። «ቅስቀሳ እያደረግን ነው በደንብ የነዳጅ እጥረት አለ አሁን እኛ ግን የነዳጅ እና እሮብን ተቀጥቅጦ አድብለናል ከትላንት በስትያ መለጠፍ ነው የዋልነው አንዳንድ የቅስቀሳዎችን እያደረግን ነው ደግሞ ማክሰኞ እና ረቡዕ ደግሞ ቅስቀሳ እናደርጋለን ብለናል።»
በሰሜን ጎጃምና በባህር ዳር ዙሪያ ያለው ሁኔታ በአደባባይ ወጥቶ የምርጫ ምልክት እና አማራጭ ሀሳብን ለህዝብ ለማቅረብ አመች አለመሆኑን የኢዜማ የአዴት ምርጫ ክልል ተወካይ የሆኑት አቶ ይበልጣል አድማሴ ይናገራሉ። «ይህ ምርጫ በችግር ላይ ሆነን የምናካሂደው ምርጫ ነው ሰላማዊ ትግል ብዙ አያዋጣም የሚሉ ዜጎች የራሳቸውን ፍላጎት የሚያራምዱበት ሌሎች ደግሞ ፓርቲ መስርተው መንግስት የሚቀየረው ሀገር ወደ የተሻለ አማራጭ የምታገኘው በሰላማዊ ትግል ነው ብለው የሚያምኑ ስለዚህ የተለየ ጎራ ተሰልፈን ሀገር ልናሻግር እየሰራንበት ያለነው ነው ስለዚህ የምርጫ ቅስቀሳዎች በእኛ ግምገማ ጥሩ እየሄዱ ነው የሚል ነው ያለን አሁን እኛ እያስቀሰቀስን ነው ምክንያቱም ቅድም እንዳልኩት ይሄ የተለያየ ጎራ የተሰለፈ ስላለ የመንገድ ላይ ቅስቀሳዎችን ብዙ ማድረግ አልቻልንም በተለያየ ምክንያት።»
በባህር ዳር ከተማም የነዳጅ እጥረት፣ በጀት እና ወቅታዊ ሁኔታ የምርጫ ቅስቀሳውን በተፈለገው መንገድ ማስኬድ እንዳልቻላቸው አቶ ኃይለማርያም ብርሃኑ የባህር ዳር የኢዜማ ተወካይ ይናገራሉ። «እንደ ፓርቲ ያደረግነው እንቅስቃሴ የምርጫ ቅስቀሳዎች በሚሰጠን የ ሚዲያ ታይሞችን ለመጠቀም ሞክረናል ከዚያ ባሻገር አንደኛ ይሄ ነው የምንለው ከወቅቱ አንፃር ሲታይ ብዙም ቅስቀሳ ለማድረግ አያስደፍርም ሰዎቹ አንዳንድ የሆነ ምክንያት መፍጠር አያሰራም ነገር ግን ከዚያ ጋር አያይዞ ብዙም እንደበፊቱ የምንቀሰቅስበት ምክንያት የለም።»
ኢሳያስ ገላው
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ
#ምርጫ2018 #EthiopiaElection2026