የታላቁ ኅዳሴ ግድብ ምረቃ
ረቡዕ፣ ጳጉሜን 5 2017
«በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በርካታ ፕሮጀክቶች ይገነባሉ» ጠ/ሚ/ር አቢይ አህመድ
ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጫናዎችን ተሻግሮ በኢትዮጵያውያን የገንዘብ መዋጮና ድጋፍ ተገንብቶ ዛሬ ለምረቃ በቅቷል። 233 ቢሊዮን ብር እንደወጣበት የሚነገረው ኅዳሴ ግድብ ዛሬ ሲመረቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ እንዳሉት በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የኒውክሌር ማብላ ያ ተቋምና የነዳጅ ማጣሪያን ጨምሮ የግዙፍ ፕሮጀክቶች ምረቃና ግንባታዎች ይከናወናሉ። በቀጣይ የሚገነቡ ፕሮጀክቶች ከ30 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ሀብት እንደሚጠይቁም አመልክተዋል።
የዛሬውን የኅዳሴ ግድብ መጠናቅቀ በማስመልከት አስተያየታቸውን ያካፈሉን አንዳንድ የአማራ ክልል ነዋሪዎች «ንድ ከሆንን የማንሠራው ነገር አይኖርም» ብለዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡን መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝምና ሰብዓዊ መብት መምህርና ተመራማሪው ዶ/ር ሲሳይ መንግሥቴ አንዱ ናቸው።
«የግድቡ ግንባታ በርካታ ውስብስብ ችግሮችን አልፏል» ዶ/ር ሲሳይ መንግሥቴ ከአአዩ
ዶ/ር ሲሳይ፣ የምረቃ ሂደቱን ከትናንት ምሽት ጀምሮ ሲከታተሉ እንደነበር አስታውሰው «የግድቡ መጠናቀቅ ደስታ ፈጥሮልኛል» ብለዋል። አፍሪካውያን እንደሚችሉ ኢትዮጵያ ምሳሌ መሆኗን አመልከተው፣ ይህም እንደ ዳግማዊ አደዋ የሚቆጠር ድል እንደሆነ አስምረውበታል። ግድቡ ውስብስብ ሂደቶችን አልፎ እዚህ ደርሷል ያሉት ዶ/ር ሲሳይ፣ «ታሪካዊ» ያሏቸው አካላት የግድቡን ሂደት ለማደናቀፍ ብዙ ቢጥሩም እንዳልተሳካላቸው ተናግረዋል።
በደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኝነት መምህርና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ዳምጠው ተሰማ የኅዳሴ ግድብን ማጠናቀቅ መቻላችን፣ በሕብረትና በአንድነት ከተነሳን ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን የመፈፀም አቅማችን ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
የግድቡ መጠናቅቀ ኢትዮጵያውያን ሌሎች ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት እንደሚችሉ ማሳያ ነውም ብለዋል። በጋራ መሥራት የማይቻል የሚመስለውን እንደሚቻል ኢትዮጵያውያን ለዓለም ማኅበረሰብ አሳይተዋልም ነው ያሉት።
«የግድቡ ፍፃሜ ከአደዋ ድል አያንስም» ሰለሞን እሸቱ ከመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ
የአደዋና የካራማራ ድሎች ተዋግተን ድል ማድረጋችን የአንድነታችን ምስጢር ነው ያሉት በመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግኑኝነት መምህር ሰለሞን እሸቱ የኅዳሴ ግድብ ፍፃሜም ከዚህ የተለየ እንዳልሆነ አስረድተዋል።
በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን የእነማይ ወረዳ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ደጉ አያሌው የቦንድ ግዥና የማስተባባር ሥራ ሲሰሩ እንደነበር አስታውሰው ግድቡ ለፍፃሜ መድረሱ እንዳስደሰታቸው ገልጠዋል። መላው የወረዳው ሕዝብ በግድቡ መጠናቀቅና ፍፃሜ በእጅጉ መደሰቱን ነው ለዶይቼ ቬሌ በስልክ የተናገሩት።
ምሁራኑ አሁን በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶችና ጦርነቶች እንዲወገዱና ሁሉም ለልማት በአንድ እንዲሰለፍ በአዲሱ ዓመት መንግሥትም ሆኑ ነፍጥ አንስተው የሚዋጉ ኃይሎች ወደ ሰላም እንዲመጡም ጠይቀዋል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ምረቃ ከተገኙ የሀገር መሪዎች መካከል የደቡብ ሱዳን፣ የሶማሊያ፣ የኬንያ የጅቡቲና የሌሎችም አገሮች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተገኝተዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ 1.78 ኬ ሜ ርዝመትና 145 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን 74 ትሪሊዮን ሊትር ውኃ ይይዛል፣ ግድቡ 5,100 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅምም እንዳለው ይገለፃል።
ዓለምነው መኮንን
ሸዋዬ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ