የታህሳስ 17 ቀን 2015 ዓ/ም የስፖርት ዝግጅት
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 17 2015በቻን የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የመጨረሻ ዝግጅቱን ለመጀመር የተጫዋች ምርጫ ማጠናቀቁን የእግር ካስ ፌዴሬሽ አስታውቋል። የኳታር ዓለም ዋንጫ ከአስገራሚ ትዝታዎቹ ጋር ከተጠናቀቀ አንድ ሳምንት አስቆጠሯል፤ ሻምፒዮናዋን አርጀንቲናን ጨምሮ እስከ አራተኛ ያጠናቀቁ ሃገራት ጀግኖቻቸውን በክብር ተቀብለዋል።
ዓለማቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ የሀገራት አዲስ የደረጃ ሰንጠዥ ይፋ አድርጓል፤ ብራዚል ደረጃውን ትመራለች ። ከዓለም ዋንጫው መለስ የታላላቅ ሊጎች ውድድሮች ተጀምረዋል። የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ የቦክሲንግ ዴይ ጫወታዎችን አመሻሹን ቀን 9 ሰአት ተኩል በተጀመረ ጫወታ ተጀምሯል።
ከፊታችን ጥር 5 ቀን 2015 ዓ/ም ጀምሮ በአልጄሪያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው በሀገር ውስጥ ብቻ በሚጫወቱ ተጫዋቾች የሚከናወነው የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዉበቱ አባተ ለ28 ተጫዋቾች ጥሪ አድርገዋል። አሰልጣኝ ውበቱ ቀደም ሲል ለ42 ተጫዋቾች ጥሪ አድርገው የነበረ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሃያ ስምንቱን ቀንሰው ከተቀሩት 24 ተጫዋቾች ጋር ዝግጅታቸውን እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
በምድብ አንድ የሚገኙት ዋልያዎቹ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ጥር 5 ቀን 2015 ዓ.ም ከሞዛምቢክ ጋር ያደርጋሉ። ሁለተኛውን የምድብ ጫወታቸውን ደግሞ ጥር 9 ቀን 2015 ዓ.ም ከአስተናጋጇ አገር አልጄሪያ ጋር ያደርጋሉ ። የመጨረሻ የምድብ ጫወታቸውን ደግሞ ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም ከሊቢያ ጋር እንደሚያደርጉ የወጣው መርኃ ግብር ያሳያል። ኢትዮጵያ ወደ ቻን ውድድር የተመለሰችው ከስድስት ዓመታት በኋላ ነው። የኢትዮጵያ ቤሔራዊ ቡድን በቻን የአፍሪቃ ዋንጫ ሲሳተፍ የአልጄሪያው ሶስተኛው ሆኖ ይመዘገባል። ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በ2006 ደቡብ አፍሪቃ ባስተናገደችው ቀጥሎም በተከታዩ የውድድር ዓመት በ2008 ርዋንዳ ባስተናገደችው ውድድሮች ተሳታፊ መሆን የቻለች ሲሆን በሁለቱም ውድድሮች ከምድብ ጫወታዎች ማለፍ ሳታችል ቀርታለች።
የዓለም ሻምፒዮናዋ የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድንን ጨምሮ የፈረንሳይ ፣ ክሮሽያ እና አፍሪቃዊቷ የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን አባላት ወደ የሀገራቸው ሲመለሱ የጀግና አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ሞሮኮ ጀግኖቿን ከነእናቶቻቸው ቤተመንግስት ድረስ ጋብዛ የክብር ሜዳይ በመሸለም አወድሳቸዋለች። ኳታርም 2022 አይረሴ ትዝታዋን በእግር ኳስ አፍቃሪያን ዘንድ ቀርጻ ያለፈችበትን ታሪክ መጻፍ ችላለች። ከተፋላሚ ሃገራት ደጋፊዎች ባሻገር ዓለምን ቁጭ ብድግ ያስደረገው አስደናቂው የውድድር ጊዜ ሌላ አራት ዓመት የሚያስጠብቅ መሆኑ ቅር ያሰኛል። ምናልባት ውበቱ ፣ ስሜቱ ጎልቶ እንዲወጣ ያስቻለውስ በዚህ ይሆን ? ቀጣዩ የዓለም ዋንጫም በሶስት የሰሜን እና ማዕከላዊ አሜሪካ ሀገራት በጎርጎርሳውያኑ 2026 ሊስተናገድ ቀጠሮ ይዞ ተሰናብቷል። ዩናይትድ ስቴትስ ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ ደግሞ አዘጋጆቹ ናቸው ። ይህ የዓለም የእግር ካስ ዋንጫ ከተጀመረ ወዲህ ሶስት ሃገራት በጋራ ሲያስተናግዱ የመጀመሪያው መሆኑ ነው።
ዓለማቀፉ የእግር ኳስ ማሕበር ፊፋ የዓለም ዋንጫ መጠናቀቅን ተከትሎ የሃገራት ደረጃን ይፋ አድርጓል። በዚህም ብራዚል በሰበሰበችው 1840 ነጥቦች የሃገራቱን ደረጃ ስትመራ ፤ የዓለም ሻምፕዮናዋ አርጀንቲና በሁለት ነጥቦች ዝቅ ብላ በ1838 ነጥቦች ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችላለች። በደረጃ ሰንጠረዡ ፈረንሳይ በ1823 ሶስተኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ቀደም ሲል ደረጃውን በአንደኝነት ስትመራ የነበረችው ቤልጅየም ቀደም ሲል ከሰበሰበችው ነጥቦች 34ቱን ጥላ በ1781 ነጥቦች ወደ አራተኛነት ተንሸራታለች። እንግሊዝ ደግሞ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። አፍሪካን ወክላ በዓለም ዋንጫው 4ኛ በመሆን ታሪክ ሰርታ የተመለሰችው ሞሮኮ ደግሞ በ1672 ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችላለች። በኳታር የዓለም ዋንጫ አስደናቂ ግስጋሴ አሳይታ የተመለሰችው ሞሮኮ ቀ,ደም ሲል ከነበረችበት 22ኛነት 11 ደረጃዎችን አሻሽላ ነው 11ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ የቻለችው። ሌላኛዋ አፍሪካዊት ሴኔጋል 19ኛ ደረጃ ተቀምጣለች። ኢትዮጵያ በደረጃ ሰንጠረዡ በ1091 ነጥቦች በመያዝ ርዋንዳን ተከትላ 138ኛ ደረጃ ተቀምጣለች።
ከዓለም ዋንጫ መለስ ስንል ዋነኞቹ የአውሮጳ የእግር ኳስ ሊጎች ከዛሬ ጀምሮ ወደ መደበኛ የውድድር መርኃ ግብራቸው ተመልሰዋል።
በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ቀን 9 ሰዓት ተኩል ላይ ቶተንሃም ከሜዳው ውጭ ተጉዞ ብሬንትፎርድን የገጠመበት የሊጉ የቦክሲንግ ዴይ የመጀመሪያ ጫወታ ነበር ። በጫወታው ቶተንሃም በብሬንትፎርድ ሁለት ለዜሮ ከመመራት ተነስቶ ሁለት አቻ ወጥቷል። ጎሎቹን ለብሬንትፎርድ ቪታሊ ጃኔልት እና ኢቫን ቶኒ ሲያስቆጥሩ ለቶተንሃም ደግሞ ሃሪ ኬን እና ፒየር ኤሚሌ አስቆጥረዋል። የቶተንሃሙ አሰልጣኝ ጣልያናዊው አንቶኒዮ ኮንቴ በዓለም ዋንጫው የዋንጫ ተፋላሚ የነበሩትን ሁለቱን ቁልፍ ተጫዋቾቻቸው የፈረንሳዩን ግብ ጠባቂ ሁጎ ሎሪስ እና የአርጀንቲናው ክርስትያን ሮሜሮ ማሳረፋቸው ነጥብ ለመጣል ሳያስገድዳቸው እንዳልቀረ ነው የታየው።
በሌሎች የሊጉ የዕለቱ መርሃ ግብር ምሽት አስራ ሁለት ሰዓት ላይ አራት ጫወታዎች እየተደረጉ ይገኛሉ ። ብራይተን ከሜዳው ውጭ ከሳውዝሃምፕተን ጋር ፤ ኒውካስትልም በተመሳሳይ ከሜዳው ውጭ ተጉዞ ከሌይስተር ሲቲ ጋር እየተጫወቱ ይገኛሉ ። በተመሳሳይ ክሪስታል ፓላስ ከ ፉልሃም እንዲሁም ኤቨርተን ከዎልቭስ ጋር በሜዳቸው እየተጫወቱ ይገኛሉ። የሊጉ ሌሎች ተጠባቂ ውድድሮች ምሽቱን ቀጥለው ሲደረጉ ምሽት ሁለት ሰዓት ተኩል ላይ ሊቨርፑል ከሜዳው ውጭ አስቶን ቪላን ሲገጥም መሪው አ,ርሴናል ደግሞ ምሽት አምስት ሰዓት ላይ ዋናው አጥቂው ብራዚላዊ ጋብሬል የሱስን በጉዳት ሳያሰልፍ ዌስትሃምን የሚስተናግድበት ጫወታ ተጠቃሾች ናቸው። ቀሪ ጫወታዎች ነገ ማክሰኞ ምሽት ይከናወናሉ።
ሊጉን አርሴናል በ37 ነጥቦች ሲመራ ማንችስተር ሲቲ በ32 ነጥቦች ይከተላል ፤ ኒውካስትል እና ቶተንሃም በ30 እና 29 ነጥቦች 3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ዎልቭስ ፣ ሳውዝሃምፕተን እና ኖቲንግሃም ፎረስት ደግሞ በ10 ፣ 12 እና 13 ነጥቦች ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።
በስፔይን የላሊጋ ውድድሮችም ከፊታችን ሐሙስ ምሽት ጀምሮ በሚደረጉ ሶስት ጫወታዎች ከዓለም ዋንጫው መልስ የሊጉን መጀመር ያበስራሉ ። ጊሮና ራዮ ቫልካኖን ፣ ሪያል ቤትስ ሪያል ቤትስ አትሌቲክ ክለብን እንዲሁም አትሌቲኮ ማድሪድ ኤልሼን የሚያስተናግዱበት የዕለቱ መርኃ ግብር ነው።
የጀርመን ቡንደስሊጋ ደግሞ የፊታችን ዓርብ መሪው ባየርን ሙንሽን ከሜዳው ውጭ አር ቢ ላይፕሽን በሚገጥምበት መርሃ ግብር ሊጉ ይጀመራል። ሁለቱ ክለቦች አንደኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ላይ እንደመቀመጣቸው ጫወታው ከወዲህ ከፍተኛ ግምት እንዲያገኝ እና በጉጉት ተጠባቂ እንዲሆን አድርጎታል። አብዛኞቹ የሊጉ ጫወታዎች የሚካሄዱት ግን በቀጣዩ ቀን ቅዳሜ ሲሆን እሁድ እና ሰኞም በተከታታይ የሚደረጉ ጫወታዎች እንዳሉ መርኃ ግብሩ ያመለክታል።
ታምራት ዲንሳ
እሸቴ በቀለ
