1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቲዊተር እና የፌስቡክ የይዘት ክትትል ሠራተኞች ቅነሳ እና መዘዙ

ሐሙስ፣ ኅዳር 15 2015

ቱጃሩ ኢሎን ማስክ ቲዊተርን በ44 ቢሊዮን ዶላር ከገዙት ወዲህ የይዘት ክትትል የሚያደርጉ በርካታ ሰራተኞችን ከስራ አሰናበተዋል። በኢትዮጵያ ግጭትን በማባባስ የሚወቀሰው ፌስቡክም ተመሳሳይ ዕቅድ አለው።ርምጃው በርካታ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ባላት ኢትዮጵያ ግጭት ቀስቃሽ እና የጥላቻ ንግግር እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል።

Hass im Netz Symbolbild
ምስል Sebastian Gollnow/dpa/picture alliance

የቲዊተር እና የፌስቡክ ዕርምጃ የጥላቻ ንግግር ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል።

This browser does not support the audio element.

የዓለማችን  እጅግ ባለፀጋ ሰው ኢሎን ማስክ ቲዩተርን በ44 ቢሊዮን ዶላር ከገዙት ወዲህ እጅግ መነጋገሪያ ሆነዋል።ሰውየው መነጋገሪያ የሆኑት በመድረኩ ላይ የጥላቻ እና አድሎአዊ ይዘትን የሚከታተሉ በርካታ ሰራተኞችን ከወዲሁ ከስራ በማሰናበታቸው ነው።ሌላው  የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ፌስቡክም ሰራተኞችን የመቀነስ ዕቅድ እንዳለው በቅርቡ ገልጿል።የኩባንያዎቹ እርምጃ  በሰዎች የሚከናወነውን  የይዘት ቁጥጥር  በማሽን ስለሚተካ በዲጅታል መድረኩ የጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃ  ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል። የዛሬውን የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዝግጅት ጉዳዩን በግጭት እና አለመረጋጋት ውስጥ ከምትኘው ኢትዮጵያ አንፃር ይቃኛል። 
እስካለፈው ሳምንት ቅዳሜ ድረስ ሜሊሳ ኢንግል በትዊተር የይዘት ክትትል ማድረግ ስራዋ ነበር።
የመረጃ ሳይንቲስቷ በኩባንያው ከብራዚል እስከ አሜሪካ በሚደረጉ ምርጫዎች የተሳሳቱ የፖለቲካ መረጃዎችን ላይ ክትትል ታደርጋለች። ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን ወዲያውኑ በመለየትም ስልተ ቀመሮችን/algorithms/ ታስናዳለች። 
በጎርጎሪያኑ ህዳር 12 ቀን 2022 ዓ/ም  ግን የእጅ ስልኳ ላይ አንድ መልዕክት ደረሳት።ይህ መልዕክት ከአሁን በኋላ ወደ ስራ ኢሜይሎቿ እንዳትደርስ የሚገልፅ ነበር። ይህን ባየች ጊዜ የ48 ዓመቷ ሴት ከስራዋ መባረሯን አወቀች። መሊሳ ብቻዋን አልነበረችም።
ቱጃሩ ኢሎን ማስክ ቲዊተርን በ44 ቢሊዮን ዶላር ከገዙት ወዲህ፤ በዚህ ወር መጀመሪያ  ከስራ ከተባረሩ  3,700 የሚጠጉ ሰራተኞች በተጨማሪ መሊሳ ኤንግልን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች የኮንትራት ሰራተኞች ባለፈው ሳምንት መጨረሻ  ውላቸው እንዲቋረጥ አድርጓል።

የዓለማችን ትልቁ ቱጃር ኤለን ማስክ ምስል Mike Blake/REUTERS

ከተቀነሱ ሰራተኞች መካከልም በተግባቦት፣ በይዘት መጠበቂያ፣ በሰብዓዊ መብቶች እና በማሽን  የስነ-ምግባር መማሪያ ላይ ኃላፊነት የተጣለባቸው ሰዎች ይገኙበታል።
ከፍተኛ የዳታ ሳይንቲስቷ ለDW እንደተናገረችው ከዚህ አንፃር ትዊተር ጤናማ መድረክ ሆኖ ስለመቀጠሉ ጥርጣሬ ገብቷታል።በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን ያካፈለን የመብቶች እና የዲሞክራሲ እድገት ማዕከል በእንግሊዥኛው ምህፃሩ CARD በመባል የሚጠራው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ዳይሬክተር የሆነው ፀሀፊ እና ጦማሪ በፈቃዱ በሀይሉም ስጋቱን ይጋራል።ከዚህ ቀደምም ቲውተር በኢትዮጵያ ጉዳዮች በሚፃፉ ይዘቶች ላይ በአግባቡ ያለመቆጣጠር ችግር  እንደነበረበትም ገልጿል።
በአሁኑ ወቅት የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የሰው ኃይላቸውን በመቀነስ ሰው ሰራሽ አስተዎሎትን በመጠቀም ማሽን የሰው ልጆችን ሥራ  ተክቶ እንዲሰራ ማድረግ እየተለመደ መጥቷል።መረጃዎች እንደሚያሳዩት እንደ ትዊተር እና ፌስቡክ ያሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ኩባንያዎችም በይዘት መቆጣጠሪያ  ስርዓቶቻቸው በማሽን ትብብር ላይ የተመሰረቱ ውስብስብ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ።
ማለትም ተጠቃሚዎች አዲስ ይዘት በሚለጥፉ ጊዜ ኩባንያው በራሱ ሶፍትዌር ይቃኛል።ማሽኑ ልጥፉ ሕገወጥ ወይም ጎጂ ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁሙ ምልክቶችን ካገኘ ለግምገማ ወደ ይዘት ተቆጣጣሪ  ባለሙያዎች ይልካል። የእነሱ ሥራ የተለጠፈው ይዘት  በመድረኩ የተቀመጡትን ደንቦች እንዲሁም የአካባቢ ህጎችን የሚያከብር መሆኑን ማየት ነው።ያ ካልሆነ ደግሞ ይዘቱን ከመድረኩ  ለማውረድ መወሰን ነው።ይህ ደግሞ ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ ውሳኔው ዳተኝነት ሲታይበት ቆይቷል።

ምስል Jakub Porzycki/NurPhoto/picture alliance

ይህን መሰሉ  ችግር ሲታይበት የቆየው ቲውተር ታዲያ፤ የጥላቻ እና አድሎአዊ ይዘትን የሚከታተሉ በርካታ ሰራተኞችን ከሰሞኑ በማሰናበቱ የይዘት ቁጥጥሩ  በማሽን  የሚተካ  ከሆነ፤  የጥላቻ ንግግር እና የተሳሳቱ መረጃዎችን ሊያስፋፉ ይችላል የሚል  ስጋት ደቅኗል። 
በአሜሪካ ኒውጀርሲ ግዛት በሞንትክሌር ስቴት ዩኒቨርሲቲ የተደረገ አንድ ጥናት ይህንን ያጠናክራል። ጥናቱ እንዳመለከተው ማስክ ቲዊተርን በባለቤትነት ከያዙት ወዲህ  የጥላቻ ንግግር ጨምሯል።
ይህ ሁኔታ ደግሞ ቀድሞውንም በቲውተር የረባ ቁጥጥር በማይደረግበት የኢትዮጵያ ጉዳይ ግጭት የሚያባብሱ መረጃዎችን የበለጠ ሊያስፋፋ ይችላል።
ምክንያቱም የማሽኑ ውሳኔ በትክክለኛው እውነታ ላይ ከመመስረት ይልቅ በተጫነለት የዳታ ስሌት ላይ የሚያተኩር ነው,።በዚህም ባህል፣ የቋንቋ አጠቃቀም እንዲሁም አቻ ትርጉም ግምት ውስጥ ላይገባ ይችላል።ከዚህ አንፃር ሰው ሰራሽ አስተዎሎት  ተጋኗል ይላል በፈቃዱ።
ከቲዊተር በተጨማሪ በየ ቀኑ ከሁለት ቢሊዮን በላይ ሰዎች ይጎበኙታል ተብሎ የሚታመነው ፌስቡክም 13 በመቶ ሰራተኞቹን ለመቀነስ መወሰኑን ከፌስቡክ በተጨማሪ ኢንስታግራምን እና ዋትሰአፕን  የሚያስተዳደረው ሜታ በቅርቡ አስታውቋል።  የፌስቡክ መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማርክ ዙከርበርግ በቅርቡ ይፋ እንዳደረገው ይህ ውሳኔ  ወደ 11 ሺህ የሚጠጉ ሠራተኞችን ነክቷል።

የፌስቡክ መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማርክ ዙከርበርግምስል Nick Wass/AP Photo/picture alliance

ፌስቡክ ፤በኢትዮጵያ ይዘቶች ላይ ከቲውተር በተሻለ መጠነኛ ቁጥጥር የሚያደርግ ቢሆንም፤ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ግጭትን በማባባስ በአሜሪካ ምክር ቤት ሳይቀር ሲተች ቆይቷል።የአሁኑ እርምጃው ደግሞ  በርካታ የፌስቡክ ተጠቃሚ ባላት ኢትዮጵያ ችግሩን የበለጠ ሊያባብሰው እንደሚችል በፈቃዱ ይገልፃል።
ቴክኖሎጅ የሰው ልጆችን የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል  የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ ነው።ያምሆኖ በአግባቡ እና በሀላፊነት ስሜት ጥቅም ላይ ካልዋለ ጉዳቶችም አሉት።ቲውተር እና ፌስቡክን የመሳሰሉ ዘመኑ የወለዳቸው ዲጅታል የመገናኛ ዘዴዎችም ሰዎችን በመረጃ በቀላሉ በማቀራረብ ረገድ የሚሰጡት ጥቅም ከፍተኛ ቢሆንም፤ከጥቅሙ ጋር ህጋዊነት እና ሀላፊነት አብረው ካልሄዱ ግጭትን ለሚፈጥሩ የጥላቻ ንግግሮች እንዲሁም ለሀሰተኛ መረጃዎች በር ይከፍታል።ስለሆነም በፈቃዱ እንደሚለው ችግሩን ለመቀነስ እነዚህ ኩባንያዎች ማኅበራዊ ሀላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ግፊት ማድረግ ያስፈልጋል።

ሙሉ ዘገጀቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
 ነጋሽ መሀመድ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW