1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአገር ጎብኒዎች ቪዛ ማጠር በቱሪዝም ላይ ያሳደረው ተጽእኖ

ቅዳሜ፣ የካቲት 16 2016

ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ ቱሪስቶች ከዚህ በፊት ይሰጥ የነበረው የረዥም ጊዜ ቪዛ በአንድ ወር እንዲገደብ መደረጉ በቱሪዝም ኢንዳስትሪው ላይ በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እንደሆነባቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የአኽሱም ሐወልት
የአኽሱም ሐወልትምስል Million Hailslassie/DW

የአገር ጎብኒዎች ቪዛ ማጠር በቱሪዝም ላይ ያሳደረው ተጽእኖ

This browser does not support the audio element.

መንግስት ወደሃገሪቱ ለሚገቡ ቱሪስቶች ይሰጥ የነበረው የረዥም ጊዜ ቪዛ በአንድ ወር መገደቡ በቱሪስቶች ፍስት አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረ እንደሆነ የቱሪዝምና አስጎብኚ ባለሙያዎች አማረሩ። ይህ አገሪቱ ከቱሪዝም ልታገኝ የሚገባውን ገቢም እንደሚቀንስ ባለሙያዎቹ አክለዋል። 
የኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዳስትሪ በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች እየተፈተነ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል፣ በኦሮሚያና  እና በተለያዩ አካባቢዎች በቀጠሉ ጦርነቶችና ግጭቶች ሃገራት ዜጎቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ የጉዞ ማስጠንቀቂያ በመስጠታቸው የቱሪዝም ኢንዳስትሪውን ከፈተኑት ዋነኛ ጉዳይ መሆኑን የመስኩ ባለሙያዎች ለDW ተናግረዋል።
አሁን ደግሞ ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ ቱሪስቶች ከዚህ በፊት ይሰጥ የነበረው የረዥም ጊዜ ቪዛ በአንድ ወር እንዲገደብ መደረጉ በቱሪዝም ኢንዳስትሪው ላይ በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍእንደሆነባቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ።
አቶ አሸናፊ ካሳ የራሳቸው የአስጎብኚ ድርጅት ያላቸውና የሆቴልና ቱሪዝም አማካሪ ናቸው። በቱሪዝም ኢንዳስትሪውም ለ18 ዓመታት ሰርተዋል። በዚህ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።
`` የቱሪስት ፍሰቱን ይገድበዋል። የሰዎቹን ኢንተረስት ያሳንሰዋል። ቱሪስቶች እዚህ ከመጡ በኅላ የመቆየት ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል። ከአንድ ወር በላይም ለማራዘም ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል። በዚህ መሃል ቪዛን እያሰቡ የሚንቀሳቀሱ ከሆነ ለነሱ ጥሩ አደለም።``
የኤክስክዩቲቭ ኢትዮጵያ የጉዞ ወኪል ባለቤትና በቱሪዝም ዘርፍ ለ12 ዓመታት የተሰማሩ በመስኩ የተሰማሩ ባለሙያ አቶ ሙሉጌታ አባቡም  የአቶ አሸናፊን ሐሳብ ይጋራሉ።
``ለአንድ ወር ብቻ መወሰኑ ጉዳቱን ልንገርህ። ለምሳሌአንድ ቱሪስት ታሪካዊ ቦታዎችን ለማየት   ከአዲስ አበባ አማራና ትግራይ እስከ ዓፋር ዳሉል ታሪካዊ ቦታዎችን ለማስጎብኘት እስከ 45 ወይም 60 ቀናት ፕሮግራም ልትይዝ ትችላለህ። አሁን ግን ያን ማድረግ አይችሉም ማለት ነው``

የጅማ ሰቃ ፏፏቴምስል Seyoum Getu/DW


ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በሚደረጉ ውይይቶች በቱሪዝም ዘርፍ የሚያጋጥሙ ችግሮች ውይይቶች እንደሚደረጉ የገለጹልን አቶ አሸናፊ አጥጋቢ ባይሆኑም አንዳንድ የቪዛ አሰጣጥ መሻሻሎች እንዳሉ አጫውተውናል።
ቱሪዝም ሰላም ይፈልጋል ያሉት አቶ አሸናፊ በአገሪቱ የሚታየው የሰላም መደፍረስ፤ በቪዛ አሰጣጥ የሚታዩ ችግሮችና ሌሎች ተደማሪ ጉዳዮች  ተደማምረው አሁናዊ የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንደበፊቱ አደለም ብለዋል።
ለቱሪስቶች ከዚህ ቀደም ይሰጥ የነበረው የረዥም ጊዜ ቪዛ ለምን በአንድ ወር ታጠረ ብለን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጠይቀን ነበረ። ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የፌደራል የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎትን እንደሆነ ተነግሮናል። በዚሁም መሰረት ከመስሪያቤቱ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት ለጊዜው አልሰመረልንም።

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ኂሩት መለሰ


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW