1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቱሪዝም መነቃቃት በትግራይ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 25 2016

በትግራይ ጦርነቱን ተከትሎ የተለያዩ ሀገራት ዜጎቻቸው የግጭት ማእከል ወደነበረችው ትግራይ እና ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንዳይሄዱ ዕቀባ ያደረጉ ሲሆን፥ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር ሀገራት የጣሉት የጉዞ ገደብ እንዲያነሱ ጥረት እያደረገ መሆኑ ተነግሯል።

Äthiopien Addis Abeba 2024 | Historische und touristische Attraktion | Axum Obelisk & Handwerkskunst
ምስል Million Hailesilasse/DW

የባሕል መድረክ፤ የቱሪዝም መነቃቃት በትግራይ

This browser does not support the audio element.

በትግራይ በጦርነቱ እና ኮቪድ ምክንያት ለዓመታት ተስተጓጉሎ የነበረው የቱሪስቶች የተለመደ ፍሰት ዳግም ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ይገለፃል። የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር  በጦርነቱ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ዳግም ክፍት መደረጉ አስታውቋል። ለዚህ እንዲረዳም የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የሆቴል የተለያዩ አቅርቦቶች እንዲሁም የፀጥታ ሁኔታ አመቺነት ተገምግሞ ዝግጁ መደረጉን ገልጿል።

ከግብርና እና አምራች ኢንዳስትሪ ቀጥሎ የክልሉ ኢኮኖሚ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ የነበረው የትግራይ የቱሪዝም ኢንዳስትሪ እንቅስቃሴ፥ አስቀድሞ በኮረና ቫይረስ ወረርሺኝ፥ ቀጥሎም ደግሞ በጦርነቱ ምክንያት ሙሉበሙሉ ተብሎ በሚገለፅ ደረጃ ተስተጓጉሎ የቆየው ከ2012 ዓመተምህረት በኃላ ነበር። 

ቱሪዝምን ለማነቃቃት

የጥንታዊ ስልጣኔ ቅሪቶች፣ በርካታ ሃይማኖታዊ ስፍራዎች፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሮአዊ መስህቦች በስፋት ባሉባት ትግራይ፥ የቱሪዝም እንቅስቃሴው መቆሙ ተከትሎ በቀጥታ በዘርፉ ተሰማርተው ከሚሰሩ አካላት በተጨማሪ በአጠቃላይ ኢኮኖሚውም ከፍተኛ በቀዛቀዝ ፈጥሮ ቆይቷል። የጥንታዊ ስልጣኔ ማእከል የነበረችው አክሱም ከተማ ዋነኛ የገቢ ምንጭዋ፣ የህዝቡ የኢኮኖሚ መሰረት ከቱሪስቶች ጉብኝት፣ ከምትሰጠው ባህላዊ መስተንግዶ እና አገልግሎት፣ በባለሙያዎች ከሚመረቱ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ቁሶች የሚገኝ ገቢ ነው። ከ2012 ዓመተምህረት በኃላ ባለው ግን ይህ ሁሉ መጥፋቱን የከተማዋ ነዋሪዎች እና የቱሪዝሙ ዘርፍ ባለስልጣናት ይናገራሉ። በመቐለ እንዲሁ ለቱሪስቶች አገልግሎት ታሳቢ ተደርገው የተሰሩ ሆቴሎች ጨምሮ ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ረዥም ግዜ ከስራ ውጭ ሆነው ቆይተዋል። የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የትግራይ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ዳግም ለማስቀጠል የሚያስችል ዝግጅቶች ሲደረጉ እንደቆዩ የሚገልፀው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር፥ አሁን ላይ የጉብኝት ስፍራዎች ምቹነት፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽነት እና ያለው አንፃራዊ ሰላም እንደ ዕድል በመጠቀም ክልሉ ዳግም ለሀገር ውስጥና ውጭ ቱሪስቶች በይፋ ክፍት መደረጉ ይገልፃል። የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ስለሺ ግርማ ፥ በኢትዮጵያ የሚሰሩ አስጎብኚ ድርጅቶች የትግራይ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ወደ ዝርዝራቸው እንዲያስገቡ ጥሪ ቀርቧል።

የአኽሱም ሃውልቶችምስል Million Hailslassie/DW

በትግራይ ለቱሪስቶች አገልግሎት በመስጠት ስራ የተሰማሩ ባለሙያዎች እንደሚሉት አንፃራዊ ሰላም ከተፈጠረ በኋላም ቢሆን እስካሁን የሚጠበቀው አልያም የተለመደው የቱሪስት ፍሰት ወደ ትግራይ እንደሌለ ይጠቁማሉ። ይሁንና ካለፈው ግዜ ጋር በማነፃፀር የተወሰኑ ለውጦች ማየታቸው ተስፋ እንደጫረባቸው በአኽሱም ሐወልቶች አካባቢ ፎቶ በማንሳት ስራ የተሰማራ ዘርኣብሩክ ሃይለ ገልጾልናል። 

ሌላዋ ባህላዊ የቡና ስነስርዓት በማስተዋወቅ ስራ የተሰማራች ወጣት  አሰፉ ፍስሃ በበኩልዋ፥ የተፈጠረው ሰላም ምክንያት  የተወሰነ እንቅስቃሴ መኖሩ ተስፋ ሰጥቷታል።
የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር እና የትግራይ ቱሪዝምቢሮ፥ በኢትዮጵያ የሚሰሩ አስጎብኚ ድርጅቶች የትግራይ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ወደ ዝርዝራቸው እንዲያስገቡ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ስለሺ ግርማ እንደሚሉት በትግራይ የቱሪዝም እንቅስቃሴ በይፋ ዳግም ለማስጀመር የመዳረሻዎች እና የመሰረተ ልማቶች ዳሰሳ ሲደረግ መቆየቱን ጠቅሰው አሁን ባለው ሁኔታ በትግራይ ለቱሪስቶች ምቹ ሁኔታ መኖሩ ይናገራሉ። 

የአኽሱም ሃውልትምስል Million Haileselassie/DW

በጥንታዊ ቅርሶች ላይ የተደቀነው አደጋ

በጦርነቱ ወቅት በቅርሶች ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱ፣ ዝርፍያ መፈፀሙ፣ ታዋቂው ነጋሽ መስጅድ፤ ተለያዩ ጥንታዊ አብያተክርስቲያናት እና ገዳማት የከባድ መሳርያ ዒላማ መሆናቸው የሚገልፀው የትግራይ ቱሪዝም ቢሮ፥ ይሁንና ባለው ሐብት እና ዝግጁነት ክልሉ ወደ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ እንዲመለስ መደረጉ ገልጿል። ይሁንና በትግራይ የሚገኙ ጥንታዊ ቅርሶች በጦርነቱ ምክንያት እንዲሁም ሌሎች ተፈጥሮአዊ እና ሰው ሰራሽ ሁነቶች አደጋ ላይ መሆናቸውም ባለሙያዎች ይገለፃሉ። ለአብነት እንኳን የአኽሱም ሐወልቶች ይደረግላቸዋል የተባለ ጥገና ዘግይቶ ከፍተኛ አደጋ ላይ መሆናቸው በአኽሱም ቱሪዝም ቢሮ የቅርስ ጥበቃ ባለሙያ አቶ አላይ ወልደስላሴ ይናገራሉ። 

ሌላው ለትግራይ ቱሪዝሙ ዘርፍ ፈተና ተደርጎ የሚጠቀሰው ደግሞ ግጭቱ ተከትሎ የተለያዩ ሀገራት መንግስት ወደሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ዜጎቻቸው እንዳይጓዙ ያኖሩት ዕቀባ ነው። ጦርነቱ ተከትሎ የተለያዩ ሀገራት ዜጎቻቸው የግጭት ማእከል ወደነበረችው ትግራይ እና ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንዳይሄዱ ዕቀባ ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን፥ ይህ ዕቀባ አሁንም አለመነሳቱ ይገለፃል። በዚህ ጉዳይ ዙርያ ማብራርያ የሰጡን የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ስለሺ ግርማ፥ ሀገራት የጣሉት የጉዞ ገደብ እንዲያነሱ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተናግረዋል።

በትግራዩ ጦርነት ወቅት በትግራይ ቅርሶች "በገንዘብ የማይለካ" ያለው ውድመት መድረሱ የትግራይ ቱሪዝም ቢሮ ይገልፃል። ከቅርብ ግዜ ወዲህ የተወሰኑ የውጭ ቱሪስቶች ጨምሮ በአብዛኛው የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ለሃይማኖት ስርዓቶች ጨምሮ ለተለያዩ ሁነቶች ትግራይ መጎብኘት ጀምረዋል። ይህም በበርካቶች ዘንድ ተስፋ የፈጠረ ሆንዋል።


ሚልዮን ሃይለስላሴ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW